ፋሲል ከነማ (አጼዎቹ) ጎንደር ፋሲለደስ ኳስ-ሜዳ ላይ ከኢትዮጵያ መድን ጋር ያደረጉትን ጨዋታ 1ለ0 በማሸነፍ አራት ጨዋታዎች እየቀሯቸው ነበር ወደፕሪሚየር ሊግ መግባታቸውን ያረጋገጡት፡፡ ፋሲል ጅማ አባ ቡናን 3ለ1 በማሸነፍ ደግሞ የከፍተኛ ሊጉ ቁንጮ ሆነው በዋንጫ ደምድመዋል፡፡ ፋሲል ከነማ አመቱን ሙሉ በከፍተኛ ሕዝባዊ መነሳሳትና ድጋፍ ሲደገፍ እንደነበረ እናስታውሳለን፡፡ ቡድኑ ኢትዮጵያ ውስጥ በክለብ ፍቅር፣ ከሜዳ ውጭም አብሮ በመጓዝ በከፍተኛ የደጋፊ ቁጥር ከሚደገፉ እግር ኳስ ቡድኖች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ የእግር ኳስ ቡድኑ በሃገር ውስጥና ውጭ የደጋፊዎች “የፌስቡክ ገጽ” ቅስቀሳ በማድረግ፣ መረጃዎችን ፈጥኖ በማድረስና የግጥሚያ ላይ ቀጥታ (ትኩስ) መረጃዎችን በየደቂቃው በማድረስ ተምሳሌትነት እንደነበረው ማንሳት ይቻላል፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ ፈረንጆቹ 12ኛ ተጫዋች የሚሉት ደጋፊ ፋሲለደስ ላይ 12ኛና 13ኛ ሆኖ ተሰልፏል፡፡ የአንጋፋው ክለብ ደጋፊዎች ከተጫዋቾች ባልተናነሰ ተጫውተዋል፡፡ ቀይና ነጩን መለዮና የአንገት ፎጣ (ስካርፕ) በማድረግ ጎንደር ላይም ከጎንደር ውጭም ከቡድናቸው ጋር አብረው ተጉዘዋል፡፡ በጩኸታቸው የኢያሪኮን ግንብ እንደናጡት ቤተ አይሁድ፣ ፋሲሎችም በጩኸታቸው ተጋጣሚን በማርበድበድ፣ ተጫዋቾቹን በማነሳሳት ተአምር ሰርተዋል፡፡ ይሄ ሁነት የሚጨምር እንጂ የሚቀንስ እንደማይሆን ይጠበቃል፡፡ ከፋሲለደስ ከተማ ውጭ ያሉ ጎንደሬዎች፣ ከጎንደር ውጭም ያሉ አማራዎች ከአማራ ውጭም ያሉ ሌሎች ኳስ ወዳዶች በክለቡ ፍቅር ሲወድቁ እያየን ነውና፡፡
በመቀጠል ኳስን የማንነታቸው መገለጫ ያደረጉ ሃገራትን፣ በኳስ ቡድናቸው ማንነታቸውን ያወጁና የገለጹ ቡድኖችንና ማህበረሰቦችን፣ እና የኳስ ቡድኖችን ተያያዥ አለማቀፋዊ ታሪኮችን በማቅረብ የፋሲልን እውነታ በዚያ መለኪያነት ላቅርብ፡፡
** ኳስ እንደማንነት ማሳያ **
*ዓለም አቀፍ አውድ*
ማንነት የአንድን ተመሳሳይ ስነ ልቦናዊ ስሪት ያለው ሕዝብ ልዩ ልዩ እሴቶች ያቀፈ መገለጫ ነው፡፡ ማንነት የአንድ ማሕበረሰብ ማን እንደሆነ ማሳወቂያ፣ የእኔነቱ መገለጫ ነው፡፡ የማንነት ጽንሰሃሳብ ውስብስብና ገጸ-ብዙ ነው፡፡ ይህን ማንነት ግለሰቦች ከተለያዩ የባህል እሳቤዎች አንጻር በመቃኘት ይገልጹታል (Archetti, 1994)፡፡ እንደ Archetti ገለጻ የእግር ኳስ ቡድኖች ማንነትን በመሳል ረገድ ሁነኛ ማሳያዎች ናቸው፡፡
እግር ኳስ የማንነታቸው መለኪያ የሆኑ በርካታ ሃገራትና ማኅበረሰባት አሉ፡፡ ብራዚል ውስጥ ኳስ ሁነኛ የሃገሬው መገለጫ ነው፡፡ ኳስ ብራዚል ሃገር ከጨዋታነት የዘለለ ትርጉም አለው፤ሁሉ ነገራቸው ነው ማለት ይቀላል፡፡ የአያሌ ብራዚላውያን ህጻናት ህልም “ስመጥር ኳስ ተጫዋች መሆን” ነው፡፡ ብራዚል የእግርኳስ ቱሪዝም መዳረሻ ሃገር ናት፡፡ ውብ የባህር ዳርቻዎቿን ከውብ ቆነጃጅቷ በተጨማሪ ህጻናት አሸዋ ላይ ኳስ ሰያንቀረቅቡ ትመለከቱባቸዋላችሁ፡፡ በርካታ የዓለማችን ታላላቅ እግር ኳስ ቡድኖች መልማዮች የታዳጊዎች ፕሮጄክቶችንና የሊግ ውድድሮችን በመታደም የወደፊቱን የኳስ ንጉስ ህጻን ቀድሞ ለመቅለብ ወደብራዚል ይጎርፋሉ፡፡ የአውሮፓ ኃያላን ክለቦች የታዳጊ ማሰልጠኛዎችን ብራዚል ውስጥ ከፍተዋል፡፡ እናም ኳስ ለብራዚል ከዋነኛ የእድገት ምንጮቿ ውስጥ አንዱ ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ2007 ዓ.ም የወጣ መረጃ እንደሚጠቁመው በዓመት በአማካይ 100 ፕሮፌሽናል ተጫዋቾች በሽያጭ ከብራዚል ወደተለያዩ ክለቦች ያመራሉ፡፡ ከዚያም ረብጣ ዶላር ወደእናት ሃገር ይዘንባል፡፡ ኳስ ማንነት ነው- ብራዚል፡፡ ብሔራዊ መለዮም ነው፡፡
ፍራንሲስኮ ሪቻቲ `La Roma: Soccer and Identity in Rome` በሚለው መጣጥፉ የ20ኛው ክ/ዘ የሮም ታሪክ፣ ባህልና ማንነት ከዋናው ክለቧ ከኤ.ኤስ ሮማ ጋር እንደሚቆራኝ ይናገራል፡፡ የ“ሮማ” ቡድን በሮም ነዋሪ የለት-ተለት የህይወት እንቅስቃሴ ውስጥ ጉልህ ሚና ይጫወታል ይላል፡፡ 48 በመቶው የሮም ህዝብ ሮማን ይደግፋል፤ 12 በመቶው ደግሞ ሌላኛውን የሮም ከተማ ክለብ ላዚዮን ሲደግፍ ቀሪው ደግሞ ለኳስ ደንታቢስ ነው የሚለው ሪቻቲ ደንታቢሱም ቢሆን በቤተሰቡ፣ በጓደኛው አሊያም በስራባልደረባው በኩል ሮማ ሕይወቱ ውስጥ አይጠፋም ይላል፡፡ እናም ሮማ የሮም መለያ ነው፡፡
ቤል (1994)፣ እንደሚለን እግር ኳስ በተለይ ከ19ኛው ክ/ዘመን ማብቂያ ጀምሮ በብሪታንያ ቁልፍ የማንነት መገለጫ ሆኗል፡፡ ለምሳሌ የካርዲፍ ከነማ እግር ኳስ ቡድን ዋነኛ የዌልስ ብሔራዊ ማንነት መፍጠሪያ፣ ማቀጣጠያና መገንቢያ ተደርጎ ይወሰዳል- እንደ ጆንስ (2000) ጥናት፡፡ ጋሪ ሮጀርስና ጆይል ሩክውድ “Cardiff City Football Club as a Vehicle to Promote Welsh National Identity” በሚለው ጥናታቸው እንደሚያስረግጡት በብዙኃኑ የዌልስ ዜጋ ዘንድ ካርዲፍ ከነማ ማለት “ዌልሳዊነት” ማለት ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ከእንግሊዛዊ ማንነት የሚለዩበት ማኅበራዊ መለዮ ነው፡፡ ደጋፊዎች ይህን አባባል ያዘወትሩታል፡- “ከነማ (ካርዲፍ) ሲጫወት ስንመለከት ስለ ዌልስ እንዘምራለን” ይቀጥላሉ፡- “ባንዲራችን እንለብሳለን፤ እንግሊዛዊ ተቀናቃኞቻችንን በየሳምንቱ እንገጥማለን፤ ዌልሳዊ መሆናችንን እናፈቅራለን፤ ለዚህ ፍቅራችን ክለባችን ድምጽ ይሆነዋል፤ እናም ዌልሳዊነታችንን እንድናንጸባርቅ ይረዳናል”፡፡ አንዳንዶች “እንግሊዝ-ጠል ብሔርተኛ ተቋም” አድርገው አሉታዊ ምስል ሊያላብሱት ይሞክራሉ፡፡ በዚህ ረገድ ባሳለፍነው የአውሮፓ ዋንጫ ዌልሳዊው ጋሬት ቤል “እንግሊዛውያንን እንጠላቸዋለን” ብሌ የተናገረውንና ባንጻሩ እንግሊዛዊው ጃክ ዊልሼል ለቤል የሰነዘረውን የጥላቻ ጥላቻ መልስ ማስታወስ ይቻላል፡፡
መቀመጫው በሃገረ ዮርዳኖስ የሆነው አል ዊህዳድ የተባለው ክለብ የፍልስጤም ብሔርተኝነት ምልክት/መገለጫ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ በዘመነ አፓርታይድ ጥቁር ያልተካተተበት ብሔራዊ ብድን ደ/አፍሪቃ ያበጀች ሲሆን፤ ጥቁሮቹ በበኩላቸው የነጻነት ትግሉ አካል የሆነ በተለይ ከነጻነትም በኋላ ዊሊ ማንዴላ የምትመራው የስፖርት ቡድን ነበር፡፡ ግብጽ ሃገር ውስጥ እግር ኳስና ፖለቲካ የተሳሰሩ ናቸው፡፡ ለአብነት ያህል ዝነኛው ቡድብ አል አህሊ የግብጽ ሕዝብ መለያ ሆኖ ነው የሚታየው። አል አህሊ በግብጻውያን በራሳቸው የተመሠረተው የመጀመሪያው ክለብ ሲሆን የግብጽ ብሔራዊ መለያ ነው። የየቡድኖቹ ደጋፊዎች በአገሪቱ ፖለቲካ ላይ ትልቅ ሚና ያላቸው ሲሆን ስታዲዮሞችም ብሶትን ለመግለጽ አመቺ ቦታዎች ናቸው።
በስፔን እግር ኳስና ፖለቲካ የማይለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ በተለይ ደግሞ ዋና ዋናዎቹ ፕሮፌሽናል ቡድኖች ከተመሰረቱበት ከ19ኛው ክ/ዘመን መገባደጃ ወዲህ፡፡ ስፔናዊው አምባገነን ፍራንሲስኮ ፍራንኮ (1936-1975 እ.ኤ.አ) በ1950ዎቹ በዓለምአቀፉ መድረክ አዎንታዊ ገጽታን ለመገንባት እግር ኳስን እንደሁነኛ መሳሪያ ተገልግሎበታል፡፡ አዲሲቷንና ማዕከላዊቷን የተረጋጋች ስፔን በዓለም ለማስተዋወቅ ትልቁን የአገሪቷን ቡድን ሪያል ማድሪድን እንደመሳርያ ተጠቀመ፡፡ የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ በ1956 ሲጀመር፣ ማድሪድም ለአምስት ተከታታይ ጊዜ አሸናፊ ሆኖ በአውሮፓ ሲነግሥ፣ ጄኔራል ፍራንኮ የሎስ ብላንኮዎቹ መደበኛ ተመልካችና የቅርብ ደጋፊ በመሆን ረብጣ የፖለቲካ ትርፍ ሊሸምት ችሏል፡፡ ማድሪድም የስፔን ብሔራዊ ማንነት ማሳያና መለኪያ ሆኖ እስከ ዘመናችን ገሰገሰ፡፡ የማንነት ጥያቄን ፖለቲካ አላብሶ በእግር ኳስ ሜዳ በማንጸባረቅ ወደር እንደማይገኝለት የሚነገርለት የካታሎን ተገንጣዮች ተወካይ ባርሴሎና ከዚህ በተጻራሪ ቀጥሎ ይመጣል፡፡ የካታሎኒያ ብሔርተኝነት ማሳያው ባርሴሎና በፍራንኮ ፈላጭ ቆራጭ ዱላ ተደቁሷል፡፡ ቡድኑም የብሔርተኝነት ንቅናቄውና የጸረ-ፍራንኮ ትግል ዋነኛ ማዕከል ሆነ፡፡ በፍጹም ራሳቸውን ስፔናዊ አድርገው የማይቆጥሩት የካታሎን ተገንጣዮች ከስፔን የተለየ ማንነትን ለማራመድና ተገንጥለው ነጻ የካታሎን መንግስት ለመመስረት ያላቸውን ህልም ለማሳካት በባርሴሎና እግር ኳስ ቡድን በኩል ብዙ ተጉዘዋል፡፡ ባርሳም የዚህ ፖለቲካዊ ውዝግብ ትልቅ ባለድርሻና “ሲምቦል” ነው፡፡ በተለይ የሊጉ ጠንካራዎቹ ክለቦች የስፔን ብሔራዊ ማንነት ማሳያ ተደርጎ የሚወሰደው ሪያል ማድሪድና የመገንጠል ጥያቄ አንጋቢዋ ካታሎን ግዛት ተወካዩ ባርሴሎና ቡድኖች ሲጫወቱ (ኤል-ክላሲኮ)፣ ከ“ደርቢ” ጨዋታ ተቀናቃኝነት በላይ፣ ጦር የተማዘዙ ሁለት ሉዓላዊ ባላንጣ ሃገራት የሚያደርጉት ፍልሚ እስኪመስል ድረስ ከኳስ ጨዋታነቱ ይልቅ የፖለቲካ ድባቡ ያመዝናል፡፡
በስፔን የብሔራዊ አንድነት አቀንቃኞች አማካኝነት በካታሎኗ ባርሴሎና ከተማ እንደተመሰረተ የሚነገርለት ስፓኞል እግር ኳስ ቡድንም ከስሙ ጀምሮ በስፔን ብሔርተኝነት መንፈስ የተቃኘ የባርሴሎና ቡድን የከተማ ተቀናቃኝ ነው፡፡ ይህም በስፔን ያለ የኳስና ማንነት መስተጋብር ሌላ ማሳያ ነው፡፡ ሌላው የስፔን ላሊጋ ተሳታፊ ቡድን የባስክ ተገንጣዮቹ አትሌቲኮ ቢልባኦም በባርሴሎና አንጻር የሚቀመጥ ነው፡፡ እነዚህ የሁለት ነጻነት ጠያቂ ክፍላተ ሃገራት ካታሎኒያና ባስክ ክለቦች ባርሳና ቢልባኦ በማኅበረሰባቸው ዘንድ ከእግር ኳስ ቡድንም በላይ ስዕል ነው ያላቸው፤ እንደብሔራዊ ቡድንም ይቆጥሯቸዋል፡፡ ለዛም ነው “የስፔንን እግር ኳስ ከፖለቲካዋ ነጥሎ ማየት አይቻልም” የሚለው አባባል ግዘፍ የሚነሳው፡፡
*የእኛ አገር አውድ*
ብራድሊ (1995) እንደሚለው የእግርኳስ ደጋፊዎች የቡድናቸውን ድል በመመልከት ጉልህ የሆነ ስነልቦናው ርካታ ያገኛሉ፡፡ ደጋፊነት ከስፖርታዊ አውድ ውጭም በህብረተሰቡ የለትተለት ኑሮ ውስጥ ስፍራ አለው፡፡ ይህም ማኀበራዊ ድርጊቶች፣ ሚዲያ ሽፋኖች፣ መለዮዎችን በመልበስ፣ የክለባቸውን መዝሙር በመዘመር፣ ምልክቶችን በማድረግ ታሪካቸውንና የቀንከቀን እውነታዎቻቸውን በማንጸባረቅ ይገለጻል ይለናል፡፡
ወደሃገራችን ስንመጣ ስፖርት ዘርፈ ብዙ የማንነት መወከያ ሆኖ ሲያገለግል አይተናል፡፡ ሩጫ የብሔራዊ ማንነታችን መገለጫ ሲሆን፤ የክለብ እግር ኳስ ደግሞ የተለያዩ ቡድኖችን አላማ ማራመጃነት ሲውል ነበር፡፡ በተለይ በ1960ዎቹና 70ዎቹ የነበሩ የአዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ፣ አስመራ፣ ሻሼመኔ፣ ጎንደርና ጅማ ላይ የተቋቋሙ ህዝባዊ መሰረት ያላቸው ክለቦች የፖለቲካ ማንነት ማራመጃ ነበሩ፡፡ ገነነ መኩሪያ ኢህአፓና ስፖርት በተባለው ባለሁለት ቅጽ መጽሐፉ 60ዎቹ መጨረሻና 70ዎቹ መጀመሪያ ላይ የነበሩ የሊግ ክለቦች ዋነኛ የኢህአፓ አላማ ማቀንቀኛ እንደነበሩ ይናገራል፡፡ ህዝባዊነት ያላቸው እንደ “አንድነት”፣ “ቅዱስ ጊዮርጊስ”፣ “ቴዎድሮስ” እና “ምድር ባቡር” (ድሬዳዋ)፣ መሰል ክለቦች ኢሃፓን ደግፎ ደርግን መንቀፊያ ነበሩ፡፡ ኢህአፓም ከህቡዕነት ግዘፍ እስከመንሳት ድረስ በክለቦቹ ውስጥ እጇ ረዥም ነበር፡፡ የኢህአፓ አባላት የነበሩና ፖለቲካውን ከልባቸው የሚያንቀሳቅሱ ተጫዋቾች ነበሩባቸው፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዘመነ ወያኔም የደርግ ጊዜውን ያክል ጠንካራና የተደራጀ ባይሆንም አልፎ አልፎ ፖለቲካዊ ተቃውሞዎች በአዲስ አበባ ስታዲዮምና በትንሹ ደግሞ በክፍለ ሃገር የኳስ ትዕይንቶች ላይ (ባለፈው ዓመት የጎንደር ፋሲለደስ ስታዲዮም የ“ወልቃይት አማራ ነው” የማንነት ጥያቄና በአጸፋው አዲግራት ላይ የፋሲል ደጋፊዎች ላይ ነውጠኛ ደጋፊዎች የወሰዱት ጠብ-አጫሪ ርምጃ እንዳብነት ሊጠቀስ ይችላል) ሲንጸባረቅ ይስተዋላል፡፡ “ሳንፈልጋቸው 20 ዓመታቸው” የሚለውን የሚስማር ተራ ህብረ ዝማሬ በዚህ ረገድ ማውሳት ይቻላል፡፡
ዐማራና ስፖርት
በኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ የዐማራ ህዝብ ያለ ተወካይ ለረዥም ዓመታት መቆየቱ ይታወቃል፡፡ ደሴ ጥቁር አባይ በአንድ ወቅት ብቅ ብሎ ጠፋ፤ ወልድያ ከነማ በ2007 ዓ.ም የውድድር ዘመን ደርሶ ተመለሰ፡፡ አምና በ2008 ዓ.ም ወደዋናው ሊግ ለመግባት በተደረገው ውድድር በከፍተኛ ሊግ ከቀጠና አንድ ፋሲል ከነማና ወልድያ ከነማ ሁለቱንም ኮታዎች በመጠቅለል አላፊ ሆነዋል፡፡ በዚህም በ2009 የውድድር ዓመት ሁለት ቡድኖች ዐማራን ይወክላሉ፡፡ እነዚህ ሁለት ቡድኖች የዐማራ ብሔርተኝነት ማነቃቂ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የዚህን ህዝብ ከኳስ መድረክ ለዘመናት ርቆ መቆየት ገዢው መንግስት ይህንን ህዝብ ለማጥፋት ከሚያራምደው እኩይ አጀንዳ ጋር አመሳስለዋለሁ፡፡ በ25ዓመታት ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዐማራዎችን የፈጀው የደደቢቱ መንግስት፣ የዚህን ህዝብ የበላይነት ከሚቀለብስባቸው መንገዶች አንዱ ስፖርት እንደሆነ ከግምት የዘለለ እውነታ ነው፡፡ እንደኦሮምያ ለሩጫ አመቺ የሆነ የአየር ንብረትና መልክዓምድራዊ አቀማመጥ ዐማራ ውስጥ አለ፤ በተለይ ሸዋና ጎጃም አካባቢ፡፡ ከነዚህ አካባቢዎች የተገኙ ጎበዝ አትሌቶችንም ታዝበናል፡፡ አገር አቀፍ ውድድሮች ላይ ውጣ ውረዶችን ተሻግረው በውድድር ሲሳተፉ ከዚያም በጎ ውጤት ሲያስመዘግቡ አይተናል፡፡ በዓለም አቀፍ መድረክ ግን አናያቸውም፡፡ ለምን? መጠርጠር ጥሩ ነው፡፡ በርግጥ ከጫካ የወጣው ገዢ ቡድን የዐማራ ህዝብ ላይ ጫካ ውስጥ ሆኖ ካረቀቀው የቂም በቀል ፖሊሲ አንጻር ስንቃኘው ጥርጣሬው ውሃ ያነሳል፡፡ ሊደረግላቸው የሚገባውን ድጋፍና ክትትል ብንተወው እንኳ በግላቸው ጥረት መሰናክሉን አልፈው እንዲወዳደሩ በሩ ቢከፈትላቸው ከነ“ገብሬ” ያነሰ “ፐርፎርም” እንደማያደርጉ አምናለሁ፡፡ ከክልሉ በጥረት የወጡ አትሌቶች ዐማራ በመሆናቸው ምን ያክል እንደሚገለሉና እንደሚገፉ ከአትሌቶቹ ጋር በቅርበት ተወያይቶ ያጫወተኝ የስፖርት ጋዜጠኛ ወዳጄ ለዚህ እማኜ ነው፡፡ እግር ኳሱም ከዚህ የተለየ ዕጣ የለውም፡፡ ስፖርት አንድን ህዝብ ለማስተዋወቅና ጥሩ ገጽታ ለማጎናጸፍ መልካሙ መንገድ መሆኑ እሙን ነው፡፡ በተለይ የሊግ ኳስ ከላይ በዓለም ዐቀፍ አውድ እንዳየነው አንድን ማህበረሰብ፣ ዘውግ፣ ተመሳሳይ ስነ ልቦናዊ ስሪት ያለው ህዝብ፣ ከተማ የመወከልና የማስተዋወቅ እድሉ ከፍተኛ ስለሆነ ሴረኛው መንግስት በዚህ በኩልም ሲደቁሰን እንደኖረ እናምናለን፡፡ እነ ይድነቃቸው ተሰማና መንግስቱ ወርቁን የመሰሉ ብርቅ የአገራችንና የአፍሪካ የእግር ኳስ ምልክቶች የወጡበት ህዝብ ለምን ያለ ተወካይ ሊቀር ቻለ? እውነቱ ከጥያቄው መልስ ውስጥ አለ፡፡ አሁን ፋሲልና ወልድያ ከዚህ ፍቱን መጠይቅ ጀርባ ያለውን ደባ እየሸረሸሩ በስፖርቱ መድረክ ገነው፣ ህዝባቸውን ከጎናቸው በማሰለፍ ብሄርተኝነትን እያቀነቀኑ፣ ፖለቲካዊና ህዝባዊ ጥያቄዎች እየተስተጋቡባቸው ይቀጥላሉ፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዋነኛ ዓላማ ፋሲል ከነማን በዚህ ነጥብ ረገድ መዳሰስ ነውና ወደዚያው ልለፍ፡፡
የፋሲል ከተማ
ምንም እንኳን በዚህ ዓመት ወደስኬት ይምጣ እንጂ ፋሲል ብዙ አስርተ አመታት ያስቆጠረ ታሪክ አለው፡፡ ጠንካራ ህዝባዊ መሰረትም አለው፡፡ በተጫዋቾች ትጋት፣ በደጋፊው ደጀንነት፣ ዓመቱን በስኬት አጠናቋል፡፡ የፋሲል የአምና ጉዞ ከስፖርትነት ባለፈ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች የተስተናገዱበት ክዋኔ ነበረው፡፡ በዓለም መድረክ ላይ እንዳየነው እግር ኳስ የተለያዩ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሌሎች እሳቤዎችና ጥያቄዎች የሚስተናገዱበት መድረክ ነው፡፡ ፍቅርንም ጥላቻንም ማስተናገድ ይቻላል፡፡ በአንድ ወቅት የኢራን ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ የነበሩት አፍሺህን እግር ኳስ ህዝብን ለማስተሳሰር ያለውን ጉልበት ሲናገሩ “ዓለምን ወደአንድ ለማምጣት ሁለት ነገሮች ያስፈጋሉ- ፍቅርና እግር ኳስ” ብለው ነበር፡፡ ለዛም ነው በስፖርታዊ መድረኮች ህዝባዊ ጥያቄዎችን ማንሳት የተለመደ የሆነው፡፡
ዘንድሮ ፋሲል ወደፕሪሚየር ሊግ መግባቱን ተከትሎ ድጋፉ እንደሚግል ይጠበቃል፡፡ የተቀጣጠለው የዓማራ ብሔርተኝነትም ሆነ ህዝባዊና ፖለቲካዊ ጥያቄዎች በተደራጀ መልኩ ይቀርቡበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ፋሲል ከክለብም በላይ ነው፡፡ ከላይ ባርሴሎና ክለብ ብቻ አይደለም እንደተባለው፤ የማንነት መጠየቂያ መድረክም እንጂ፡፡ እናም ፋሲል የዓማራነት መወከያ ነው፤ የተገፋ ህዝብ ጋሻ፤ የተንቋሸሸ ታሪክና ማንነት መመለሻና ማደሻ፡፡ ይህ ዓማራዊ ማንነትና ብሶት በደጋፊዎቹ ይዘመራል፤ ፋሲል በደጋፊ መሰረት ላይ የታነጸ ክለብ ነውና፡፡ እንደኛ ሃገሩ ቡና እና እንደአውሮፓ ታላላቅ ቡድኖች የደጋፊ ልዩነት ፈጣሪነት ፋሲል ላይ ግዘፍ ይነሳል፡፡ ህዝባዊ እምቢተኝነትና ፋሲል ከነማ ጎን ለጎን የሚሄዱ ሁነቶች ናቸው፡፡ ፋሲል የጎንደር ክለብ ነው፤ ጎንደር- የዐማራ ተጋድሎ የተጠነሰሰባትና የተቀጣጠለባት ምድር ናት! በተዋህዶ የከበረች ምድር፤ አንድም በጀግንነት አንድም በጨዋነት- በተዋህዶ መክበር የምልህ ይሄንን ነው፡፡ ጀግንነት ብትል መፈጠሪያው ጎንደር፤ እንግዲያስ ጨዋነት (ማተብ ይልሃል! ሃቀኝነት- ሰው አክባሪነት፣ እንግዳ ወዳድነት፣ አዛኝነት)፡፡ ይሄንን እንግዲህ በኳሱ መድረክ አብረን የምናየው ይሆናል፡፡ ኳስ የበሬ ግንባር በምታክል ሜዳ ቅሪላ ከማንከባለል የዘለለ ነው የሚባለውም ለዛ ነው፡፡ የገሃዱ ዓለም እውነት ነው፡፡ ኳስ የዓለምን ቢዝነስ ይመራል፣ የዓለምን ፖለቲካ ይመራል፣ የዓለማችንን ሁሉ ነገር በቅጽበት መቀየር የሚችሉ አቋማሪዎችና ማፍያዎች ኳሱ ውስጥ አሉ፡፡
አሁን በዘመነ ደደቢት ዐማራነት በራሱ ፖለቲካ ሆኗል፡፡ ቀሪዋ ኢትዮጵያ በገዢዎች አምባገነናዊ ዱላ ስትመታ ዐማራ ግን ከዚህም ያልፍና በዘሩ ብቻ ደደቢት በርሃ ውስጥ በተነገፈለት የበቀል አጀንዳ ላለፉት 40 ዓመታት (በይበልጥ 25 ዓመታት) የሚገደል፣ የሚሳደድ፣ በድህነት ውስጥ ይኖር ዘንድ የተፈረደበት፣ በስነ ልቦና የሚመታ፣ ትምህርት/ጤና/መሰረተ ልማቶች የተነፈጉት፣ የሚሰደብ፣ የዘር ማጥፋት የታወጀበት ህዝብ ሆኗል፡፡ ይህም የሚሆነው ዐማራ ስለሆነ ብቻና ብቻ ነው፡፡ እናም የዐማራነት ጥያቄ የመኖር-አለመኖር ጥያቄ ነው፤ የህልውና ጥያቄ፡፡ ይህን ለመዋጋት የዐማራ ብሔርተኝነት ወሳኙ መንገድ ሲሆን ንቃተ ህሊና ደግሞ መንገዱን ይጠርጋል፡፡ ለዚህም መድረኮች ያስፈልጉናል፡፡ በማኅበራዊ ሚዲያው፣ በቡድን ውይይት፣ በመደራጀት፣ በ“አክቲቪዝም” እና ሌሎች መንገዶች ከሚደረገው የንቃተ ህሊና ማዳበሪያ መድረኮች በተጨማሪ ኳስ (ስፖርት) አንዱ ሆኖ ይቀርባል ማለት ነው፡፡ ይህን ንቃተ ህሊና የሚፈጠርበት፣ የሚሟሟቅበት፣ የሚዳብርበት መድረክ ይሆናል- ፋሲል ከነማ፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም በሁሉም መድረኮች ዐማራ ስም አጠራር እንዳይኖረው ላለፉት 25 ዓመታት እየተጋ ያለው ስርዓት ካቅሙ በላይ በሆነ ህዝባዊ መነሳሳትና ወኔ ፋሲል ፕሪሚየር ሊጉን መቀላቀሉ ደደቢቶቹን ውስጥ ውስጡን እርር ድብን እንዳደረጋቸው መገመት ቀላል ነው፡፡ በተለይ ፋሲልና ወልድያ የሰሜን ተወካዮችን ከስር ጥለው መምጣታቸው ንዴታቸውን ሊያንረው ይችላል፡፡ እናም እነዚህ የዐማራ ተወካዮች በመጡበት አግራቸው ተመልሰው እንዲወርዱ “ፕሮፌሽናል” ሴራ ሊያሴሩ ይችላሉ፤ ከዳኝነት እስከ ፌዴሬሽን ቢሮክራሲ፡፡ ስለሆነም ይህንን ጉዳይ ነቅቶ መከታተል ክለቦቹን ከመደገፍ ጋር ጎን ለጎን ትኩረት ሊቸረው የሚገባ አቢይ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ጽሑፍ/እይታ ፋሲል ከነማን ማዕከል አርጎ ይጻፍ እንጂ በተመሳሳይ ወልድያ ከነማንም ይወክላል፡፡ እነዚህ ሁለት ቡድኖች የዐማራ ብሔርተኝነት ማቀጣጠያ ሆነው ከዐማራነት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች የሚነሰሱባቸው መድረኮች ይሆኑ ዘንድ ይጠበቃል፡፡ ፋሲልና ወልድያ ማንነታችን ያነጥሩልናል፤ ታሪካችንን መልሰው፣ ውለታችንን አወራርደው፣ ወደሰገነታችን ያወጡናል፡፡ በሰላማዊው መድረክ ዐማራ ይነግሳል፡፡ ፋሲልና ወልድያ የዐማራ ባርሴሎናዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ይጠበቃል፡፡
ቸር ያሰማን!
ስኬት ለፋሲልና ወልድያ ከነማ!