የትናንት ምሽቱን የቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ ሳይጨምር ለአራት ጊዜው የዓለም ኮከቡ ሊዮኔል ሜሲ የዘንድሮ ሲዝን በመልካም ጎኑ የሚጠቀስለት አይደለም ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ምክንያቱም ከጥቂት ሳምንታት በፊት በደረሰበት ጉዳት ሳቢያ ከሜዳ ለመራቅ ከመገደዱም አልፎ በጥሩ ጤንነት ሆኖ ግጥሚያዎችን የሚያደርግበት ጊዜ መች እንደሚሆን እርግጠኛ ሆኖ የማያውቀው ነገር የለውም፡፡ የ28 ዓመቱ አርጀንቲናዊ ኢንተርናሽል በአሁኑ ወቅት ከጉዳቱ ለማገገም በተጠናከረ ሁኔታ ጥረትን በማድረግ ላይ ባለበት ሁኔታ ስሙን ከእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ሃያላን ክለቦች ዝውውር ጋር በስፋት የሚያያዙት ዘገባዎች በማቅረብ ላይ ናቸው፡፡
ከዚህ በፊትም የሜሲ ስም ቼልሲ፣ ማንችስተር ሲቲና ማንችስተር ዩናይትድን ከመሳሰሉት የእንግሊዝ ሃያላን ክለቦች ዝውውር ጭምጭምታ ጋር አብሮ መነሳቱ የተለመደ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሆኖም ግን በዚህ ጉዳይ ዙሪያ የእስካሁኑ የፉትቦል ህይወቱን በባርሴሎና ማሊያ ያሳለፈው ሜሲ አስተያየቱን ከመስጠት ተቆጥቦ መዝለቁ ይታወቃል፡፡ በያዝነው ሳምንት ውስጥ ከያሆ ስፖርት ድረገፅ ጋር ባደረገው ሰፊ ቃል ምልልሱ ግን ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህ ጉዳይ ዙሪያ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ ‹‹ወደፊት ከስፔን ውጪ በሌላ ሀገር ትልቅ የሊግ ውድድር የመሳተፍ ፍላጎት ይኖርሃል›› በሚል ለቀረበለት ጥያቄ ሜሲ ምላሹን የሰጠው ‹‹ወደፊት ስለሚፈጠረው ጉዳይ አስቀድሜ የማስብ ባህል የለኝም፡፡ ምክንያቱም ሁልጊዜም የምኖረውና የማስበው የአሁኑ ህይወቴን ብቻ ነው፡፡ የማውቀው ለበርካታ ዓመታት ከባርሴሎና ባለመለየት ያማረ ህይወትን አሳልፌያለሁ፡፡ በአሁኑ ወቅት በባርሴሎና ባለኝ የተረጋጋ ህይወት ሙሉ ለሙሉ ደስተኛ ነኝ ከሁለት ልጆና ከአጠቃላዩ ቤተሰቦቼ ጋር በአሁኑ ወቅት አስደሳች ህይወትን በመኖር ላይ ነኝ፡፡ ተስፋ የማደርገውም ይህ ሁኔታ ተጠናክሮ ይቀጥልልኝ ብዬ ነው፡፡››
ይህንን የሜሲ መግለጫን ተከትሎም የባርሴሎናው ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ማሪያ ባርቶሚ በሰነዘሩት አስተያየት የቡድናቸው ቁልፍ ተጨዋች ‹‹በየጊዜው ስሙ ከተለያዩ ሃያላን ክለቦች ዝውውር ጭምጭምታዎች ጋር ሲያያዝ መስማት በከፍተኛ ደረጃ የሚያሰለች ሆኖብኛል›› የሚል መግለጫቸውን ሰጥተዋል፡፡ በተለይም ባለፈው ሳምንት ውስጥ አብዛኛዎቹ የስፔን ሚዲያዎች ሊዮኔል ሜሲ በጉልበቱ ላይ ከደረሰበት ጉዳት ለማገገም እያደረገው ከሚገኘው ጥረት በተጓዳኝ ባርሴሎናን በዘንድሮ ሲዝን መጠናቀቅ በኋላ የመልቀቅ ሃሳቡን ከመያዝም አልፎ ቀጣዩ ክለቡ ማን መሆን አለበት የሚለውን ጉዳይ ልዩ ትኩረትን ሰጥቶበት በማመዛዘን ላይ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር የመሳተፍ ፍላጎቱ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ እያደገ ሄዷል በሚል የቀረበው ዘገባ ለባርሴሎናው ፕሬዝዳንት የሚያበሳጭ ሆኖባቸዋል፡፡
ባርቶሜ በአንርጀንቲናዊው ኮከብ ዙሪያ እንደዚሁም አይነቱ ጭምጭምታዎች መሰማታቸውን የሚጠሉበት ዋነኛ ምክንያቶች ውስጥ አንዱ የጭምጭምታዎቹ መሰማት ከጉዳቱ በማገገም ጥረቱ ሙሉ ትኩረትን ከመስጠት እንዲቆጠብ የበኩሉን ስነ ልቦናዊ መረበሽን ይፈጥርበታል በሚል ስጋት ስላላቸው መሆኑን ከመጠቆምም አልተቆጠቡም፡፡
ባርቶሜ በጉዳዩ ዙሪያ በያዝነው ሳምንት ኤይቲ ቲቪ ለተባለው ቻናል መግለጫቸውን የሰጡት ‹‹ሊዮኔል ሜሲ ባርሴሎናን የመልቀቅ ፍላጎት ይኖረዋል ብለው የሚያስቡት ሰዎች ራሳቸውን ላልተፈለገ የግራ መጋባት መንፈስ ያጋለጡት ብቻ ናቸው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ምክንያቱም ራሱ ሜሲ ብቻ ሳይሆን ወላጅ አባቱ በተደጋጋሚ የሚናገሩት ባርሴሎናን የመልቀቅ ሃሳብ በጭራሽ ሊኖረው እንደማይችል ነው፡፡ ከባርሴሎና ጋር ያለው ወዳጅነት እንዳለፉት በርካታ ዓመታት ሁሉ እጅግ ያማረና የተዋበ ሆኖ ዘልቋል፡፡ ከሜሲ ባሻገር የቤተሰቡ አባላት በጠቅላላ ከክለባችን ጋር እርስ በርስ የተዛመዱ ናቸው ለማለት እችላለሁ፡፡ በአሁኑ ወቅት ከባርሴሎና ጋር ያለው ኮንትራት የሚጠናቀቀው ከሶስት ዓመታት በኋላ ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው ለሜሲ አዲስ ኮንትራት ለመፍቀድ የምንጣደፍበት ምንም አይነት ምክንያት አይኖረንም፡፡
በአሁኑ ወቅት ግን በታክስ ጉዳይ ከስፔን መንግሥት የተነሳበትን ጥያቄ መሰረት በማድረግ ብቻ ተጨባጭነት የሌላቸው ዘገባዎች እየቀረቡበት መሆኑ የክለባችን አባላት የሚያበሳጭ ሆኖብናል፡፡ ምክንያቱም እንደዚህ አይነቱ ከሃቅ የራቀ ጭምጭምታ ከደረሰበት ጉዳት ለማገገም በሚያደርገው ጥረት ላይ ሙሉ ትኩረት እንዳይኖረው የሃሳብ መበታተን ችግር እንዳይፈጥርበት ስጋትን ያሳደረብን ሆኖናል›› በማለት ነው፡፡
የባርሴሎናው ፕሬዝዳንት በዚሁ መግለጫው ላይ በሌላው የቡድናቸው ተጨዋች ማለትም ብራዚላዊው ኢንተርናሽል ኔይማር ኮንትራት ሁኔታ ዙሪያ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሻቸውን የሰጡት ‹‹የኔይማር ጉዳይ ከሜሲ አንፃር በብዙ መልኩ የተለየ በመሆኑ በዘንድሮው ዓመት አዲስ የኮንትራት ማራዘሚያ ውልን ልናቀርብለት አቅደናል፡፡ አስቀድመን ለኔይማር ቃል በገባንለት መሰረት ከወዲሁ የኮንትራት ማራዘሚያ ድርድሩ የመጀመሪያው ምዕራፍ ተግባራዊ በመሆን ላይ ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው የኔይማር ተጨመሪ በርካታ ዓመታት ከክለባችን መሰለፍን እንዲቀጥል ከፍተኛ ጉጉትን አሳድረን መዝለቃችንን ነው፡፡ ምክንያቱም በአሁኑ ወቅት ከቡድናችን እጅግ ቁልፍ ተጨዋቾች ውስጥ መሆኑን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከያዘው አጠቃላይ አስተማማኝ አቋሙ በቀላል ለመረዳት የምንቸገር አይሆንም በማለት ነው፡፡
‹‹በእርግጥ ኔይማር በቅርብ ሳምንታት ወዲህ ባርሴሎና በተከታታይ ግጥሚያዎች ድልን ለማስመዝገብ እንዲችል ከፍተኛ አስተዋፅኦን እያበረከተለት ይገኛል፡፡ የቀድሞው የሳንቶ ክለብ ስታር ባለፉት ዓመት የባርሴሎና ግጥሚያዎቹ አምስት ጎሎችን በስሙ ለማስመዝገብ መቻሉ ለዚህ በቂ ማስረጃ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ባለፉት ስድስት የባርሴሎና የሁሉም ውድድሮች ግጥሚያዎች ላይ በአጠቃላይ 5 የጎል አሲስቶችን በስሙ ለማስመዝገብ ችሏል፡፡ ይህ የሚያሳየው ሊዮኔል ሜሲ በጉዳት ከሜዳ ከራቀ ወዲህ ለባርሴሎና ውጤታማ ተግባርን በመፈፀም የ23 ዓመቱ ብራዚላዊው ኢንተርናሽናል ግንባር ቀደሙ ስፍራን ለመያዝ መቻሉን ነው፡፡ ከኔይማር ባሻገር ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ባርሴሎና አይበርን 3ለ1 በፈታበት የስፓኒሽ ላሊጋ ግጥሚያው ሀትሪክ የሰራው ኡራጓዊው አጥቂ ሉዊስ ስዋሬዝ በጥሩ አቋም መገኘት የካታላያኑ ክለብ ደጋፊዎች የሜሲ ጉዳት ከሜዳ መራቅ በቡድናቸው ውጤታማነት ላይ ያስከተለው ያንን ያህል ጎልቶ የሚጠቀስ ችግር አለመኖሩን እንዲገነዘቡት የረዳቸው ቢሆንም የአብዛኛዎቹ የባርሴሎና ደጋፊዎች ከፍተኛ ጉጉት ግን ቡድናቸው በቀጣዩ ወር ከሪያል ማድሪድ ጋር ለሚያደርገው የዘንድሮ ሲዝን የመጀመሪያው ኤልክላሲኮ ፍልሚያ የሜሲ በጥሩ ጤንነት ሆኖ መድረስ መቻልን ማየት ነው፡፡ ሜሲ በሰሞኑ ቃለ ምልልሱ ግን ከጉዳቱ አገግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚሰለፍበት ግጥሚያ የትኛው እንደሚሆን ለመገመት መቸገሩን ተናግሯል፡፡ በአሁኑ ወቅት ቲያጎና ማቲዬ የሚል መጠሪያ ያላቸው ሁለት ልጆችን ያፈራው ሜሲን በቃለ ምልልሱ ላይ ከተነሱለት ጥያቄዎች ውስጥ አንዱ ሁለት ልጆች አባት መሆኑ በሜዳ ላይ ላለው ፉትቦሉ ዙሪያ ያስከተለበት ለውጥ አለ የሚለው ይገኝበታል፡፡ ለጥያቄው ምላሹን የሰጠው እንደማንኛውም አባት ሁሉ ልጆቼን የማሳድግበት ተጨማሪ ኃላፊነት ያሸከመኝ ሆኗል፡፡ ይህ ግን በሜዳ ላይ ላለው ፉትቦሌ እንደወትሮው ሁሉ የማደርገው ሙሉ ትኩረትን የቀነሰብኝ አልሆነም›› በማለት ነው፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጨዋታው ሚና ስለመቀየሩና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ላደረገው ቃለ ምልልስ ይህንን ይመስላል፡፡
ጥያቄ፡-ስለ አሁኑ የጨዋታ ሚናህ ምን አስተያየት አለህ?
መልስ፡- በእያንዳንዱ ግጥሚያዎች ከቡድናችን ከፍተኛ ጠቀሜታን ለማስገኘት ይችላል ብለን ባመንበት መልኩ የጨዋታ እንቅስቃሴዎችን የማድረግ ባህል አለን፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ ጊዜ ወደ ኋላ ተመልሼ ኳስ የማዘጋጀት ተግባርን የምፈፅምበት እንዲሁም ጎሎችን በማስቆጥርበት ቦታ ላይ የመገኘት ኃላፊነቱን የምፈፅምበት አጋጣሚዎችም አሉኝ፡፡ እንደዚህ አይነቱ በበርካታ ተግባሮች ላይ በመሳተፍ የጨዋታ እንቅስቃሴን ማድረግ የባርሴሎና የተለመደ ባህል በመሆኑ አዲስ ተቀይሯል የምለው የጨዋታ ስታይል ለውጥ ያንን ያህል የለም ለማለት እደፍራለሁ፡፡
ጥያቄ፡- ክርስቲያኖ ሮናልዶ በሚጫወትበት የእግርኳስ ትውድል አብረህ መጫወት ላይ መሆንህ ችሎታህን ወደ ትልቅ ደረጃ ለማሸጋገር እንድትችል ያደረገልህ ድጋፍ አለ?
መልስ፡- እንደዚህ አይነት አመለካከት በሰዎች ዘንድ መኖሩ ያስገርመኛል፡፡ ምክንያቱም እኔ በግሌ ራሴን ከክርስቲያኖ ሮንልዶ ጋር ፉክክርን በማድረግ ላይ ነኝ በሚል የቆጠርኩበት ወቅት የለኝም፡፡ በእኔ ግምትም እሱም (ክርስቲያኖ ሮናልዶን) ከእኔ ጋር ፉክክር በማድረግ ላይ ነኝ የሚል አመለካከትን መያዙን እጠራጠራለሁ፡፡ የእኔ ሙሉ ትኩረት ለምሰለፍበት ቡድን ውጤታማነት በተቻለኝ አቅም ሁሉ ጥረትን ማድረግ መቻል ነው፡፡ እንደዚህ አይነቱ መንፈሴን ወደፊትም ቢሆን ልቀይረው እንደማልሻ ለማረጋገጥ እወዳለሁ፡፡
ጥያቄ፡- ከአገርህ ብሔራዊ ቡድን ጋር ያለህ ግንኙነት ምን ይመስላል? ሰዎች እንደሚናገሩት ሁሉ በበርካታ ውጣ ውረዶች የተሞላ ነው?
መልስ፡- አጀርንቲናዊያን በአብዛኛው ከፍተኛ የሆነ የእግርኳስ ፍቅር ያላቸው በመሆናቸው የአገራችንን ብሔራዊ ቡድንን በትልቅ ኢንተርናሽናል ውድድር ደረጃ በመወከል ለምንጫወተው ተጨዋቾች ከፍተኛ የሆነ ክብርን የሚሰጡበት አመለካከትን ተላብሰዋል ለማለት እችላለሁ፡፡ በዚሁ መልኩ ግን በጣም ጥቂቶች ለአገራችን ብራዊ ቡድን ስኬታማነት በሜዳ ላይ የተቻለንን ሁሉ ጥረትን በምናደርግበት ወቅት ጩኸትን በማሰማት ሊሰድቡን የሚሞክሩ አሉ፡፡ሆኖም ግን እኔ በግሌ ሁሌም የአገራችንን የፉትቦል አፍቃሪዎች በእኩል አይን የመመልከት ባህል አለኝ፡፡
ጥያቄ፡- በአመጋገብ ስርዓትህ ላይ መጠነኛ ለውጥን አምጥተሃል ስለሚባለው ነገር የምትነግረን ይኖርሃል?
መልስ፡- ጠንካራ ሰውነት እንዲኖረኝ ምንም አይነት ጠቀሜታን የማይሰጡን አንዳንድ የምግብ አይነቶችን ከመቀነስ በስተቀር በአመጋገብ ስርዓቴ ላይ ያመጣሁት አጠቃላይ ለውጥ የለም፡፡ ከሌሎች ፕሮፌሽናል ፉትቦለሮች በዚህ ጉዳይ እለያለሁ የሚል እምነት የለኝም፡፡
ጥያቄ፡- በሌላ አገር የሊግ ውድድር ለመሳተፍ የምትችልበት አጋጣሚ ይኖርሃል?
መልስ፡- ወደፊት ስለሚፈጠረው ነገር ከወዲሁ አስቀድሜ በማሰብ አስተያየቴን ለመስጠት አልሻም፡፡ የምኖረውና የማስበው በአሁኑ ወቅት ስላለኝ ህይወት ብቻ ነው፡፡ ይህ በመሆኑም በአሁኑ ወቅት በስፓኒሽ ላ ሊጋ ውድድር ተሳትፎና በባርሴሎና ክለብ መገኘቴን ብቻ ነው የማውቀው፡፡ የማስበው በቅር ስለሚፈጠሩ አውነታዎች ብቻ መሆኑን በድጋ ለማረጋገጥ እወዳለሁ፡፡
ጥያቄ፡- ከዚህ በፊት የግል ህይወትህን የያዘው መፅሐፍን ማንበብህን መጀመርህ ተነግሮን ነበር፤ አሁንስ መፅሐፍን አንበብህ ጨርሰኸዋል?
መልስ፡- ስለ እውነቱ ለመናገር መፅሐፉን አንብቤ አልጨረስኩትም፡፡ ምክንያቱም ባለፈው ታሪክም ሆነ ወደፊት ከበርካታ ዓመታት በኋላ ስለሚፈጠረው ነገር ማሰብን አልወድም፡፡
ጥያቄ፡- በሜዳ ላይ በምታደርገው ፉትቦልን ይበልጥ እንዲደሰት የምትጓጓው እነማን ነው የምትሰለፍበት ቡድን ደጋፊዎችን ወይስ ቤተሰቦችህን?
መልስ፡- ወደ ሜዳ የምገባው በውጤታማ ፉትቦሌ የማስደስተው ሰው እንዲኖረኝ መመኘትን ዋነኛ አላማዬ በማድረግ አይደለም፡፡ እግርኳስን በከፍተኛ ደረጃ ስለምወደው እጫወታለሁ፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ ወደ ሜዳ ይዤው የምገባው ዋነኛ አላማ ለምሰለፍበት ቡድን ስኬታማ ተግባርን ለመፈፀም የተቻለኝን ሁሉ ጥረትን ማድረግ መቻል ነው፡፡
ጥያቄ፡- በቅርቡ ጉዳት ሲደርስብህ ለመጀመሪያ ጊዜ በውስጥህ ያሳደርከው ስሜት ምንድነው?
መልስ፡- ከዚህ በፊት ጉዳት ሲደርስብኝ ከነበረኝ ሁኔታ በተለየ ለየት ያለ ስሜትን አሳድሬያለሁ፡፡ ምክንያቱም ጉዳቱ አንድ መደበኛ ግጭት አለመሆኑንና አስከፊነት ያለው መሆኑን ያወቅኩት ገና ከዛኑ ጊዜ አንስቶ ነው ለጉዳት መጋለጥ ለማንኛውም ፕሮፌሽናል ስፖርታዊ ትልቁ ሃዘንን የሚፈጥር ጉዳይ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን በጠንካራ ስነ ልቦና ሆኜ በፍጥነት ለማገገም የሚረዳኝን እንቅስቃሴዎችን ላይ በመሆኔ ጥረቴ ፍሬያማ እንደሚሆንብኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ጥያቄ፡- ከሪያል ማድሪድ ጋር ለሚረገው የዘንድሮው ሲዝን የመጀመሪያው ኤልክላሲኮ እደርሳለሁ የሚል ግምት አለህ?
መልስ፡- በዚህ ጉዳይ ዙሪያ እርግጠኛ ሆኜ አስተያየትን መስጠት ይከብደኛል፡፡ ሙሉ ትኩረት የህክምና ባለሙያዎች የሚሰጡንን መመሪያን በማክበር ሁሉንም አይት የማገገም ጥረቶችን በማድረጉ ተግባር ላይ ያነጣጠረ ነው፡፡ ከዚህ በተረፈ ግን በጥሩ ጤንነት የምገኝበት ወቅትን በትክክል ለመገመት የሚችሉት በማገገም ጥረቴ ከጎኔ ሳይለዩ ድጋፍን እየሰጡን በሚገኙት የህክምና ባለሙያዎች እንጂ እኔ ልሆን አልችልም፡፡
ጥያቄ፡- ባርሴሎና ያለፈው ሲዝንን የሶስት ትላልቅ ውድድር ዋንጫዎች ድሎችን ዘንድሮ ይደግመዋል የሚል እምነት አለህ?
መልስ፡- የውድድር ዘመኑ ገና የመጀመሪያው ሶስት ወራት ያላለቀ በመሆኑ በዚህ ጉዳይ ከወዲሁ እርግጠኛ ሆኖ መናገር ይከብዳል፡፡ ምክንያቱም የሲዝኑ ሰፊው አካል ያለው ከፊታችን ያለው ስድስት ሰባት ወራት ውስጥ ነው፡፡ ካለፈው ሲዝን በትሪፕል ዊነርነት(ሶስት ዋንጫ) ድል ለማጠናቀቅ የቻሉት አብዛኛዎቹ የቡድናችን ተሰላፊዎች እስካሁንም ድረስ በስኳዳችን የሚገኙ በመሆናቸው ግን በተሳተፍንባቸው እያንዳንዱ ውድድሮች የዋንጫ ሽልማቶችን ለማግኘት እንችላለን የሚል ሙሉ እምነትን ለማሳደር የምንቆጠብበት ምክንያት አይኖረንም፡፡
የውድድር ዘመኑን የጀመርነውም በጥሩ አቋም ሆነን መሆኑን አምናለሁ፡፡ ከመጀመሪያዎቹ ዘጠን የስፓኒሽ ላ ሊጋ ግጥሚያዎች በኋላ በደረጃው ሰንጠረዥ ከዋነኛ ተቀናቃኞቹ ሪያል ማድሪድ እኩል 21 ነጥቦችን መያዛችን ከግንዛቤ ሲገባም የዛሬ ዓመት በተመሳሳይ ወቅት ከነበረን የነጥብ ድምር አንፃር የዘንድሮው የተሻለ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ያለፈው ሲዝን እስኪጋመስ ድረስ በቡድናችን ላይ የታየው የአቋም አለመረጋጋት ችግር ዘንድሮ ሲደገም አልታየም፡፡ ከዚህ አንፃር የዘንድሮ ሲዝንን ለሌላ የትሪፕል ዊነርነት ድል ለመብቃት በማለም የማናካሂድበት ምክንያት አይኖርም፡፡
The post Sport: ‹‹የምኖረውና የማስበው ስለ አሁኑ ብቻ ነው›› ሜሲ – (አዲስ ቃለምልልስ ከያሁ ስፖርት ጋር) appeared first on Zehabesha Amharic.