Quantcast
Channel: ስፖርት | ዘ-ሐበሻ (ZeHabesha) - Latest Ethiopian News Provider
Viewing all articles
Browse latest Browse all 419

ገነነ መኩሪያ (ሊብሮ) “የኃይሌ ገብረሥላሴ የብሔራዊ ቡድኑን የማሰልጠን ጥያቄ ድጋፍ ያሻዋል”

$
0
0

የምን ጊዜም ምርጡ አትሌታችን ሀይሌ ገብረስላሴ ሰሞኑን የኢትዮጵያ ብሄራዊ እግር ኳስ ቡድንን ለማሰልጠን በሚዲያ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ የሀይሌም ፍላጎትና ሀሳብ በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ ሀይሌ በኢትዮጵያ ሳይሆን በአለም ዝነኛ ስፖርተኛ ነው፡፡ 27 ሪከርዶችን የሰባበረ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በኦሎምፒክ የአስር ሺ ሜትሩን ድል መልሶ ያመጣና በሁለት ተከታታይ ኦሎምፒክ ባለድል ያደረገን ብርቅዬ አትሌታችን ነው፡፡ ሀይሌ ‹‹ይቻላል›› በሚለው የማነሳሻ ሀሳቡም ይታወቃል፡፡ ማንኛውም ነገር ጠንክሮ ከተሰራ ‹‹ይቻላል›› የሚል አቋም አለው፡፡ እሱም ይሄን መንገድ ለሌሎች በማሳየት አርአያ በመሆን ይታወቃል፡፡ ሀይሌ ሰሞኑን ለዚህ ሀሳብ ምን አነሳሳው ሲባል በኢትዮጵያ ወስጥ እግር ኳስ ተወዳጅ ነው፡፡

Ethiopia's long distance runner and marathon world record holder Haile Gebrselassie

ህዝቡ ለእግር ኳሱ ምን አይነት ፍቅር እንዳለው ያውቃል፡፡ ነገር ግን በእግር ኳሱ ደካማ ውጤት የህዝቡን ብሶትና ሮሮ(እሱም ከህዝቡ አንዱ አዛኝ ነው) በመመልከት የበኩሉን ሀገራዊ አስተዋጽኦ ለማድረግ እንደሆነ ይታመናል፡፡ እሱ በውድድር አለም በቆየበት ተሸናፊ ሳይሆን አሸናፊ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ህዝብ ከዳር እስከ ዳር አስደስቷል፤አስጨፍሯል፡፡ ሀይሌ አሳፍሮን አያውቅም፡፡ ለህዘቡ ቃል የገባውን ያደርጋል፡፡ በአትሌቲክስ አለም አደባባይ የኢትዮጵያ ባንድራ ሲውለበለብ በእግር ኳሱ ግን ይሄ ነገር የለም፡፡ ሀይሌም በአትሌቲክሱ ህዝቡ እንደረካና እንዳተደሰተ ‹‹ይቻላል ›› በሚለው መርሁ በእግር ኳሱ ይሄ ነገር እንዲኖር ይፈልጋል፡፡ እግር ኳስ ብሄራዊ ድኑ ከ60 እና 70 ደቂቃ ጀምሮ እንደሚዳከምና የአካል ብቃት ችግር እንዳለባቸው ገልጾ ይሄ ነገር እንዲቀረፍ እሱ የአካል ብቃት አሰልጣኝ ሆኖ ቢመደብ ለውጥ እንደሚመጣ ተናግሯል፡፡ እሱ ፈቃደኝነቱን አሳይቷል፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምላሽ ይጠበቃል፡፡

 

ሀይሌ ብሄራዊ ቡድኑ እንዲሰጠው ድጋፋችን መስጠት ይኖርብናል፡፡ ሀይሌ ብሄራዊ ቡድን ለማሰልጠን የጠየቀው እንደሌሎች አሰልጣኝ ደሞዝ እየተከፈለው ለማገልገል አይደለም፡፡ በብሄራዊ ስሜት ተነሳስቶ ብሄራዊ በድኑ ውጤታማ ሆኖ ህዝቡ እንዲደሰት ለማድረግ ነው፡፡ እሱ ደግሞ በኢንዱራንስ ስራ የታወቀ ነው፡፡ከዚህ በፊት ክሩገር የተባለ የጊዮርጊስ አሰልጣኝ ክለቡ በዛማሌክ ነጥብ ጥሎ ከወድድር ሲወጣ ‹‹የኢትዮጰያ ተጫዋቾች ከ60 ደቂቃ በላይ መጫወት አይችሉም›› ብሎ ተናግሯ ፡

፡የሀይሌም ሀሳብ ተመሳሳይ ስለሆነ ሀይሌ ጥያቄ አቅርቧል፡፡ እድሉ ሊሰጠው ይገባል፡፡ሀይሌ ከምንም ተነስቶ እንዲህ እንዳላለ ይታወቃል፡፡ ብዙ ነገር ከመረመረ በኋላ ጥያቄውን እንዳቀረበ ነው፡፡ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ዙሪያ ጥናት አድርገው አማራጭ ሀሳብ አለን ለሚሉ ፌዴሬሽኑ እድሉን ሊሰጥ ይገባል፡፡ ሀይሌም ከዚህ ጥያቄ አቅራቢዎች አንዱ ነው፡፡ነገር ግን ሀይሌ ችግሩ የአካል ብቃት ነው ብሏል፡፡እሱ አሰርቶ ለውጥ ከሌለ ችግሩ ‹‹እኔ ያልኩት አልነበረም›› ብሎ ለህዝቡ ማሳወቅ ይኖርበታል፡፡ አሱ የሚለውን አሰርቶ ውጤት ከሌለ ሌላ ነገር ውስጥ መግባት የለበትም(አስተዳደር፤አደረጃጀት፤ከታች ወርደን እንስራ የመሳሰሉት እንዳይደረደሩ) ፌዴሬሽኑ አማራጭ ሀሳብ ያላቸውን አቀርቦ ማሰራት አለበት፡፡ የሀይሌንም ሆነ የሌላውን ጥያቄ ‹‹ብሄራዊ ቡድኑ መሞከሪያ አይደለም›› ብሎ በር መዝጋት የለበትም፡፡ ምክኒያቱም አሁን እየተሰጠ ያለው ስልጠና በራሱ እየተሞከረ ነው ያውም 60 አመት ፡፡ ይህ ስልጠና 60 አመት ተሞክሮ ምንም ነገር አላስገኘም፡፡ ስለዚህ አማራጭ ሀሳብ ሲመጣ መሞከሪያ አይደለም በሚል ፌዴሬሽኑ ሌሎችን ሀሳብ መቃወም የለበትም፡፡(በእርግጥ የሀይሌ አማራጭ አይደለም) እናም ለሀይሌ ድጋፍ ስጡ፡፡ ግን ሀይሌም ችግሩ አካል ብቃት ብቻ ነው ብሎ ከመግባቱ በፊት ነገሮችን መዝኖና አመዛዝኖ መግባት አለበት፡፡

አካል ብቃት ለእግር ኳስ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው፡፡አንድ ተጨዋች ለጓደኛው አቀብሎ ያንን ለመቀበል መሮጥ አለበት፡፡90 ደቂቃ ለመጫወት ለእግር ኳስ አስፈላጊ ተብሎ የታመነበትን መስራት አለበት፡፡ ነገር ግን ለእግር ኳስ የሚስፈልገውን ነገር ሰርተን ብልጫ ከተወሰደብን ሌሎች ነገሮችን ከሌላ አቅጣጫ መመርመር አለብን፡፡ሀይሌ እንደሚያውቀው በረጅም ርቀት ሩጫ ውጤታማ ነን፡፡ ነገር ግን 100 እና 200 ሜትር በአፍሪካ ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን ሚኒማ ማምጣት እንዴት እንደቸገረን ያውቃል፡፡ ሀይሌ በተወዳዳሪነት ጊዜው የጋና እና የናጀርያ ሯጮችን ከእሱ ጋር ሲወዳደሩ አይቷል እንዴ? አላየም፡፡ የናጀርያና ጋና አትሌቶች በኦሎምፒክ በሺ0 እና 5 ሸ ውጤት ሊያመጡ ቀርቶ ሚኒማ እንኳን የላቸውም፡፡ እነርሱ ሳይስሩ ቀርተው ነው እንዴ? የሚያሰራቸው ሰው አጥተው አይደለም፡፡ ጎበዝ አሰልጣኝ አላቸው፡፡ ሀይሌም እንደሚያውቀው ብዙ ጊዜ የናይጀርያና ጋና አትሌቲክስ ኢንስትራክተሮች ናቸው እኛን አትሌቶት አሰልጣኞች የሚያሰለጥኑት ፡፡ ይህን ያህል ብቃት ያላቸው አሰልጣኝ እያላቸው በረጅም ርቀት ሩጫ ሰው ማፍራት አልቻሉም ፡፡ ነገር ግን ናይጀርና ጋና በአጭር ርቀት ሩጫ ኦሎምፒክ ፋይናሊስት እስከመሆን የደረሱ ናቸው፡፡ በፍሪካ በሴትም በወንድም በ100 እና 200 ሻምፒዮና ናቸው፡፡ እንግዲህ እነርሱ በአጭር ርቀት ተፈጥሮን ጥገኛ ባደረገ መልኩ ሰርተው ውጤት አመጡ ፡፡በረጅም ርቀት ሞከሩ አልቻሉም ፡፡እኛም በረጅም ርቀት ተፈጥሮን ጥገኛ ባደረገ መልኩ ሰርተን ውጤት አመጣን፡፡ በ100 እና 200 አስቸጋሪ ሆነብን፡፡

እንግዲህ እግር ኳስ ፍጥነትና ጉልበት ስለሚጠይቅ ይሄን ነገር እናሟላለን ወይ ብለን ስንጠይቅ እንደማናሟላ በአትሌቲክሱ እያየን ነው፡፡ስለዚህ እነ ናጀርያና ጋና ጋር ስንገጥም የሚበልጡን በዚህ ከሆነ ከዚህ ነገር መውጣት እንጂ ሁል ጊዜ እዛ ውስጥ መንቦራጨቅ የለብንም፡፡ ፍጥነት ጉልበት ለእግር ኳሱ አስፈላጊ ነው፡፡ ለፍጥነት ማሻሻያ ተብሎ በእግር ኳሱ ውስጥ በስልጠናው የተቀመጡ ነገሮች አሉ(አካል ብቃት ውስጥ ስለሚመደብ) ለዚህ የሚሆን ልምድ ሰርተን መብለጥ ካልቻለን ይሄን በሌላ መተካት ነው፡፡ምክኒያቱም ለእግር ኳስ አስፈላጊ ነው ተብሎ በሚታመንበት ነገር ብልጫ ከተወሰደብህ ይሄን በሌላ መተካት ነው፡፡እኛም ማድረግ ያለብን ፍጥነትን በሌላ መተካት ጉልበትን በሌላ መተካት እንጅ እዛ ውስጥ ሆነን እኝኝኝኝኝኝኝኝ ……ብንል ምንም አናመጣም፡፡ብዙ የውጭ አሰልጣኞች መጥተው ቴክኒክ አላችሁ የአካል ብቃት ነው ችግራችሁ ይሉና ያንን ደካማ ነገር ለመሸፈን የአካል ብቃት ያሰሩና ችግሩ አይቀረፍ፡፡ሀይሌም እንደነዛ ሰዎች የአካል ብቃት ችግር መሆኑን አይቷል እሱም እንደሌሎቹ እዛ ውስጥ ያለውን መፍታት ሳይሆን ማባባስ ይሆናል፡፡እስካሁን የተበላሸነው እነ ናይጀርያ ጥሩ በሆኑበት እነርሱን መግጠማችን ነው ችግር ያመጣብን፡፡ እኛ ጥሩ በሆንበት ነገር አሰልጥኞ የተሻለ እንድንሆን የሚያድርግ ሰው ነው የሚያስፈልገው፡፡39 የውጭ አሰልጣኝ አምጥተን በዚህ መንገድ ሰርተን አልተለወጥንም፡፡ በተለይ ከምእራብና ሰሜን አፍሪካ ጋር ስንጫወት ይህ ነገር ጎልቶ ይወጣል፡፡ እነርሱ በተፈጥሮ ከእኛ የተሻለ ጉልበት አላቸው፡፡ብቻ ለብቻ ስንገኛኝ እነርሱ በዚህ የተሸለ ስለሆኑ ይበልጡና ፡፡ በጉልበት ሲያሹን ሲሸራርፉን እየተዳከምን እንሄዳል፡፡ያን ጊዜ ኢንዱራንሳችንም ይጠፋል ፡፡ ሀይሌ በራሱ በኩል በሩጫ ያለውን አካል ብቃት ነው ያየው፡፡ ሩጫ ዝም ብሎ መሮጥ ነው ንክኪ የለውም ፡፡ እየተገፈታተሩ እየተደባደቡ ቢሮጡ ለነሀይሌም ያስቸግራል፡፡

ባለፈው ከ9 ወር በፊት በአ/አ ስታዲየም ፌስቲቫል ጨዋታ እነ ቀነኒሳን ጨምሮ አትሌቶች እግር ኳስ ሲጫወቱ ምን ያህል እንደተቸገሩ ታይቷል፡፡ በ1992 ዓ.ም ለሲድኒ ኦሎምፒክ የሚዘጋጀው ቡድን በስታዲየም ልምምዱን በመሮጫ በትራኩ ላይ ያደርጋል፡፡ የእግር ኳስ ብሄራዊ በድኑ እነ ኩኩሻ፤ ሚኬሌ ሌሎችም ሜዳው ላይ እየተለማመዱ ነው፡፡ ትራኩን ዳኞች ኩፐር ቴስት ስለሚፈተኑበት ለ12 ደቂቃ ያህል አትሌቶቹ ፈቃድ ተጠይቀው ለቀቁላቸው ፡፡ አትሌቶቹ ሜዳ ውስጥ ገብተው ከብሄራዊ እግር ኳስ ቢድን ጋር ጫወት ጀምሩ፡፡ ‹‹ትችሉናላችሁ አትችሉንም›› በሚል ተፎካከሩና ተጋጠሙ፡፡ቀድመው የደከሙት እነ ሀይሌ የነበሩበት አትሌቶች ናቸው ፡፡ አትሌቶቹ ታክል ሲገቡ፤ ሲገፈታተሩ፤ በአጭር ቦታ ሲመላለሱ፤ ኳሱን ሲገፉ፤ ለመንጠቅ ሲታገሉ ተዳከሙ ፡፡ የእግር ኳስ ተጫዋቾቹ ግን አልደከማቸውም፡፡ አትሌቲክስ ውስጥ ይሄ ነገር የለም፡፡ እግርኳስ ውስጥ አብዛኛው ነገር ንክኪው ነው፡፡ ንክኪው ጉልበት ስለሚጠይቅ ይሄ ነገር ያዳክመናል ያን ጊዜ ቡድናችን ሲዝረከረክ ተዳከሙ ይባላል፡፡ መዳከሙ አይቀሬ ነው ፡፡ ንክኪው ጉልበት ይጠይቃል ይበዘብዛል ፡፡ንክኪው የሚመጣው ብቻ ለብቻ ባለው ግንኙነት ነው፡፡መጀመሪያ ብቻ ለብቻ የምንገናኝበትን ነገር ካስቀረን ስለ ሌላው ነገር መቅረፉ አስቸጋሪ አይሆንም፡፡የብቻ ለብቻውን ነገር በረዳት ማስቀረት ይቻላል፡፡እኛ ቴክኒኩ አለን፡፡ ቴክኒኩ ደግሞ ረዳትን ለመጠቀሚያ ዋነኛው መሳሪያ ነው፡፡

ስራዎቻችን እዚህ ላይ አተኩረን ይሄንን ለማገዝ የሚያሰችል አካል ብቃት ከተሰጠ ችግሩ ይፈታል፡፡ነገር ግን አሁን ሀይሌ እንደሚለውና ሌሎችም የውጭ አሰልጣኞች እንዳሰሩት ጥሬ አካል ብቃት ስራ ለምእራብና ሰሜን አፍሪካ ቡድኖች አሳልፎ የሚሰጠን ነው፡፡ለሜክሲኮ ኦሎምፒክ ማጣሪያ የእግር ኳስ ብሄራዊ ቡድን ተጋባዥ ሆኖ ሄደ፡፡ እግር ኳስ ቡድኑም አትሌቲክሱም ወንጂ ላይ ይለማመዱ ነበር፡፡ አበበ ቢቂላ እግር ኳስ ስለሚወድና አልፎ አልፎ ለክፍሉ ስለሚጫወት እየገባ ይጋጠም ነበር ነገር ግን እየደከመው ይወጣ ነበር፡፡ አበበ ሀይልና ትንፋሽ በሚጠይቀው ሩጫ ነው የሚታወቀው፡፡ ነገር ግን በእግር ኳሱ ውስጥ ባለው አካል ብቃት አልቻለበትም፡፡ኤፍሬም ሀይሌ ለጊዮርጊስ፤ ሙገር፤ እርሻና ለወጣት ቡድን ተጫውቷል፡፡ አፍሬም 14 አመት እግር ኳስ ተጫውቶ ካቆመ በኋላ አሁን በማራቶን እየሮጠ ነው፡፡የተሻለ ሰዓትም አለው፡፡ኤፍሬም በእግር ኳስ እንደማንኛወም ተጫዋች ይዳከማል፡፡ ነገር ግን በአትሌቲክሱ ውጤታማ ነው(የእግር ኳስ ተጨዋቾቻችን የኢንዱራንሱ ችግር እንደሌለባቸው የኤፍሬም ተሞክሮ ይነግረናል)፡፡ ሀይሌም እነዚህን ነገሮች መርምሮ መግባት እንዳለበት ነው፡፡፡ሀይሌ በእግር ኳስ አሰልጥኖ አያውቅም ግን ጎበዝ አትሌት ነው ፡፡ሀይሌን ውጤታማ ያደረጉት ዶክተር ወልደመስቀል ናቸው፡፡ከሀይሌ ይልቅ በማስልጠኑ ዶክተር ይሻላሉ፡፡ ድሮ አቶ ይድነቃቸው ብዙ ጊዜ ቡድኑ በምእራብ ቡድኖች ሲሸነፍና በአካከል ብቃት ተዳክሞ ሲታይ እነንጉሴ ሮባ ለብሄራዊ ቡድኑ የአካል ብቃት አሰልጣኝ እስከመሆን ደርሰው ነበር፡፡ያኔ ንጉሴ በአትሌቲክሱ ውጤታማ ነበሩ፡፡፡፡ዶከተር ወልደመስቀል ለሰባተኛ አፍሪካ ዋንጫ የተጫወተውን ቡድን ያዘጋጁት እሳቸው ነበሩ፡፡

ቡድኑ በሶስቱ ጨዋታ ተዳክሞና ተበልጦ ነው የታየው ፡፡በአይቮሪኮስት 6ለ1 ተሸነፈ (ይሄ እስካሁን በአፍሪካ ሪከርድ ነው) በምድብ ጨዋታ 12 ግብ ተቆጠረብን(ይሄም እስካሁን ሪከርድ ነው፡፡በምድብ ጨዋታ 12 ግብ በአፍሪካ ዋንጫ 12 የተቆጠረበት የለም) ቡድኑ ሜዳ ላይ የምእራብ አፍሪካ በድኖችን መቋቋም አልቻለም፡፡ዶከተር ወልደመስቀል ከአካል ብቃቱ አሰልጣኝነት ሌላ ጊዮርጊስን ዋናው ቡድን አሰልጥነዋል ፡፡(እነመንግስቱ ወርቁ የነበሩበትን)ካምፓላ ሲቲ በተባለ የኡጋንዳ ክለብ 4ለ0 ሲሸነፍ አሰልጣኝ ነበሩ፡፡ከዚያ በኋላ ሙሉ ለሙሉ ወደ አትሌቲክሱ ገቡ ፡፡ግን እሳቸውም ሆነ ንጉሴ የተናገሩት (ተጨዋቹ ለእግር ኳሱ ክፍያ አያገኙም፤በሳምንት ሁለት ጊዜ ብቻ እየተሰራ ለውጥ አይመጣም፤በካምፕ መቀመጥ አለባቸው፤መደበኛ ስራ መስራት የለባቸውም ያን ጊዜ ከስራ እየመጡ ትሪኒንግ ይሰሩ ነበር) ያን ጊዜ ይሄ ነገር ቀረበ፡፡ አሁን እነዚያ ችግሮች ሁሉ ተፈትተዋል ሜዳ ላይ ያለው ድክመቱ ግን እንደ ትላንትናው ነው፡፡ ዶክተር በእግር ኳሱ ብዙ ከሰሩ በኋላ ለውጥ ስላልተገኘ ወደ አትሌቲክሱ መጡ ፡፡ እዚያ ውጤታማ ሆኑ፡፡ ከአትሌቲክሱ አሰልጣኝ ሌላ እነ እስጢፋኖስን የመሰሉ የቦክስ አሰልጣኞች ለብሄራዊ ቡድኑ የአካል ብቃት ሆነው ሰርተዋል ግን በዚህ በኩል ያለው ችግር አልተቀረፍም ፡፡

ሀይሌም ከነ ንጉሴ ሮባ ከነወልደመስቀልና ከሌሎችም(በእግር ኳሱ ሰሩ) የአትሌቲክስ አሰልጣኞች በኋላ እነደነርሱ ችግሩ አካል ብቃት ነው ብሎ መጥቷል፡፡ለማኛውም ተሰጥቶ ሞክሮ ትክክለከኛውን ነገር ሊነግረን ይችል ይሆናል፡፡ወደ ስራው ከመግባቱ በፊት የነዶክተር ወልደመሰቀልን ተሞክሮ አይቶ እሳቸውን ጠይቆ ቢጋባ የተሻለ ነው፡፡ በእግር ኳሱ ያለው ችግር ግን ሀይሌ ከሚለው መውጣት እንጅ ሀይሌ ችግር ነው ባለው በኩል መስራት እንዳልሆነ የትላንቱ ተሞክሮ ነግሮናል፡፡ለማንኛውም ይሰጠውና አሰርቶ እውነቱን ይንገረን::

The post ገነነ መኩሪያ (ሊብሮ) “የኃይሌ ገብረሥላሴ የብሔራዊ ቡድኑን የማሰልጠን ጥያቄ ድጋፍ ያሻዋል” appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 419

Trending Articles