ማንችስተር ዩናይትድ ለአንቶኒ ማርሻል ግዥ 38 ሚሊየን ፓውንድ ሂሳብን ለሞናኮ ሲከፍል ሆላንዳዊው አሰልጣኝ ሉዊ ቫንሃል የእብደት ተግባርን የፈፀሙ ተደርገው በአንዳንዶች ተቆጥሮባቸው ነበር፡፡ ለአንድ የ19 ዓመት ወጣት 36 ሚሊዮን ፓውንድ እጅግ ውድ የሚባል ዋጋ ነው የሚል አስተያየትን የሰጡ ወገኖችም በርካታዎች ሲሆኑ ታይተዋል፡፡ በግሩም የአጨራረስ ብቃት ሁለት ጎሎችን በሳውዝ ሀምፕተን መረብ ላይ ለማሳረፍ መቻሉ ቫንሃል ትክክለኛውን ውጤታማ የአጥቂ መስመር ተጨዋችን ማግኘታቸውን ያረጋገጠላቸው ሆኗል፡፡
ማንችስተር ዩናይትድ በሴንት ሜሪ ስቴዲየም ሳውዝሀምፕተንን 3ለ2 በሆነ ውጤት ለማሸነፍ በቻለበት ግጥሚያ ከመረብ ያሳረፋቸው የመጀመሪያዎቹ ሁለት ግጥሚያዎች በስሙ ያስመዘገቧቸው ጎሎቹን ብዛት ሶት በማድረስ የኦልድ ትራፎርድ የፉትቦል ህይወቱን ባማረ ሁኔታ ለመጀመር ችሏል፡፡ ማርሻል ለማንችስተር ዩናይትድ ሶስቱን የፕሪሚየር ሊግ ጎሎችን ለማስቆጠር የፈጀበት ለ80 ደቂቃዎች ብቻ በሜዳ ላይ መቆየት ነው፡፡
በአንፃሩ ራዳሜል ፉልካኦ ባለፈው ሲዝን ሙሉ ሲዝንን ለማንችስተር ዩናይትድ በስሙ ያስመዘገባቸው ጎሎች ብዛት አራት ብቻ ናቸው፡፡ ይህ የሚያሳየው ሉዊ ቫንሃል ማንም ባልገመተው መልኩ የቡድናቸው ጎሎችን የማስቆጠር ችግርን ሙሉ ለሙሉ ለመቅረፍ ኃይል ያለው አስገራሚ ወጣትን ማግኘት መቻላቸውን ነው፡፡ ከዝውውሩ ወዲህ ማንችስተር ዩናይትድ ሊቨርፑልን 3ለ1፣ እንዲሁም ሳውዝሀምፕተንን 3ለ2 በረታበት ሁለት ተከታታይ የፕሪሚየር ሊግ ግጥሚያዎች ከመረብ ያሳረፋቸው ሁሉም ሶስት ጎሎች በግሩም የአጨራረስ ብቃት ከመረብ የተገናኙ በመሆናቸው በ19 ዓመቱ ፈረንሳዊው ኢንተርናሽናል አጥቂ ብቃት የፉትቦሉ አለም አግራሞቱን በመግለፅ ላይ ነው፡፡
በሴንት ሜሪ በተደረገው ግጥሚያ ሁን ማታ ያስቆጠራት ሌላኛዋ ጎል በሜዳ ላይ የነበሩት ሁሉም የማንቸስተር ዩናይትድ ተጨዋቾችን ባሳተፈ መልኩ በ45 ፓሶች በሜዳ ላይ የነበሩትን ሁሉንም የማንችስተር ዩናይትድ ተጨዋቾችን ባሳተፈ መልኩ ቢሆንም የሁሉም ታዋቂ የፉትቦል ተንታኞችን ልዩ ትኩረት የሳበው ግን አንቶኒ ማርሻል የወጣበት ውድ ዋጋ ምንም አይነት ተፅዕኖ ሳይፈጥርበትና በማንቸስተር ዩናይትድ የፊት አጥቂ መስመር መሰለፍ የሚፈጥረውን ከፍተኛ ጫናን በመቋቋም ከወዲሁ ሶስት የፕሪሚየር ሊግ ጎሎችን ከመረብ ለማሳረፍ መቻሉ ነው፡፡
በማርሻል ዙሪያ አስተያየታቸውን ከሰነዘሩት የፉትቦል ተንታኞች ውስጥ የቀድሞው የሊቨርፑል ዝነኛ ግርሃም ሶውነስ ‹‹ሰፊ ልምድን ከማጣቱ በስተቀር ሁሉንም አይነት ብቃቶችን አሟልቶ የያዘ አስገራሚ ወጣት ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ በተለይም ከፍተኛ ፍጥነቱና እውነተኛ የሆነ የሰውነት ጥንካሬን መላበሱ አስገራሚ ሆኖብኛል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ እስካሁን ለማንቸስተር ዩናይትድ በተሰለፈባቸው ሁለት ግጥሚያዎች ያደረጋቸው ሶስቱንም አላማቸውን የጠበቁ ጎል የማስቆጠር ሙከራዎችን ከመረብ ማሳረፉ ያማረ የጎል አጨራረስ ብቃትን መላበሱን የሚያሳይ ነው›› በማለት ፈረንሳዊው ወጣት አጥቂን አድንቆታል፡፡
የማንችስተር ዩናይትዱ የቀድሞ ዝነኛ አምበል ጋሪ ኔቭል በበኩሉ ‹‹ሉዊ ቫንሃል ለአንቶኒ ማርሻል ግዥ ውድ ዋጋ መክፈላቸው አስገራሚ ሆኖብኝ ነበር፡፡ ምክንያቱም በአንድ ሲዝን ሌላው ቀርቶ እስከ 15 የሚደርስ ጎልን ማስቆጠሩ አጠራጣሪ ሆኖብኝ ነበር፡፡ በተግባር ያየነው ግን ማርሻል ማንችስተር ዩናይትድን ብዛት ያላቸው ጎሎችን ለማሳፈስ የሚያስችለው ትክክለኛው የአጥቂ መስመር ተጨዋች መሆኑን ነው፡፡ ለዚህ አባባሌ አንዱ ምክንያት የሆነኝ ጎሎችን ካስቆጠረ በኋላ ደስታውን በተጋነነ መልኩ የመግለፅ ባህል የሌለው መሆኑ ነው፡፡ እንደዚህ አይነቱ ባህል ያላቸው ተጨዋቾች ብዙውን ጊዜ የራስ የመተማመን መንፈሳቸው እጅግ ያማረ ሲሆን መታየቱ የተለመደ ነው›› የሚል አስተያየቱን በመሰንዘር ሉዊ ቫንሃል ማርሻልን በዝውውር መስኮቱ መጨረሻ ቀን የገዙበት ተግባራቸውን አድንቆላቸዋል፡፡
(ይህ ስታትስቲክስ ከ3 ሳምንት በፊት የነበረና የትናንት ምሽቱን የቻምፒዪንስ ሊግ ጨዋታ አይመለከትም)
የአንቶኒዮ ማርሻል የእስካሁኑ የሲዝኑ የፕሪሚየር ሊግ የቁጥር መረጃዎች
80- በሜዳ ላይ የቆየባቸው የፕሪሚየር ሊግ ደቂቃዎች
4- ያደረጋቸው አጠቃላይ ጎል የማስቆጠር ሙከራዎች
3- አላማቸውን ያገኙለት የጎል ሙከራዎችና ያስቆጠራቸው የሊጉ ጎሎች
አንቶኒ ማርቫል በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በተሰለፈባቸው የመጀመሪያዎቹ ሁለት የሊጉ ግጥሚያዎች በእያንዳንዱ ላይ ጎልን በማስቆጠር ታሪክ ሶስተኛው የማን ዩናይትድ ተጨዋች ሆኗል፡፡ ሌሎቹ ሉዊስ ሳህና ፍሬዲሪኮ ሜኬዳ ናቸው፡፡
ማርሻል በእስካኑ ሲዝን ያስቆጠራቸው 3 የፕሪሚየር ሊግ ጎሎች የቼልሲዎቹ ኤደን ሃዛርድ፣ ዲያጎ ኮስታና ፔድሮ በድምሩ በስማቸው ካስመዘገቧቸው ጎሎች ብዛት ጋር እኩል ናቸው፡፡
The post Sport: አንቶኒ ማርሻል – አዲሱ የቀይ ሰይጣኖቹ አለኝታ appeared first on Zehabesha Amharic.