‹‹በዘመናዊ ፉትቦል እጅግ ተፈላጊው የአጥቂ መስመር ተጨዋች ነው›› በማለት የማንችስተር ሲቲው አሰልጣኝ ማኑኤል ፔሌግሪኒ የገለፁት በ49 ሚሊዮን ፓውንድ ከሊቨርፑል የገዙትን የ20 ዓመቱን እንግሊዛዊ ራሂም ስተርሊንግን ነው፡፡ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ውድድርና በማንችስተር ሲቲ ታሪክ የውድ ዋጋ ግዥ የሆነው ስተርሊንግ በበኩሉ በአዲሱ ክለቡ ከሚገኑ ወርልድ ክላስ ፉትቦለሮች ጋር አብሮ ለመሰለፍ ያለው ጉጉት በእጅግ ከፍተኛ መሆኑን ያረጋገጠበት መግለጫን ሰጥቷል፡፡
ለበርካታ ሳምንታት የሚዲያውን ሰፊ ትኩረትን ስቦ የዘለቀው ስተርሊንግ ከአንፊልድ ወደ ኢትሃድ ያደረገው ዝውውር ሙሉ ለሙሉ ተፈፃሚ የሆነው ተጨዋቹ ከማንችስተር ሲቲ የቀረበለት 180 ሺ ፓውንድ ሳምንታዊ የደመወዝ ክፍያን ለመቀበል ፈቃደኛ በመሆኑ ነው፡፡ ማንቸስተር ሲቲ የአቡዳቢ ባለሀብቶች በሚመሩት ሼክ መንሱር ባለቤትነት በ2008 ከተገዛ ወዲህ ለስተርሊንግ የከፈለውን ጨምሮ ባለፉት ሰባት ዓመታት ውስጥ በአጠቃላይ ለ467 ተጨዋቾች ግዢ በድምሩ 719.1 ሚሊዮን ፓውንድ ሂሳብ አውጥቷል፡፡
በሼክ መንሱር ባለቤትነት 46ኛው የተጫዋች ግዥ ውልን የፈረመው ስተርሊንግ ለቀድሞው ክለቡ ሊቨርፑል በ129 ግጥሚያዎች ከተሰለፈ በኋላ ወደ ማንቸስተር ሲቲ ለማምራት የወሰነበት ዋነኛ ምክንያቱ ሊቨርፑል ባቀረበለት የተጨማሪ ዓመታት ኮንትራት ውል ሊሰጠው ባቀደው 100 ሺ ፓውንድ የሳምንት ደመወዝ ደስተኛ ባለመሆኑ ነው፡፡ ሆኖም ግን ስተርሊንግ ለማንቸስተር ሲቲ በይፋ በመፈረም በተቃራኒው አቅጣጫ ወደ ሊቨርፑል በነፃ ዝውውር የሄደው ሌላው እንግሊዛዊው ኢንተርናሽል ጀምስ ሚልነር ይለብሰው የነበረው 7 ቁጥር ማሊያን ከተረከበ በኋላ በሰጠው መግለጫው ዝውውሩን ያደረገበት ዋነኛ ምክንያቱ በሜዳ ላይ ካለው ፉትቦሉ ጋር የተያያዘ መሆኑን ለማመልከት ሞክሯል፡፡
‹‹የዝውውር ውሉ ከሚጠበቀው ጊዜ ቀደም ብሎ ተፈፃሚ በመሆኑ ከፍተኛ የሆነ የደስታ መንፈስን አሳድሬያለሁ፡፡ ይህ ለእኔም ሆነ ለቤተሰቤ አባላት በጠቅላላ ትልቅ እፎይታን የፈጠረልን ጉዳይ ሆኗል›› ያለው ስተርሊንግ በመቀጠልም ‹‹ከሁሉም በላይ የእኔን ከፍተኛ ትኩረትን የሳበው በርካታ ኳሊቲ ያላቸው ፉትቦለሮች የሚገኙበት የማንቸስተር ሲቲ ጠንካራ ስኳድ አንዱ አባል መሆን መቻሌ ነው፡፡ በስኳዱ የሚገኙት አብዛኛዎቹ ተጨዋቾች ከዚህ በፊት የትላልቅ ውድድሮች የዋንጫ ሽልማቶችን የማግኘት ሰፊ ልምድን ያካበቱ በመሆናቸውም በማንችስተር ሲቲ ቆይታዬ እጅግ ተደናቂ ስኬትን ለማስመዝገብ እንደምችል እርግጠኛ ነኝ፡፡ በእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ካምፕ ለመጨረሻ ጊዜ በተገኘንበት ወቅት ጆ ኸርት የማንቸስተር ሲቲ ስላለው አጠቃላዩ እውነታ ምንነትን በጥንቃቄ አስረድቶኛል፡፡
በተለይ የማንችስተር ሲቲ ደጋፊዎች ተደናቂነቱን ሲነግረኝ ወደዚህ ክለብ የመምጣት ውሳኔዬን እንድገፋበት ምክንያት ሆኖኛል፡፡ ወደዚህ እጅግ ትልቅ ክለብ ለመምጣት የቻልኩት ከኪው.ፒ.አር አንስቶ ለበርካታ ዓመታት ፉትቦሌን ወደ ትልቅ ደረጃ ለማሸጋገር ሳደርገው በዘለቅኩበት ያለሰለሰ ጥረት ፍሬያማ ሆኜ በመሆኑ በራሴ ኩራትን የማላሳድርበት ምክንያት አይኖረኝም፡፡ ስኬታማ እንድሆን ከጎኔ ባለመለየት ከፍተኛ የሆነ ድጋፍን ሲያደርጉልኝ ለዘለቁት ባለሙያዎች በጠቅላላ ያለኝ ምስጋናም ከፍተኛ ነው፡፡
በተለይም ራፋ ቤኒቴዝ ገና በ15 ዓመት ዕድሜዬ ለሊቨርፑል እንድፈርም በማድረግ ትልቅ ውለታን ሰርተውልኛል፡፡ ምክንያቱም ከኪውፒአር ወደ ሊቨርፑል መሸጋገር አጠቃላዩ የፉትቦል ህይወቴን ወደ ትልቅ ደረጃ ለማሸጋገር የቻልኩበትን መሰረትን ያመቻችልኝ ሆኗል፡፡ ከዛ በኋላም ኬኒ ዳግሊሽ ለሊቨርፑል ዋናው ቡድን በመደበኛ ቋሚ ተሰላፊነት የመጫወት እድልን ሰጥቶኝ ሌላኛውን ትልቅ ውለታን አበርክተውልኛል፡፡
ብሬንዳን ሮጀርስም ለእኔ ብቃት ሙሉ እምነትን አሳድረው በመዝለቃቸው በዚህ አጋጣሚ ላመሰግናቸው እወዳለሁ፡፡ በተለይም ሮጀርስ ከማንቸስተር ሲቲ ጋር በተደረገው ግጥሚያ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሊቨርፑል ዋናው ቡድን በመደበኛ ቋሚ ተሰላፊነት የመጫወት ዕድልን በመስጠት መላው ዓለም ምርጥ ብቃቱን ለማየት እንዲችል ትልቅ አስተዋፅኦን ስላበረከቱልኝ ከልብ ላመሰግናቸው እወዳለሁ፡፡ በአጠቃላይ የሊቨርፑል ቆይታዬም ችሎታዬን ወደ ትልቅ ደረጃ ለማሸጋገር የቻልኩበት በመሆኑ ለክለቡ ደጋፊዎችና አባላት የሚኖረኝ ክብር ከፍተኛ ሆኖ ይዘልቃል፡፡ ተስፋ የሚደረገውም የሊቨርፑል ደጋፊዎች ይህንን ዝውውርን ለማድረግ እንድወስን ምክንያት የሆነኝ ጉዳይ ምን እንደሆነ ጠንቅቀው ይረዱታል ብዬ ነው›› የሚል አስተያየቱን አክሏል፡፡
ስተርሊንግ ለሊቨርፑል ለመጨረሻ ጊዜ የተሰለፈበትን የ2014/15 ሲዝንን ያሳለፈው በ35 ግጥሚያዎች ተሰልፎ 7 ጎሎችን ብቻ በማስቆጠር ነው፡፡ ይህንን ከግንዛቤ በማስገባት በርካታ አስተያየት ሰጪዎች ማንቸስተር ሲቲ ለ20 ዓመቱ እንግሊዛዊ ኢንተርናሽል ያወጣበት 49 ሚሊየን ፓውንድ ሂሳብ በትክክል የሚመጥነው መሆኑ አጠራጣሪ ሲሆንባቸው መታየታቸው የተለመደ ሆኗል፡፡ ሆኖም ግን የማንቸስተር ሲቲው አሰልጣኝ ማኑኤል ፔሌግሪኒ ስተርሊንግን የገዙበት የዋጋ መጠን ትክክለኛ መሆኑ በአዲሱ ሲዝን ተጫዋቹ ለቡድናቸው በሚኖረው ቁልፍ ሚና በትክክል እንደሚጋገጥ እርግጠኛ ሆነዋል፡፡
‹‹ራሂም ስተርሊንግ በአሁኑ ወቅት በዓለም ፉትቦል ከሚገኙት እጅግ የተዋጣለት ብቃት ካላቸው የማጥቃት ላይ ያተኮረ ውጤታማ እንቅስቃሴ ካላቸው ምርጥ ፉትቦለሮች አንዱ ነው፡፡ ለዚህ ምንም አይነት ጥርጣሬ ስለሌለኝም ክለባችን በውድ ዋጋ እንዲገዛው ባደረግኩት ውሳኔዬ ሙሉ ኃላፊነትን እንደምወስድለት ማረጋገጥ እወዳለሁ›› ያሉት ቺሊያዊው አሰልጣን በመቀጠልም ‹‹እርግጠኛ ሆኜ ለመናገር የምወደውም የማንቸስተር ሲቲ ደጋፊዎች በዚህ ተጨዋች አስገራሚ ብቃት ገና ከመጀመሪያ ግጥሚያው አንስቶ ሙሉ ለሙሉ ደስተኛ የሚሆኑበት መሆኑን ነው፡፡ የዝውውር ውሉ ከወዲሁ ሙሉ ለሙሉ ተፈፃሚ መሆን መቻሉም ከሌሎቹ የቡድናችን ተሰላፊዎች ጋር በመሆን በአውስትራሊያና ወደ ሩቅ ምስራቅ በመጓዝ የምናደርገውን የፕሪ ሲዝን ዝግጅት ጉዞ ላይ ተሳታፊ ለመሆን የሚረዳው ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ስተርሊንግ ከቡድናችን የጨዋታ ስታይል ጋር በፍጥነት ለመዋሃድ እንደሚችል ምንም አይነት ጥርጣሬ የለኝም›› የሚል አስተያየታቸውን አክለዋል፡፡
ማንቸስተር ዩናይትድ አንሄል ዲ ማሪያን እንዲሁም ቼልሲ ፈርናንዶ ቶሬስን ከገዛባቸው ውሎች ቀጥሎ ማንቸስተር ሲቲ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ታሪክ ሶስተኛው ትልቅ ዋጋ የወጣበት ስተርሊንግ በበኩሉ ለአዲሱ ክለቡ ደጋፊዎች ባስተላለፈው መልዕክቱ ‹‹ማንቸስተር ሲቲን ወደ መሰለ ግዙፍ ስኳድ ወዳለው ክለብ የመጣሁት የትላልቅ ውድድሮች የዋንጫ ሽልማቶችን ለማግኘት ያለኝን ጉጉት ለማሳካት እንድችል የበኩሌን ትልቅ እገዛን ለማበርከት የምችልበት አስተማማኝ ብቃትን ለመላበስ ለመቻል ሙሉ ለሙሉ እርግጠኛ በመሆኔ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር በዚህ ክለብ ቆይታዬ ተደናቂ ስኬት እንደሚኖረኝ ከወዲሁ ለማንቸስተር ሲቲ ደጋፊዎች ቃል ልገባላቸው እወዳለሁ›› ብሏል፡፡
የራሂም ስተርሊንግ ውጣ ውረድ የበዛበት የአንፊልድ ቆይታው ሲዳሰስ
በአሁኑ የዝውውር መስኮት በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ከተፈፀሙት ውሎች ውስጥ በአወዛጋቢነቱ ቅድሚያ የተሰጠው ራሂም ስተርሊንግ ለሊቨርፑል በበቂ ሁኔታ ጥቅም ሳይሰጥ ለማንቸስተር ሲቲ የፈረመበት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ተጨዋቹ ሊቨርፑልን የመልቀቅ ሃሳብ እንዳለው ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ የሆነው አሰልጣኝ ብሬንዳን ሮጀርስ ማርች 20/2015 በሰጡት መግለጫ ስተርሊንግ ክለባቸው ያቀረበለት የሳምንት ደመወዝን ወደ 100 ሺ ፓውንድ ኮንትራት ውል ማራዘምን እንደማይቀበለው እንደነገራቸው ይፋዊ መግለጫ ከተሰጠ በኋላ ነው፡፡
ከዛ ወዲህ ባሉት ወራት ውስጥ ሮጀርስና ሌሎቹ ኃላፊዎች የስተርሊንግን ሃሳብ ለማስቀየር የተቻላቸውን ሁሉ ጥረት ቢያደርጉም የ20 ዓመቱ እንግሊዛዊው ኢንተርናሽል የከፍተኛ ደመወዝ ተከፋይ የመሆን ጉጉትን ለመቀልበስ ሳይችሉ በመቅረታቸው በክለባቸው ደጋፊዎች ትልቅ ተስፋ አሳድሮ የዘለቀው ቁልፍ ተጨዋችን በ49 ሚሊየን ፓውንድ ሂሳብ ለማንቸስተር ሲቲ ለመሸጥ ተገድደዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት በይፋ በተፈረመው ውል ስተርሊንግ ለማንቸስተር ሲቲ ለመጫወት የተስማማው በአምስት ዓመታት ኮንትራት ውል ነው፡፡ በዛኑ ቆይታው ማንቸስተር ሲቲ 180 ሺ ፓውንድ የሳምንት ደመወዝ የሚከፍለውም ይሆናል፡፡
ይህንን እውነታን ከግንዛቤ በማስገባትም የፉትቦል ተንታኞች ስተርሊንግ ዕድሜው 15 ለመድፈን ሲቃረብ ኪው.ፒ.አርን በመልቀቅ ለሊቨርፑል ከፈረመ በኋላ በአንፊልድ የፉትቦል ህይወቱ ያጋጠመው አጠቃላዩ ሁኔታን ከዚህ በታች ባለው መልኩ መለስ ብለው ቃኝተውታል፡፡
ፌብርዋሪ 2010
ሊቨርፑል ራሂም ስተርሊንግን ከኪውፒአር ለመግዛት በተደረገው ጨረታ ከማንችስተር ዩናይትድ፣ ከማንቸስተር ሲቲ እና ከአርሰናል ጋር ያጋጠመውን ጨረታ በማሸነፍ ከ500 ሺ ፓውንድ ሂሳብ ገዝቶታል፡፡ በወቅቱ የዝውውር ስምምነት ውል ላይ ሊቨርፑል ተጨዋቹን መልሶ በሚሸጠው ወቅት ከሚያገኘው ሂሳብ 20 ፐርሰንቱን ለኪው.ፒ.አር ያካፍላል የሚለው አንቀጽ ተጠቅሶበታል፡፡
ፌብርዋሪ 2011
የሊቨርፑል ወጣት ቡድን የሳውዝ ኢንድ አቻውን 9ለ0 በሆነ ሰፊ ውጤት በረታበት የኤፍ.ኤ ዩዝ ካፕ ላይ ስተርሊንግ 5 ጎሎን በስሙ አስመዝግቧል፡፡
ማርች 2012
ዕድሜው 17 ዓመት ከ107 ቀናት በነበረበት ወቅት ስተርሊንግ ተቀይሮ በመግባት ሊቨርፑል ዊጋን አትሌቲክን 2ለ1 በረታበት ግጥሚያ ለመጀመሪያ ጊዜ ለዋናው ቡድን ተሰልፏል፡፡ ያንን ግጥሚያ ያደረገው በዛን ወቅት የሊቨርፑል አሰልጣን የነበሩት ኬኒ ዳግሊሽ ጨዋታው ሊጠናቀቅ ደቂቃዎች ብቻ ሲቀሩት በሆላንዳዊው ዲርክ ካይት ምትክ ቀይረውት አስገብተውት ነው፡፡
ኦክቶበር 2012
በአንፊልድ ሮድ በተደረገው ግጥሚያ ለሊቨርፑል የመጀመሪያው የነጥብ ጨዋታ ጎልን በስሙ ለማስመዝገብ ችሏል፡፡ ስተርሊንግ በጨዋታው 29ኛ ደቂቃ ላይ ከመረብ ያሳረፉት ጎሉ በመታገዝ የአሰልጣን ብሬንዳን ሮጀርስን ቡድን ሬዲንግን 1ለ0 ለማሸነፍ ችሏል፡፡
አፕሪል 2014
ለሊቨርፑል ዋናው ቡድን ለሙሉ ሲዝን ባደረጉት ግጥሚያዎች በአብዛኛዎቹ ጨዋታዎች ላይ በመሰለፍ የአሰልጣኝ ብሬንዳን ሮጀርስ ቡድን ጠንካራ የፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮንነት ፉክክርን እንዲያደርግ ረድቶታል፡፡ በተለይም በአፕሪል 2014 ስተርሊንግ ለሊቨርፑል ድል መገኘት ከፍተኛ ወሳኝነት ያላቸው ሶስት ጎሎችን ለማስቆጠር ችሏል፡፡ የስተርሊንግ ሶስት ወሳኝ ጎሎች ከመረብ ያረፉት ሊቨርል ማንቸስተር ሲቲና ኖርዊችን 3ለ2 በሆነ ተመሳሳይ ውጤት በረታባቸው የፕሪሚየር ሊግ ግጥሚያዎች ላይ ነው፡፡
ጁን 2014
ለእንግሊዝ ዋናው ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ በተሰለፈበት የ2014 የዓለም ዋንጫ ውድድር በሶቱም የአገሩ የምድብ ማጣሪያ ግጥሚያዎች ላይ በመደበኛ ቋሚ ተሰላፊነት በመጫወት ለወደፊቱ ትልቅ ተስፋ የሚጣልበትን ውጤታማ እንቅስቃሴን ለማበርከት ችሏል፡፡ ሆኖም ግን የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ከምድብ ማጣሪያው ውጭ ከመሆን አደጋ ሳያተርፈው ቀርቷል፡፡
ኦገስት 2014
ለእንግሊዝ ዋናው ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ በተሰለፈበት የ2014 የዓለም ዋንጫ ውድድር በሶስቱም የአገሩ የምድብ ማጣሪያ ግጥሚያዎች ላይ በመደበኛ ቋሚ ተሰላፊነት በመጫወት ለወደፊቱ ትልቅ ተስፋ የሚጣልበትን ውጤታማ እንቅስቃሴን ለማበርከት ችሏል፡፡ ሆኖም ግን የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ከምድብ ማጣሪያው ውጭ ከመሆን አደጋ ሳያተርፈው ቀርቷል፡፡
ኦገስት 2014
ሰርተርሊንግ የ2014/15 ሲዝንን የከፈተው በመጀመሪያዎቹ ሶት የፕሪሚየር ሊግ ግጥሚያዎቹ ሁለት ወሳኝ ጎሎችን በማስቆጠር የታጀበ ውጤታማ ፉትቦልን በማበርከት ነው፡፡ ጎሎቹን ከመረብ ያሳረፈው ሊቨርፑል ሳውዝ አምፕተንን በአንፊልድ 2ለ1 እና ቶተንሃምን በኋይት ኸርትሌን 3ለ0 በረታበት ጨዋታዎች ላይ ነው፡፡
ኦክቶበር 2014
የውድድር ዘመኑን በእያንዳንዱ የሊቨርፑል ግጥሚያዎች ላይ በመሰለፍ ከጀመረ በኋላ በእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ሁለት ግጥሚያዎች ለማጠናቀቅ የሚያስችለው ትንፋሽ እንደማይኖረው ለአሰልጣን ሮይ ሆጅሰን ነግሯቸዋል፡፡ በዚህም ሆጅሰን ከሳንማሪኖ ጋር በተደረገው ግጥሚያ ለ45 ደቂቃዎች እንዲሁም ኢስቶኒያን ሲገጥሙ በመጨረሻዎቹ 30 ደቂቃዎች ውስጥ ተጠቅመውበታል፡፡
ጃንዋሪ 2015
በውድድር ዘመኑ አጋማሽ ላይ የሊቨርፑሉ አሰልጣኝ ብሬንዳን ሮጀርስ ብዛት ያላቸውን ግጥሚያዎች ማድረጉን ከግንዛቤ በማስገባት የጥቂት ቀናቶች የእረፍት ጊዜውን ወደ ትውልድ አገሩ ጃማይካ በመሄድ ባሳለፈበት ወቅት የሊቨርፑል ሁለት ወሳኝ ግጥሚያዎች አምልጠውበታል፡፡
አፕሪል 2015
ስተርሊንግ ከቢቢሲ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ከሊቨርፑል የቀረበለት የተጨማሪ ዓመታት ኮንትራት ማራዘሚያ ውልን ለመቀበል መወሰኑን በይፋ አረጋግጧል፡፡ ሊቨርፑልን ለመልቀቅ ያሰበው ከገንዘብ ጥቅም ጋር በተያያዘ አለመሆኑን መግለጫውን ሰጥቷል፡፡
ሜይ 2015
የስተርሊንግ ወኪል ተጨዋቹ ከሊቨርፑል በቀረበለት የኮንትራት ማራዘሚያ ውል ዙሪያ መነጋገርን ጨርሶ እንደማይፈልግ ማጋገጫውን ሰጥቷል፡፡
ጁን 2015
ማንቸስተር ሲቲ ስተርሊንግን በ2ኛው ሙከራው በ40 ሚሊየን ፓውንድ ለመግዛት ያቀረበው ሂሳብ በሊቨርፑል ኃላፊዎች ውድቅ ሆኖበታል፡፡
ጁላይ 2015
ስተርሊንግ የሊቨርፑልን የፕሪ ሲዝን ዝግጅት ቢጀመርም ከቡድኑ ጋር ግን ለዝግጅት ወደ ሩቅ ምስራቅ ለመጓዝ ፈቃደኛ ሳይሆንለት ቀርቷል፡፡ በዛኑ ማግስት ማንቸስተር ሲቲ በሶስተኛው ጥሪው ባቀረበው 49 ሚሊየን ፓውንድ ሂብ በሊቨርፑል ኃላፊዎች ተቀባይነት አግኝቶለት ስተርሊንግን በእጁ አስገብቶታል፡፡
The post Sport: ራሂም ስተርሊንግ ‹‹በማንችስተር ሲቲ ስኬታማ እንደምሆን እርግጠኛ ነኝ›› appeared first on Zehabesha Amharic.