ምንም እንኳን ማንችስተር ዩናይትድ ከሊጉ መሪ አርሰናል በዘጠኝ ነጥቦች ርቀት ላይ ቢገኝም የግማሽ የውድድር ዘመን የቀያዮቹ ሰይጣኖች አቅም ሲመዘን አሁንም ዩናይትድ የሊጉ ሻምፒዮን አሊያም በቻምፒዮንስ ሊግ የሚያሳትፈውን ደረጃ ይዞ ለማጠናቀቁ ዋስትና የለውም፡፡
ግብ ለማስቆጠር የሚቸገረው የሉዊ ቫን ሃል ቡድን በመጀመሪያው ሮክ ግማሽ የውድድር ዘመን ጥሩ ጎኑ ይነሳ ከተባለ የተከላከይ ክፍሉ በየጨዋታው በአማካይ ከአንድ ጎል በታች የሚያስተናግድበት መልካም ሪከርዱ ነው፡፡ ስፔናዊው ግብ ጠባቂ ዴቪድ ደ ሂያ አሁንም ምርጥ ብቃቱን ይዞ መዝለቁ ጉልህ ድርሻ አለው፡፡ ታዲያ ግብ ጠባቂው በውድድር ዘመኑ ዩናይትድ አንድ አይነት ዋንጫን አንስቶ ማጠናቀቅ ከፈለገ ይሄን የመከላከል ሪከርዱን ጠብቆ መጓዝ እንደሚኖርበት ሂያ በአፅንኦት ያስረዳል፡፡
በስፔን ብሔራዊ ቡድን ውስጥ የአኪር ካሲያስ የረዥም ጊዜ ተተኪ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው ዳቪድ ደ ሂያ በሰጠው ቃለ ምልልስ ይሄንና ሌሎችን ጉዳዮች ዳስሷል፡፡
ጥያቄ፡- ተደጋጋሚ ጉቶች የፈጠረው ተፅዕኖ እንዳለ ሆኖ የጣላችኋቸው ቁልፍ ነጥቦች ተስፋ እንድትቆርጡ አድርጓችሁ ይሆን?
መልስ፡- ይመስለኛል፡፡ ሁልጊዜም ቁልፍ ተጨዋቾች ጉዳት የሚያስተናግዱ ከሆነ ጨዋታዎችን ማሸነፍ ይከብዳል፡፡ እኛም በዚህ አይነት ሁኔታዎች ያለፍንባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ፤ ነገር ግን ይሄ በተለይ ደረጃው ከፍ ባለ ሊግ የሚያጋጥም ነገር ነው፡፡ ኣዲሶቹ ወጣቶች ልምድ ያላቸውን ተጨዋቾች ተክተው የሚችሉትን ያህል አገልግሎት ሰጥተዋል፡፡ የአንጋፋዎቹን ያህል አስተዋፅኦ ከወጣቶቹ መጠበቅ ግን ተገቢ አይመስለኝም፡፡
ጥያቄ፡- ከዘንድሮው ዩናይትድ ጥሩ ነገር ይነሳ ከተባለ የተከላካይ ክፍሉ ሪከርድ ይጠቀሳል፡፡ በሙሉ ጥንካሬው ላይ ሲገኝ የውድድር ዘመኑን በስኬት ለማጠናቀቅ ምን ያህል አስተዋፅኦ ይኖረዋል?
መልስ፡- የተከላካይ መስመራችን ከአምናው በተሻለ ዘንድሮ ጠንካራ ይመስልሃል፡፡ ይሄ ደግሞ በጣም ወሳኝ እና አስፈላጊ ነው፡፡ ጎሎችን እንደ አምናው አብዝተን እያስተናገድን አይደለም፡፡ በማጥቃት ሚና ያለንን ጥራት በሚገባ ተጠቅመን ጎሎችን ካስቆጠርንና የተከላካይ ክፍሉ በዚህ ጥንካሬው ከቀጠለ ዩናይትድ የውድድር ዘመኑን በስኬት የማጠናቀቅ ዕድሉ የሰፋ ነው፡፡
ጥያቄ፡- ከዚህ ቀደም በኦልድ ትራፎርድ መጫወት የሚከብዳቸው በተለይ የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ዩናይትድን እየፈተኑት ነው፡፡ ምናልባት የትኩረት እና የመደራጀት ችግር ይሆን?
መልስ፡- ይመስለኛል፤ ብዙ ጊዜ በኦልድ ትራፎርድ ስንጫወት ኳስን አብዝተን ስለምንቆጣጠር፤ በትኩረት ማጣት ጎሎችን አስተናግደን ነጥብ የጣልንባቸው ጨዋታዎች ነበሩ፡፡ አንዳንድ ቡድኖች ለረዥም ደቂቃ የጎል ዕድል ሳይፈጥሩ ቆይተው በድንገት መዳኛ መከላከል ቀጠና ይደርሳሉ፡፡ በዚህ ጊዜ የመከላከል ቅርፃችን ከተበላሸና ትኩረታችንን ካጣን ጎል ይቆጠርብናል፡፡
ጥያቄ፡- አንተ ወደ ኦልድ ትራፎርድ በመጣህበት ዓመት በሜዳችሁ ስትጫወቱ የነበረውን ሁኔታ ከዘንድሮው ጋር ስታነፃፅረው ምን አይነት ምስል ይሰጥሃል?
መልስ፡- ወደ ኦልድ ትራፎርድ መጥተው የሚጫወቱ ክለቦች ሁልጊዜም አዕምሯቸው ውስጥ የሚይዙት ከግዙፍ ክለብ ጋር እንደሚጫወቱ ነው፡፡ እነዚህ ክለቦች በራሳቸው ሜዳ ላይ ጥቅጥቅብለው መጫወትን ይመርጣሉ፡፡ ግን እንደ የክለቦቹ ይለያያል ክፍተቶችን ፈልገው ጎል ሊያስቆጥሩብን የሚመጡ ቡድኖችም ነበሩ፡፡ አሁን የዚህ አይነት ቡድኖች በርክተዋል፡፡
ጥያቄ፡- በማንቸስተር ዩናይትድ አምስተኛ ዓመትህን ይዘሃል፡፡ ከቆይታህ አንፃር አሁን የበለጠ ኃላፊነት ይሰማሃል?
መልስ፡- አሁን በዩናይትድ በርካታ አዳዲስ ወጣቶችን እየተመለከትኩ ነው፡፡ በርካታ ጨዋታዎችን ታደርጋለህ፡፡ ይሄ ደግሞ ተፅዕኖህ ከፍ እያለ እንዲሄድ ያደርገዋል፡፡ እንደ ግብ ጠባቂነቴ በተለይ የተከላካይ ክፍሉን መምራት ይጠበቅብኛል፡፡ ተከላካዮቻችን ከጫና ነፃ ሆነው እንዲጫወቱ ያደርጋቸዋል፡፡
ጥያቄ፡- በቻምፒዮንስ ሊግ ከምድብ ጨዋታዎች ማለፍ አለመቻላችሁ ምን ስሜት ፈጠረባችሁ? ዩሮፓ ሊግ መፅናኛ ይሆናችኋል?
መልስ፡- ዩሮፓ ሊግ ለእኔ ጥሩ ስሜት የሚሰጠኝ ፉክክር ነው፡፡ በተለይ በ2010 ከአትሌቲኮ ማድሪድ ጋር ሆኜ ይሄን ዋንጫ አጣጥሜዋለሁ፡፡ ነገር ግን ይሄ በቻምፒዮንስ ሊግ ታሪክ ደማቅ አሻራ ያለው ማንቸስተር ዩናይትድ ነው፤ አሁን በሌላ ውድድር ውሰጥ ነን፤ ዩሮፓ ሊግን በዜይቢያዊ መንገድ ለማሸነፍ ጥረት እናደርጋለን፡፡ የማክሰኞ እና ረቡዕ የቻምፒዮጀንስ ሊግ ምሽቶችን ለለመደው ዩናይትድ ግን እንግዳ ነገር መሆኑ እርግጥ ነው፡፡ ቢሆንም ግን የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎችን በበቂ ዝግጅት ማድረግ ይኖርብናል፡፡ የምንገጥመው ትንሽ የሚመስለውን የዴንማርኩን ሚዲቲላድን ነው፤ ነገር ግን የደርሶ መልሱን ጨዋታ አሸንፈን በድል መንገድ እንደምንጓዝ ሙሉ ተስፋ አለኝ፡፡
ጥያቄ፡- ከአትሌቲኮ ማድሪድ ጋር የዩሮፓ ሊግን ዋንጫ ያነሳው ከቻምፒዮንስ ሊግ ውጭ ከሆናችሁ በኋላ ነበር፡፡ ድሉን ያከበራችሁት ግን ለየት ባለ ሁኔታ ነበር፡፡
መልስ፡- በጣም ትክክል፡፡ ዋንጫዎችን ማሸነፍ የተለየ ስሜት ይሰጣል፡፡ እግርኳስ የቡድን ስፐርት እንደ መሆኑ ደስታውን በጋራ ማጣጣም ልዩ ነው፡፡ ለእኔ ግን የእንግሊዙን ፉልሃም አሸንፈን ዋንጫውን ያነሳንበትን ቀን የማልረሳው ነው፡፡
ጥያቄ፡- ከፊትህ የዩሮ 2016 ሻምፒዮና ይጠብቅሃል፤ ከፈረንሳይ ጉዞ በፊት ምን እያሰብክ ነው?
መልስ፡- ውድድሩ የሚጀምረው ገና ሰኔ ወር ላይ ነው፡፡ የመጀመሪያው ከዚያ በፊት በርካታ ፈተናዎች በክለቤ ይጠብቀኛል፡፡ ጊዜው ሲደርስ ግን ልዩ ስሜት የሚፈጥር ውድድር ይሆናል፡፡ ከስሜን ጋር የዩሮ 2012 ክብራችንን ለማስጠበቅ ከቡድኑ ጋር ተካትቼ መጓዝ ያስደስተኛል፡፡
The post Sport: ‹‹የተከላካይ ክፍሉ በዚህ ጥንካሬው ከቀጠለ ዩናይትድ የውድድር ዘመኑን በስኬት የማጠናቀቅ ዕድሉ የሰፋ ነው›› ዳቪድ ደ ሂያ appeared first on Zehabesha Amharic.