Quantcast
Channel: ስፖርት | ዘ-ሐበሻ (ZeHabesha) - Latest Ethiopian News Provider
Viewing all articles
Browse latest Browse all 419

Sport |ኬቪን ደብሩኒ የሲቲዎች አዲሱ አለኝታ

$
0
0

 

ቤልጅየማዊው ኢንተርናሽል አማካዩ ኬቪን ደብሩኒ በቀድሞው ክለቡ ዎልስበርግ ቆይታው ያለፈው ሲዝንን ያጠናቀቀው በባየር ሙኒክ ስኳድ የሚገኙ በርካታ ወርልድ ክላስ ፉትቦለሮችን በመብለጥ የጀርመን ቡንደስሊጋ ውድድር ኮከብ ተጨዋች በመባል መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሆኖም ግን ከሁለት ዓመታት በፊት በቼልሲ ቆይታው ሌላው ቀርቶ የምዕራብ ለንደኑ ክለብ መደበኛ ቋሚ ተሰላፊ ለመሆን የሚያስችለውን አስተማማኝ ብቃትን ለመያዝ መቸገሩን ከግንዛቤ በማስገባት አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች የማንቸስተር ሲቲው አሰልጣኝ ማኑኤል ፔሌግሪኒ የ24 ዓመቱ ቤልጅየማዊ ኢንተርናሽልን በእጃቸው ያስገቡበት ውሳኔያቸው ፍሬያማ መሆን መቻሉን ተጠራጥረውት ነበር፡፡ በተለይም በበርካታዎች ዘንድ ከዚህ በፊት በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ተሳትፎው ስኬታማ ለመሆን አለመቻሉን ከግንዛቤ በማስገባት ማንችስተር ሲቲ በታሪኩ አቻ በማይገኝለት ከፍተኛ የግዢ ሂሳብን ማለትም 54 ሚሊዮን ፓውንድ ሂሳብ ለዎልስበርግ መክፈሉ ለደብሩኒ ብቃት የሚበዛበት ዋጋ ነው የሚል አመለካከታቸውን ሲገልፁ ተደምጠዋል፡፡

Manchester City v West Ham United - Premier League

ሆኖም ግን ደብሩኒ ለማንችስተር ሲቲ በእስካሁኑ ሲዝን በመስጠት ላይ ያለው ግልጋሎት እጅግ ከፍተኛ ሆኖ መገኘት ፔሌግሬኒ ያወጡበት ከፍተኛ የግዢ ሂሳብን በሜዳ ላይ ባለው ውጤታማ ፉትቦሉ በአግባቡ ለመክፈል እንደሚችል የጠቆመ ሆኗል፡፡ ይህንን በማመንም የባየር ሙኒኩ አሰልጣኝ ፔፔ ጋርዲዮላ በያዝነው ሳምንት ውስጥ በሰጠው መግለጫው ‹‹በአሁኑ ወቅት በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር በመሳተፍ ላይ ካሉት ተጨዋቾች በምርጥ ብቃቱ የቅድሚያው አድናቆት የምገልፅለት ተጨዋች ኬቪን ደብሩኒ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ለዎልስበርግ በተሰለፈባቸው 18 ወራት በሜዳ ላይ ሁሉንም አይነት ስኬታማ ተግባሮን በመፈፀም ሲያስገርመኝ ዘልቋል፡፡ ለማንችስተር ሲቲም በዘንድሮው ሲዝን ይህንን ውጤታማ ፉትቦሉን በተሟላ ሁኔታ ሲደግመው ማየቴ በደብሩኒ አስገራሚ ብቃቶች መገረሜን እንድቀጥል ምክንያት ሆኖኛል፡፡ በእኔ አመለካከትም የዘንድሮው ሲዝን ከጀመረበት ያማረ ታላቅ ፐርፎርንሱ አንፃር ለማንችስተር ሲቲ የተሰለፈበት የመጀመሪያውን ሲዝን የሚያጠናቅቀው በእንግሊዝ ፉትቦል ያሉትን ሁሉንም አይነት የኮከብ ተጨዋችነት ስያሜዎችን በማግኘት ይሆናል፡፡ ዎልስበርግ ደብሩኒን በመሸጡ ደግሞ ምትክ የማያገኝለት ቁልፍ ተጨዋቹን ለማጣት ተገድዷል፡፡ በዛኑ መጠን ግን የማንችስተር ሲቲው አሰልጣኝ ማኑኤል ፔሌግሬኒ እውነተኛ የማሸነፊያ መሳሪያቸውን በእጃቸው ለማስገባት ችለዋል፡፡›› ብሏል፡፡

በእርግጥም ደብሩኒ ከማንችስተር ሲቲ የጨዋታ ስታይል ጋር በፍጥነት በመዋሃድ ለአዲሱ ክለቡ በተሰለፈባቸው በእስካሁኑ ግጥሚያዎች 5 ወሳኝ ጎሎችን ከማስቆጠር አልፎ አራት የጎል አሲስቶችን በስሙ ማስመዝገቡ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር በሚገኙት ተጨዋቾች ምርጥ ብቃቱ አቻ የማይገኝለት በሚል በብዙዎች ዘንድ እንዲወደስ ምክንያት ሆኖታል፡፡

ደብሩኒ ከዚህ በፊት ለዎልስበርግ በአብዛኛው የሚሰለፈው የ10 ቁጥር ሚናን በመያዝ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ለማንችስተር ሲቲ ከፈረመ ወዲህ የተጫዋቹ ሁለገብ ብቃት ባለቤትነትን በመገንዘብ ቺሊያዊው አሰልጣኝ በተደራቢ አጥቂነት ብቻ ሳይሆን በግራና በቀኝ ክንፎች በኩልን በመጠቀም የቡድናቸው አጠቃላዩ የማጥቃት እንቅስቃሴን ከፍተኛ ኃይልን እንዲያስገኝለት ማድረጋቸው ይታወቃል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ማንችስተር ሲቲ በኢትሃድ ስቴዲየም የስፔኑ ኬቪያን 2ለ1 በሆነ ውጤት በረታበት የቻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ውስጥ በፊት አጥቂ ሚና ተጠቅመውበታል፡፡

kevin de brunye

ይህ ቡድናቸው ወሳኙ የማሸነፊያ ጎልን ለማግኘት ከፍተኛ ጥረትን በማድረግ ላይ ባለበት ወቅት በግጥሚያው ሂደት የፈፀሙት ታክቲካል ውሳኔያቸው ፍሬያማ ሆኖላቸውም ደብሩኒ የማንችስተር ሲቲ የዘንድሮ ሲዝን የቻምፒዮንስ ሊግ ዘመቻ ወደ ትክክለኛው መስመር ያስገባላቸውን ወሳኙ የማሸነፊያ ጎልን በመጨረሻው ደቂቃ ላይ ከመረብ ለማሳረፍ ችሏል፡፡ በዚህም በማንችስተር ሲቲ ስኳድ የሚገኙት ተጨዋቾን የቡድናቸው የዘንድሮ ሲዝን አጠቃላዩ ዘመቻ የሚወሰነው ከኬቪን ደብሩኒ ጥሩ ብቃት ጋር በተያያዘ ምክንያት እስከማለት በመድረስ ላይ ናቸው፡፡ ይህንን እምነትን በማሳደር በተለይም እንግሊዛዊያን የቡድኑ ግብ ጠባቂ ጆ ሀርት በሰጠው መግለጫው ኬቪን ደብሩኒን ‹‹የቡድናችን የስኬት መሳሪያ›› በማለት ገልፆታል፡፡ ማንችስተር ሲቲ በአሁኑ ወቅት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የደረጃ ሰንጠረዥ ዋነኛ ተቀናቃኙ አርሰናልን በጎል ክፍያ በልጦ በመሪነት ስፍራ ላይ ለመቀመጥ እንዲችልና ከእስካሁኑ ሶስት የቻምፒዮንስ ሊግ ምድብ ማጣሪያ ግጥሚያዎቹ ሁለቱን ድል እንዲቀናው ግንባር ቀደሙን አስተዋፅኦን ካበረከቱለት ተጨዋች ግንባር ቀደሙ ደብሩኒ መሆኑን በማመን ሀርት አስተያየቱን ሲቀጥል፡- ‹‹… በእኔ አመለካከት ኬቨን ደብሩኒ ከክለባችንም አልፎ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር የእስካሁኑ እጅግ ምርጡ ተጨዋች ለመሆኑ አጠራጣሪ አይደለም፡፡ በእርግጥ ስኳዳችን ሌሎችንም በርካታ ብቃታቸው አስተማማኝ የሆኑ ተጨዋቾችን ይዟል፡፡ በተለይም ሌሎቹ አዲስ ፈራሚዎችን ከሆኑት ውስጥ ራሂም ስተርሊንግና ኒኮላስ አታሜንዴ ለቡድናችን የጨዋታ ስታይል ጋር በፍጥነት ለመዋሃድ ችለው የቡድናችንን ጥንካሬን ወደ ትልቅ ደረጃ ለማሸጋገር የቻሉበት አስተዋፅኦን እያከረክቱልን ይገኛሉ፡፡ ከሁሉም ግን ኬቨን ደብሩኒ እጅግ የተለየ አይነት ተጨዋች ሆኖብኛል፡፡ በእያንዳንዱ ግጥሚያዎች ለቡድናችን ከፍተኛ ወሳኝነት ያለው ጎልን በማስቆጠር ወይም ወሳኝ የጎል አሲስትን በስሙ በማስመዝገብ ማሳለፉን የተለመደ ባህሉ ማድረጉ በከፍተኛ ደረጃ እንድገረምበት ምክንያት ሆኖኛል፡፡ ባለፈው ሲዝን የጀርመን ቡንደስሊጋ ውድድር ኮከብ ተጨዋችነት ስያሜን ማግኘቱን ባወቅም የያዘው ብቃት ግን እንደ አሁኑ ሁሉ ፍፁም እንከን የማይወጣለት ይሆናል በሚል ግምት ግን በጭራሽ እንዳልነበረኝ ከማመን አልቆጠብም›› በማለት ተናግሯል፡፡

ከማንችስተር ሲቲ ቁልፍ ተጨዋቾች ውስጥ አንዱ ሆኖ የዘንድሮውን ሲዝንን የጀመረው እንግሊዛዊው ግብ ጠባቂ በሌሎች ጉዳዮችም ዙሪያ አስተያየቱን ሰሞኑን ሰጥቷል፡፡ በተለይም በግሉ በያዘው ባህሪን በማስመልከት ለቀረበለት ጥያቄ ምላሹን የሰጠው ‹‹…የተሰጠኝን ኃላፊነት በአግባቡ ለመፈፀም ሁሉንም አይነት ከፍተኛ ጥረቶችን የማደርግበት ባህሪ እንዳለኝ አምናለሁ፡፡ ይህ ባህሪዬ በሜዳ ላይ ላለው ፉትቦሌ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በህይወቴ በማደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ላይ ጭምር ሲደገም መታየቱ የተለመደ መሆኑን እኔን በቅርበት የሚያውቁኝ ሰዎች ምስክርነታቸውን ይሰጡኛል፡፡ ለእያንዳንዱ ግጥሚያዎች አስቀድሜ ከፍተኛ ትኩረትን በመስጠት በተጠናከረ ሁኔታ ልምምድን በመስራት ባህል አለኝ፡፡ ለምሳሌ ባለፈው ሰሞን የስፔኑ ኬቪያን ባስተናገድንበት የቻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያ ከፍተኛ ወሳኝነት ያለውን ድልን ለመቀዳጀት ችለናል፡፡ ሆኖም ግን እኔ በድሉ ከመኩራራት ይልቅ በሳምንቱ መጨረሻ ከማንችስተር ዩናይትድ ጋር ለማናደርገው ግጥሚያ በሙሉ ትኩረትን መስጠት የጀመርኩት ሐሙስ ጠዋት ከእንቅልፌ ስነቃ አንስቶ ነው›› በማለት ነው፡፡

Kevin and sterling

ሀርት በዚሁ መግለጫው ላይ ቡድናቸው የዘንድሮው ሲዝን አጀማመሩን በመዳሰስ አስተያየቱን የሰነዘረው ‹‹የዛሬ ዓመት ከነበረን አጀማመር አንፃር የዘንድሮው ሲዝን አጀማመራችን በመልካም ጎኑ ሊጠቀስ የሚገባው ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ይህንን ስል ግን በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የደረጃ ሰንጠረዥ አናት በአሁኑ ወቅት ያለን አቀማመጥ በሰፊው ሲዝን የሚፈጠረው ሁኔታን የመወሰን ኃይል እንደማይኖረው በማመን ነው፡፡ በእኔ አመለካከትም የዘንድሮ የፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮንነት ፉክክር እስከመጨረሻው ጥቂት ሳምንታት ድረስ የተካረረ ፉክክር የሚያስተናግድበት ይሆናል፡፡ ይህንን ለመቋቋም የምንችለው ደግሞ ከሃያላን ክለቦች ጋር ለምናደርጋቸው ግጥሚያዎች ብቻ ሳይሆን በሊጉ ከሚገኙት እያንዳንዱ ክለቦች ጋር የሚጠብቀን ግጥሚያዎችን በሙሉ ትኩረትን በመስጠት ወደ ሜዳ ለመግባት ስንችል መሆኑን አምናለሁ፡፡ ለምሳሌ የእሁዱ የማንቸስተር ደርቢን የጀመርነው ከፍተኛ የሆነ ትኩረት ሳይለየን ነው፡፡ ይህንን በቀጣይ የሊጉ ግጥሚያዎችም በተሟላ ሁኔታ የመድገም ኃላፊነት አለብን፡፡ ይህንን በአግባቡ ለመፈፀም ስንችል በቀጣዮቹ አምስትና ስድስት ወራት የሚጠብቀን የተጠናከረ ፉክክርን በመቋቋም ማንቸስተር ሲቲን ከሁለት ዓመታት በኋላ ደግሞ ከእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮንነት ክብር የማገናኘት አላማችንን በአግባቡ ለመፈፀም እንችላለን›› በማለት ነው፡፡

ሀርት በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር መሳተፍ የጀመረው ገና የ19 ዓመት ወጣት እያለ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ዕድሜው 28 በመድረሱ በዛ ጊዜ ከነበረው አንፃር በአሁኑ ወቅት የተሟላ ብቃት ያለው ግብ ጠባቂ መሆን መቻሉን በማመን በመቀጠልም አስተያየቱን የሰነዘረው ‹‹የግብ ጠባቂዎች ብቃት የሚለካው የሚቃጣባቸው የጎል ማስቆጠር ሙከራዎችን ለማዳን ተሰጥኦአቸው አኳያ ብቻ መሆን የለበትም፡፡ ግብ ጠባቂዎች ከኋላ ሆነው በሚያስተላልፉት መመሪያቸው የቡድናቸው የተከላካይ መስመርን የማደራጀትና የማነቃቃት ኃላፊነት ጭምር አለባቸው፡፡ ይህንን ኃላፊነትን ከአንዱ ዓመት ወደ ሌላው በተሸጋገርኩ ቁጥር ያሳደኩት ተሰጥኦም ከኋላ ሆኜ ለቡድናችን በምሰጠው መመሪያዎች እንዲነቃቁ የማስቻል ተሰጥኦን ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ዕድሜዬ እያደገ ሲሄድ አጠቃላዩ የግጥሚያችን እንቅስቃሴን በአግባቡ የማነብበት ብቃቴም በማዳኑ ለእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድንና ለማንችስተር ሲቲ በምሰለፍባቸው ግጥሚያዎች ላይ በፊቴ ከሚገኙት የተከላካይ መስመር ተጨዋቾች ጋር የበለጠ ባማረ ሁኔታ የመግባባት ደረጃዬ ሊያድግልኝ ችሏል ለማለት እችላለሁ›› ብሏል፡፡ የማንችስተር ሲቲው ቁጥር አንድ በአሁኑ ወቅት የዓለም ፉትቦል ከሚገኙት ግብ ጠባቂዎች በምርጥ ብቃታቸው ሶስቱን እንዲጠቅስ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሹን የሰጠው የባየር ሙኒኩ ማኑኤል ኢዬር፣ የማንቸስተር ዩናይትዱ ዳቪድ ዳሂአና የጁቬንቱሱ ጂያን ሉዊስ ቡፎንን የመጀመሪያዎቹ ሶስቱ ምርጥ ግብ ጠባቂዎች በማድረግ ነው፡፡

The post Sport | ኬቪን ደብሩኒ የሲቲዎች አዲሱ አለኝታ appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 419

Trending Articles