አስተማማኝ የነበረው የፍራንሲስ ኮከለ እና የባንቲ ካቦርላ ጥምረት በጉዳት ሳቢያ መፍረሱን ተከትሎ አርሰን ቬንገር አሮን ራምሴን ከማቲው ፍላሚኒ ጋር ለመጫወት ተገድደዋል፡፡ ውድድር ዘመኑ ወደ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ በደረሰበት ጊዜ መድፈኞቹ በጉዳት የመሳሳት አደጋ ቢጋረጥባቸውም የጥር ወር የዝውውር መስኮት ግን በጊዜ ደርሶላቸዋል፡፡
አርሰናል የሊጉን ዋንጫ ከ12 ዓመታት በኋላ ለማንሳት መልካም አጋጣሚ እንደ ዘንድሮው ያገኘ አይመስልም፡፡ ታዲያ ይሄን ዕድል ለመጠቀም አርሰን ቬንገር ከዝውው ገበያው ሸምተዋል፡፡
ከእነዚህ ውስጥ በግንባር ቀደምትነት ሊጠቀስ የሚችለው የባዝሉ ሞሐመድ ኤልኔኒ የኤምሬትስን በር አንኳክቶ መግባቱ ነው፡፡ ገና የአምስት ዓመት ጨቅላ ሳለ ነው የታላቁን የግብፅ ክለብ አል አህሊን አካዳሚ የተቀላቀለው ኤልኒኔ ለአፍሪካ የምንጊዜውም ስኬታማ ክለብ ዋና ቡድን መጫወት ባይችልም ወደ አውሮፓ አቅንቶ በስዊዘርላንድ ከባዝል ጋር ጣፋጭ አምስት ዓመታትን አሳልፏል፡፡ በዝነኛው የሜዳ ቴኒስ ኮከብ ሮጀርስ ፌዴረር ከሚደገፈው ባዝል ጋር አራት የሊግ ዋንጫዎችን ማንሳት ችሏል፡፡ ኤልኔኒ ከባዝል ጋር የቻምፒዮንስ ሊግ ምሽቶችን አጣጥሟል፤ እንዲያውም በ2013 ቼልሲን ቢያሸንፍ የግብፃዊው አስተዋፅኦ ጉልህ ነበር፡፡
የ23 ዓመቱ አማካይ አሁን የመፈተኛ ጊዜው ላይ ደርሷል፡፡ በአርሰን ቬንገር የምልመላ ኔት ዎርክ አዲሱ መድፈኛ ለመሆን ችሏል፡፡ ቬንገር ለተንቃነቀባቸው የሆልዲንግ አማካይ ቦታ አይናቸው ብዙ አማትሯል፡፡ የስፖርቲንግ ሊዝበኑ ዊሊያም ካርቫልሆ፣ የሲቪያው ግሪጎርዝ ኪሪያ፣ ያክ እና የሳውዝምፕተኑን ቬክቶር ዋንያማ ትኩረታቸውን ከሳቡት መካከል ዋነኞቹ ነበሩ፡፡ በመጨረሻም ግን ሞሐመድ ኤልኒኔ ምርጫቸው ለመሆን በቅቷል፡፡ ለመሆኑ የአርሰናልን አማካይ ክፍል ጥንካሬ ይመልሳል የተባለለት ሞሐመድ ኤልኔኒ ጠንካራ ጎኑ የትኛው ነው? በቬንገር ይሞሉለታል ተብለው የሚጠበቁት ደካማ ጎኖቹስ? በየትኛውም ሚና ስታይል ስኬታማ ይሆናል?
የመጀመሪያው መንገድ
ኤልኔኒ የአል አህሊ አካዳሚን የተቀላቀለው እ.ኤ.አ በ1997 ነበር፡፡ ታዲያ የመኖሪያ ቤታቸው ከካይሮ ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቃ ከምትገኘው ኤል ማሃላ ወደ አል አህሊ በየዕለቱ ወደ ልምምድ ለመሄድ በባቡር መጓዝ አልያም አውቶቡስ መሳፈር ይጠበቅበት ነበር፡፡ ጨቅላው ኤልኔኒ ይሄን ብቻውን ስለማይወጣው ወላጅ እናቱ ዘወትር አብረውት ይሆኑ ነበር፡፡
አመሻሽተው ወደ መኖሪያ ቤታቸው መመለስም ግዴታቸው ነበር፡፡ በአል አህሊ ዕድገት ያሳየው ኤልኔኒ በወጣት ቡድን ደረጃ በግብፁ ኃያል ክለብ በርከት ያሉ ጨዋታዎችን ማድረግ ቢችልም ዋናውን ቡድን ሰብሮ ለመግባት ግን አልተቻለውም፣ እንዲያውም በ2008 አል አህሊ ለሌላኛው የግብፅ ክለብ ኤል ሞካውሉን አሳልፎ ሰጠው፡፡ በአዲሱ ክለቡ ወደ ዋናው ቡድን ለማደግ ሁለት ዓመታትን በትዕግስት ከጠበቀ በኋላ በግብፅ ሊግ በየሳምንቱ የሚታይ ፊት ሆነ፤ በብቃቱ የተማረኩ የግብፅ ከ23 ዓመት በታች ቡድን አሰልጣኝ ወደ ለንደን ኦሎምፒክ ባመራው የግብፅ ቡን ውስጥ አካተቱት፡፡ ግብፅ በሩብ ፍፃሜው በጃፓን ተሸንፋ ከኦሎምፒክ ውጪ እስክትሆን ድረስ ኤልኔኒ አራት ጨዋታዎች አደረገ፡፡
ኤልኔኒ በስዊዙ ባዝል እይታ ውስጥ የገባው ከለንደን ኦሎምፒክ በኋላ ነበር፡፡ ባዝል ለስድስት ወራት በኳስ አዘዋዋሪነት ብቃቱ አመርቂ ሆኖ ካገኘው በቋሚነት ሊያስፈርመው ከአል ሞካውሉን ጋር ስምምነት ላይ ደረሱ፡፡ በ2013 ባዝል የሊግ ዋንጫውን እንዳነሳ ኤልኔኒን በቋሚነት እንደሚያዘዋውረው ይፋ አደረገ፡፡
የአጨዋወት ስታይል እና ጥንካሬ
አብዛኛውን ጊዜ በጥልቅ አማካይነት ሲጫወት ቢስተዋልም በአማካይ ክፍል የተለያዩ ሚናዎችን በብቃት መወጣት ይችላል፡፡ ከሳጥን ሳጥን የሚሮጥ አማካይ ሆኖ ባዝልን አገልግሏል፡፡ ለአጥቂ ጀርባ የአስር ቁጥር ሚናን መወጣት እንደሚችልም አሳይቷል፡፡ ኤልኔኒ ረዥም ኳሶችን ለተጋጣሚዎቹ ሲያቀብል ስኬታማ ነው፡፡ የሚያስቆጥራቸው ጎሎች አብዛኞቹ ከፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውጪ የተመቱ ናቸው፡፡ በቆሙ ኳሶች አጠቃቀሙ የሚወደሰው ኤልኔኒ የክለቡ ቋሚ የቅጣት ምት፣ ፍፁም ቅጣት ምትና የማዕዘን ምት መቺ ነው፡፡
የቴክኒክ ክህሎቱን ያህል ሜዳ ላይም አይደክሜ ነው፡፡ ኳሷን ለማስጣል የሚወርዳቸው ሸርተቴዎች በአብዛኛው ስኬታማ ናቸው፡፡ ባዝል ዘንድሮ በዩሮፓ ሊግ ስኬታማ ጉዞን ሲያደርግ ኤልኔን በአምስት ጨዋታዎች ከጥልቅ አማካይ ሚናው እየተነሳ ሁለት ጎሎችን አስቆጥሯል፡፡ የጨዋታ ኮከብ በተባለበት የፊዮረንቲና ጨዋታ ያስመዘገበው የማቀበል ስኬቱ 92.4 በመቶ ነበር፡፡
ደካማ ጎን
የበርካታ ኳሊቲዎች ባለቤት የመሆኑን ያህል ኤልኔኒ ድክመቶችም አሉበት፣ የድሪብል ችሎታውን ካላሳደገ በተለይ ተጭነው (higher up the pltch) የሚጫወቱ ቡድኖች ሲያጋጥሙት ይቸገራል፡፡ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ high tempo pressing አጨዋወት እየተመረጠ መምጣት ለኤልኔኒ ስጋት ሊሆን ይችላል፡፡
በአርሰናል የትኛው ሚና ይስማማዋል?
ሳንቲ ካዞርላ፣ ፍራንሲስ ኮከለ እና ጃክ ዊልሽር ከጉዳታቸው ሲያገግሙ የአርሰናልን የአጨዋወት ክፍል ጥንካሬ የመመለስ ብቃት ቢኖራቸውም፣ መድፈኞቹ ዕድሜያቸው የገፋው ሚኬል አርቴታ ቶማስ ሮዚስኪ እና ማቲው ፍላሚኒን በክረምቱ ኮንትራታቸው ሲጠናቀቅ ተሰናባቾች ናቸው፡፡
ኤልኔኒ ለአርሰናል የረዥም ጊዜ መፍትሄ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ካዞርላና ኮከለ ከጉዳት እስኪያገግሙ ለአርሰናል አማካይ ክፍል በቂ ሽፋን መስጠት ይችላል፡፡ በአማካይ ክፍል የተለያዩ ሚናዎች የመወጣት ኳሊቲ ቢኖረውም አርሰን ቬንገር በዋነኛነት በተከላካይ አማካይ ሚና የፍራንሲስ ኮክለ ሽፋን እንዲሆንላቸው ይፈልጋሉ፡፡
ባለፈው ሐምሌ ወር 23ኛ ዓመቱን የያዘው ኤልኔኒ ከፊቱ ብሩህ ጊዜ ይጠብቀዋል ብሎ መናገር ይቻላል፡፡ ወጣቶችን በማፍራት በሚታወቁት አርሰን ቬንገር እጅ መውደቁ ወደፊት የተሻሻለው እና ምርጡን ሞሐመድ ኤልኔኒን እንድናየው ያደረገን ይሆናል፡፡ ሞሐመድ ኤልኔኒ ከባዝል ወጥቶ ፕሪሚየር ሊጉን የተቀላቀለ ብቸኛው ግብፃዊ አይደለም፡፡ እንደ ወንድሙ የሚያየው እና በግብፅ በኤል ሞካውሉን ክለብ አብሮት የተጫወተው ሞሐመድ ሳላህም ለቼልሲ ተጫውቷል፡፡ ሳላህ በ2012 ባዝልን ሲቀላቀል ‹‹ወንድሙ›› ኤልኔኒ በዓመቱ ተከትሎታል፡፡
The post Sport: አዲሱ መድፈኛ ሞሐመድ ኤልኔኒ ማነው? appeared first on Zehabesha Amharic.