በማንችስተር ዩናይትድ ዘንድ ክስተት ከሆኑ ተጨዋቾች መሃከል አንዱ ነው፣ ጆሴ ሊንጋርድ፡፡ አሰልጣኝ ሉዊስ ቫን ሃል ዘንድሮ በዋናው ቡድን በቂ የመሰለፍ ዕድል ከሰጧቸው ተጨዋቾች መሃከል የሆነው ሊንጋርድ ለአሰልጣኙ እምነት ምላሽ ሰጥቶ አስደስተዋቸዋል፣ ቫን ሃል እንግሊዛዊውን ወጣት ኮከብ በተለያዩ ቦታዎች አጫውተው እየጠቀሙበት ይገኛሉ፣ የግራ እና ቀኝ መስር አማካይ ሆኖ መጫወት ይችላል፡፡ የ23 ዓመቱ እንግሊዛዊ በ10 ቁጥር ቦታ ላይ እንዲጫወት ዕድሉ ሲሰጠው አጋጣሚውን የመጠቀም ችግር የለበትም፡፡
ባለፈው ዓመት በውሰት ለደርቢ ካውንቲ ተሰጥቶ ብቃቱን ወደላቀ ምዕራፍ ያሸጋገረው ሊንጋርድ ከአጥቂ ጀርባ ሆኖ መጫወት እንዳስደሰተው ገልጿል፡፡ ቦታው ላይ በርካታ በርካታ ተጨዋቾች ይገኛሉ፡፡
ሜምፊስ ዴፓይ በግራ መስመር በኩል ቢጫወትም እዚህ ቦታ ላይ የመጫወት ችግር የለበትም፡፡ ሁዋን ማታ ለዚያ ቦታ የተሰራ ይመስላል፣ ጉዳት ላይ የሚገኘው ዌይን ሩኒ ከዕድሜው መግፋት ጋር ተያይዞ እዚህ ቦታ ላይ ሲጫወት ይበልጥ አቅሙን አውጥቶ ይጠቀማል፣ ሄሬራ ደግሞ በተደራቢ አጥቂነት ሲሰለፍ ጎሎችን ማስቆጠር ይችላል፡፡
ዘንድሮ በሁሉም ውድድሮች 31 ጨዋታዎችን ፈፅሞ አምስት ጎሎችን በማስቆጠር ስኬታማ የውድድር ዘመን እያሳለፈ እንደሆነ አረጋግጧል፡፡፣ ከምንም በላይ በማንቸስተር ደርቢ ጨዋታ ያሳየው አቋም የሁሉንም ትኩረት ስቧል፣ ተጨዋቹን የደርቢ ጨዋታው በዘንድሮ የውድድር ዓመት ምርጥ ብቃትህን ያሳየህበት ነው የሚል ጥያቄ ስታነሱበት ‹‹አዎን፣ አሰልጣኙም ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በውድድር ዓመቱ ካሳየሁት ብቃት ምርጡ እንደሆነ ነግሮኛል፣ በግልም ይሄ ስሜት ተሰምቶኛል›› የሚል ምላሽ ይሰጣል፡፡
‹‹እርግጥ ነው የማሸነፊያን ጎል ያስቆጠረው ማርክስ (ራሽፎርድ) ነው፤ ከአካዳሚው የተገኘ ሌላ ተጨዋች በመሆኑ መጪው ዘመን ለማንቸስተር ዩናይትድ ብሩህ እንደሆነ ማረጋገጫ ነው፡፡ በእርሱ ጎል ወሳኙን ጨዋታ በድል መወጣት አስደሳች ስኬትን ይፈጥራል›› የሚል መረጃን የሚሰጠው ሊንጋርድ መጫወት ስለሚችልበት ቦታ ስትጠይቁት ‹‹ሁልጊዜም ቢሆን በ10 ቁጥር ቦታ ላይ መጫወት ያስደስተኛል፣ እዚያ ቦታ ላይ ስትጫወት በርካታ ኳሶች ይደርሱሃል፣ የጨዋታውን እንቅስቃሴ መምራት ትችላለህ፡፡ በእርግጥ የግራ ወይም የቀኝ መስመር አማካይ ሆኜ የመጫወት ችግር የለብኝም፡፡ በአጠቃላይ አሰልጣኙ በጠየቀኝ ቦታ ላይ ለመጫወት ዝግጁ ነኝ፡፡ ነበዚህ ወቅት ይሄ ቦታ ነፃ ሚና ያለው ነው፤ እዚህ ቦታ ላይ የሚጫወት ተጨዋች በነፃነት የመጫወት ችግር የለበትም፡፡ እዚያ ቦታ ላይ ሆኖ አዳዲስ ነገሮችን መፍጠር ይችላል፤ ጎሎች ያስቆጥራል፣ ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን መስጠት ይችላል፡፡ ጎሎችን ያስቆጥራል፤ ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን ያቀብላል፣ ነገር ግን የዚያኑ ያህል በጥለቀት ወደ ኋላ ተመልሶ የመከላከሉን ኃላፊነት በአግባቡ የመወጣት ግዴት አለበት›› የሚል ምላሽ ይሰጣል፡፡
ለእንግሊዝ ከ21 ዓመት በታች የተጫወተው ሊንጋርድ ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር ለከርሞ በቻምፒዮንስ ሊግ ለመሳተፍ እቅድ ይዟል፡፡ እነሆ ከስካይ ስፖርት ጋር ያደረገው ቃለምልልስ፡-
ጥያቄ፡– በውድድር ዘመኑ ከተደረጉ ጨዋታዎች የደርቢው ጨዋታ ምርጡ ነው ማለት ይቻላል?
ሊንጋርድ፡- ትክክል ነው፣ በመጀመሪያ ደረጃ መሳተፍ ከምፈልግባቸው ጨዋታዎች መሀከል የማንችስተር ደርቢ ቀዳሚውን ቦታ ይወስዳል፡፡ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ አሰልጣኙ በውድድር ዓመቱ ካደረግኳቸው ጨዋታዎች ይሄ ቀዳሚው እንደሆነ ነግሮኛል፤ በዚያ ጨዋታ ላይ በተደራቢ አጥቂ ቦታ ላይ (10 ቁጥር) መጫወቴ አስደስቶኛል፡፡ እዚያ ቦታ ላይ ስጫወት የምቾት ስሜት ይሰማኛል፣ እዚያ ቦታ ላይ በርካታ ኳሶችን ታገኛለህ፤ ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን የማቀበል ችግር አይገጥምህም፡፡ የፈለግከውን ነገር ለመስራት የሚያስችል ዕድል ይፈጥርልሃል፣ ጎሉን ያስቆጠረው (ማርኮስ) ራሽፎርድ መሆኑ የተለየ ስሜት ፈጥሮብናል፣ ምክንያቱም የተገኘው ክለቡ ከሚገኝበት አካባቢ እና አካዳሚ ውስጥ ነው፡፡
ጥያቄ፡– አሰልጣኝ ስዊስ ቫን ሃልም ተደራቢ አጥቂ ቦታ የአንተ ምርጡ እንደሆነ ጠቅሰው ነበር፡፡ እዚህ ቦታ የአንተ ምርጡ እንደሆነ ጠቅመው ነበር፤ እዚያ ቦታ ላይ መጫወት ያስደስትሃል?
ሊንጋርድ፡- በግሌ 10 ቁጥር ቦታ ላይ መጫወት ያስደስተኛል፡፡ እዚያ ቦታ ላይ ስትጫወት በርካታ ኳሶችን ያገኛለህ፣ የጨዋታውን አቅጣጫ ለመመራት ያስችልሃል፣ እርግጥ ነው በቀኝ መስመር አማካይ ሆኜ መጫወት ያስደስተኛል፡፡ በግራ መስመር በኩልም እንዲሁ፡፡ ሆኖም አሰልጣኙ በየትኛውም ቦታ ላይ እንድጫወት ዕድሉን ከሰጠኝ አጋጣሚውን ለመጠቀም ዝግጁ ነኝ፡፡
ጥያቄ፡– የ10 ቁጥር ሚና የተለወጠ ይመስልሃል? በፊት እዚህ ቦታ ላይ የሚጫወቱ ተጨዋቾች ማጥቃቱ ላይ ትኩረት የሚያደርጉ እና በቴክኒክ ረገድ የተዋጣላቸው ነበሩ፤ ሆኖም አሁን ሚናው ተለውጧል ማለት ይቻላል?
ሊንጋርድ፡- በአሁኑ ሰዓት እዚህ ቦታ ላይ መጫወት ነፃነት የሚሰጥ ሆኗል፤ እዚያ ቦታ ላይ ስትጫወት ሜዳውን አካልለህ በመጫወት ምንም ነገር እንዲፈጠር ታደርጋለህ፤ ቡድኑን የሚጠቅም አዳዲስ ነገሮች ትፈጥራለህ፤ ወሳኙ ነገር እንዳለ ሆኖ ወደ ኋላ ተመልሰህ መከላከል ግድ ይልሃል፡፡
ጥያቄ፡– ኢትሃድ ላይ ማንቸስተር ሲቲን ባሸነፋችሁበት ጨዋታ ጨዋታው የሚወድቀውን አካላዊ ፈተና በብቃት ተወጥተሃል፣ ይህ ተክለ ሰውነትህ አካላዊ ፈተናዎች ጋር ተፃራሪ ነው?
ሊንጋርድ፡- በፕሪሚየር ሊጉ ግዙፍ ከሚባሉ ተጨዋቾች መሀካል ቀዳሚውን ቦታ ከሚወስደው ያያ ቱሬ ጋር መፋለም ቀላል አይደለም፡፡ ፈርናንዱንሆንም በዚህ ተርታ የሚካተት ተጨዋች ነው፡፡ ስለዚህ ፈተናው ቀላል አይሆንም፡፡ እኔ ብቻ ሳልሆነ ሌሎች የቡድናችን ወጣት ተጨዋቾችም ለገጠማቸው ፈተና ራሳቸው ዝግጁ አድርገው በአግባቡ ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል፡፡ አማካዩ ክፍል ላይ የማይክል (ካሪክ) ሚና የላቀ ነበር፡፡ ልምዱን ተጠቅሞ ሊመራን ነበር፡፡ ጨዋታውን ተቆጣጥሮ ያጠናቀቀበት መንገድ በጣም ይገርማል፡፡ ወሳኔ ነገር የምትጫወትበት መንገድ ነው፡፡ በሊጉ ማንቸስተር ሲቲን ጨምሮ በአማካይ ክፍሉ ላይ በርካታ ግዙፍ ተጨዋቾች አሉ፡፡ በደርቢው ጨዋታ ራሴን በአካልም ሆነ አዕምሮ ዝግጁ ማድረግ ነበረብኝ፡፡
ጥያቄ፡– ሪዮ ፈርንዲናንድ በቅርቡ ‹‹ጄሴ ሲንጋርድ አስደናቂ ተጫዋች ነው፡፡ በእርሱ ዕድሜ የሚገኙ ተጨዋቾች የሚያደርጉትን ከኳስ ውጭ ድንቅ እንቅስቃሴ ያከናውናል›› ብሎ ነበር፡፡ ይሄንን አስተያየት ሰምተሃል?
ሊንጋርድ፡- አዎን፤ በተለይ በ10 ቁጥር ቦታ ላይ ስትጫወት የዚህ አይነት ብልሃት ሊኖርህ ይገባል፡፡ ያለቀለት ኳስ ለማቀበል በዙሪያ ያሉትን ነገሮች የመቆጣጠር ብቃትህ እና እይታህ ወሳኝነት አለው፡፡
ሆኖም የሪዮ አስተያየት በራሱ የመተማመን ስሜትህን ከፍ ያደርገዋል፡፡ ሁልጊዜም ቢሆን ከእርሱ ጋር ያለማቋረጥ እንወያያለን፡፡ አሁንም ድረስ የእርሱን ምክር እየተገበርኩኝ እገኛለሁኝ፡፡ በየጊዜው ይከታተለኛል፤ በየጊዜው እንወያያለን፤ እርሱም ቢሆን ይከታተለኛል፡፡
ጥያቄ፡–በደርቢው ጨዋታ የቀድሞው የሊቨርፑል ተጨዋች ዳኒ መርሬ የጨዋታው ኮከብ እንደነበርክ ጠቅሷል…?
ሊንጋርድ፡- የዚህ አይነት አስተያየቶች ጠንክረህ እንድትሰራ እና ለድል ያለህን የረሃብ ስሜት ከፍ ያደርገዋል፡፡ በቀጣይ ያለ ማቋረጥ እና መዘናጋት ጠንክሬ መስራቱ ይቀጥላል፡፡ ይህ ዓመት የመጀመሪያዬ በመሆኑ ገና ያላሳካኋቸው በርካታ ነገሮች አሉ፡፡ በቀጣይ ጠንክሬ መስራቴን እቀጥላለሁኝ፡፡
ጥያቄ፡– በየጨዋታው ቋሚ ተሰላፊ መሆንህ በራስ የመተማመን ስሜትህን አጎልብቷል ማለት እንችላለህ?
ሊንጋርድ፡- በየጨዋታው ቋሚ ተሰላፊ መሆን በራሱ የመተማመን ስሜት እንደሚያጎለብተው ጥርጥር የለውም፤ ዘንድሮ በራስ የመተማመን ስሜቴን ያሳደገው ይኸው ያለማቋረጥ መጫወቴ ነው፤ ወሳኙ ነገር በሜዳ ውስጥ የምታሳየው ብቃት እንደሆነ አያጠራጥርም፡፡ ተጨማሪ ጎሎችን ባስቆጥር ደስተኛ እሆናለሁኝ፡፡ በቀጣይ ይሄ ፍላጎቴ እውን እንደሚሆን ጥርጥር የለውም፤ በቀጣዩ ዓመት ይበልጥ ተጠናክሬ እና ውጤታማ ሆኜ እመለሳለሁኝ፡፡
ጥያቄ፡– ከተደራራቢ እና ፈታኝ የጨዋታ ፕሮግራሞች በኋላ የዓለም አቀፍ (ብሔራዊ ቡድን) ጨዋታዎች መከናወናቸው እንደ በጎ የሚታይ ነገር ነው?
ሊንጋርድ፡- እርግጥ ነው ጥቂት እረፍትና ቀለል ያለ የእረፍት ጊዜ ማግኘት ያስደስታል፡፡ ልምምዱ ሲቀንስ የእረፍት ጊዜ ማግኘት ይቻላል፤ ከሪዘርቭ ቡድኑ የመጡ ተጨዋቾችም አብረውን ልምምድ ሲሰሩ ነበር፡፡ ጥቂት ቀናት እረፍት ማግኘታችን ፍም ያስደስታል፡፡ ባለፉት ዓመታት በፋሲካ በዓል ሰሞን ጨዋታዎች ነበሩ፡፡ አሁን ግን የእረፍት ጊዜ አለው፡፡
ጥያቄ፡– ማንቸስተር ሲቲን ማሸነፍ እስከ አራተኛ ያለውን ደረጃ ይዞ ለመፈፀም ምን ያል አስተዋፅኦ አለው?
ሊንጋርድ፡- ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ሲቲን ማሸነፍ ወሳኝ ነበር፡፡ ይህንንም በሚገባ አሳይተናል፡፡ የደርቢ ጨዋታዎች ሁልጊዜም ትኩረት ያገኛሉ፡፡ የአሸናፊውን ቡድን ሞራል የማነሳሳት አቅም አላቸው፡፡ ደጋፊዎቻችን ጨዋታውን በጉጉት ስሜት ሆነው ይጠብቃሉ፡፡ እኛ ደግሞ እነርሱን ለማስደሰት እንፋለማለን፤ ጨዋታውን በድል ስንወጣ ደግሞ ይበልጥ ሁሉም ነገር ያስደስታል፡፡ ጨዋታውን ብናሸንፍ ኖሮ ነገሮች ይበልጥ ፈታኝ ይሆኑ ነበር፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን እስከ አራተኛ ያለውን ደረጃ ይዘን ለመፈፀም ጥረት እያደረግን እንገኛለን፡፡ የቡድናችን ተጨዋቾች በየዓመቱ በቻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡ ይህ ህልማችን እውን እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁኝ፡፡ ማሳካትም እንችላለን፡፡
ጥያቄ፡– የውድድር ዓመትን መለስ ብለህ ስትቃኘው ከጠበቅከው የበለጠ እንደሆነ ይሰማሃል?
ሊንጋርድ፡- አዎን ትክክል ነው፡፡ በኤፍኤ ካፕ ፍፃሜ ዌምብሌይ ላይ ብጫወት ደስ ይለኛል፡፡ ለፍፃሜ ከቀረብን ዋንጫውን ማንሳት እንችላለን፡፡ ከዚህ ውጭ እስከ አራተኛ ያለውን ደረጃ ይዞ መፈፀም ሌላው ዓላማችን ነው፡፡ በግሌ ትክክለኛ ነገሮችን ለመፈፀም እሻለሁኝ፡፡ ይህንን ለማሳካት ደግሞ በሜዳ ውስጥም ሆነ ከሜዳ ውጭ ጠንክሬ እየሰራሁኝ እገኛለሁኝ፡፡ ሉዊስ ቫን ሃል ይህንን በሚገባ አስተውሏል፡፡ እርግጥ ነው በወጣት ተጨዋቾች መጠቀም አደጋ ቢኖውም የተጣለብህ እምነት አስደሳች ነው፡፡ አሁን የምንገኘው በመጀመሪያው ዓመት ላይ ነው፣ በምፈልገው ደረጃ የተሳካ ነገር አለ ብዬ አላስብም፡፡ ስለዚህ በቀጣይ ጠንክሬ መስራቴን እቀጥላለሁኝ፡፡
ጥያቄ፡– ከንግግርህ በመነሳት በስኬትህ እንደማትኩራራ ግልፅ ነው፡፡ አሁን የምትፈልገውን ነገር በማሳካት ሂደት ውስጥ ነህ ማለት ይቻላል?
ሊንጋርድ፡- በጭራሽሽ በግሌ በምንም አይነት መልኩ መዘናጋት አልፈልግም፡፡ እስከ ውድድር ዓመቱ መጨረሻ በርካታ ጨዋታዎችን በሙሉ መፈፀም እፈልጋለሁኝ፤ በኤፍኤካፕ እስከ ፍፃሜ በመጓዝ በሊጉ እስከ አራተኛ ያለውን ደረጃ ይዘን መፈፀም አለብን፡፡
የሌንጋርድ መረጃዎች
ስም፡- ጆሴ ኤሊስ ሊንጋርድ
የትውልድ ዘመን፡- ዲሴምበር 15/1992
ዕድሜ፡- 23
የትውልድ ቦታ፡- ዋሪንግተን/እንግሊዝ
ቁመት፡- 1.75 ሜትር
ቦታ፡- የአማካይ አጥቂ
ክለብ፡- ማንቸስተር ዩናይትድ
የማልያ ቁጥር፡- 35
የዩናይትድ የወጣት ቡድን ቆይታ፡- 2000-2011
የዋና ቡድን ቆይታ
2011…..ማንችስተር ዩናይትድ
2012/13….ሌይስተር ሲቲ (ውሰት)
2013/14… በርሚንግሃም ሲቲ (ውሰት)
2014… ብራይተን ኤንድ ሆቭ አልቢዮን (ውሰት)
2015… ደርቢ ካውንቲ (ውሰት)
ብሔራዊ ቡድን
2008…. እንግሊዝ ከ17 ዓመት በታች
2013-2015…. እንግሊዝ ከ21 ዓመት በታች