ሜሱት ኦዚል ከአርሰናል ጋር ማሳካት የሚፈልጋቸው ህልሞች እንዳሉ ይፋ አድርጓል፤ በቅርብ ጊዜ አርሰናልን መልቀቅ እንደማይፈልግ ያሳወቀው ኢዞል ዋንጫዎችን የማንሳት ህልም እንዳለው አረጋግጧል፡፡
በ2013 ሪያል ማድሪድን ለቅቆ ወደ አርሰናል ሲመጣ የወጣበት 42.5 ሚሊዮን ፓውንድ ትኩረትን የሳበው ኦዚል ዘንድሮ 18 ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን አቀብሎ ምርጥ እይታ ያለው ተጨዋች እንደሆነ አረጋግጧል፤ የ27 ዓመቱ ጀርመናዊ የኮንትራት ስምምነቱ በ2018 የሚጠበቅ መሆኑ ብዙዎች ከክለቡ ጋር እንደሚለያይ ሲያስቡ ቆይተዋል፡፡ ኦዚል ግን ይሄንን እያስተባበለ ነው፡፡
‹‹ይሄ የውድድር ዓመት ከተጠናቀቀ በኋላ ለተጨማሪ ሁለት ዓመታት በአርሰናል የሚያቆይ የኮንትራት ስምምነት አለኝ›› ይላል- ኦዚል፤ ጨምሮም ‹‹ከዚህ ቀደም ብዬ እንደተናገርኩት በአርሰናል ጥሩ ስሜት ይሰማኛል፡፡ ከክለቡ ጋር መቆየት እፈልጋለሁኝ፤ የቡድን ጓደኞቼ ጥሩ ናቸው- ከተማዋም ተስማምታኛለች፤ ያም ቢሆን በእግርኳስ እርግጠኛ መሆን በጣም ከባድ ነው፤ አሁን ባለው ሁኔታ በአርሰናል ፍፁም ደስተኛ ነኝ፡፡
‹‹የሁልጊዜም አላማዬ ግልፅ ነው- በዓለማችን ለሚገኙ ትልልቅ ክለቦች መጫወት እፈልጋለሁኝ፤ በቻምፒዮንስ ሊግ መሳተፍ እንዲሁም ዋንጫዎችን የማንሳት ፍላጎት አለኝ፤ ይሄንን ህልም እውን ለማድረግ ግን ሰፊ የተጨዋቾች ስብስብ ያስፈልገናል፤ ምክንያቱም ወሳኝ ሊባሉ የሚችሉ ተጨዋቾች ዓመቱን ሙሉ ጤነኛ ሆነው አይጫወቱም፣ ጉዳት እንደሚያስተናግዱ ግልፅ ነው፡፡›› ሲል ተናግሯል፡፡
በጀርመን ጋዜጦች ላይ አርሰናል ወደፊትም ቢሆን የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ያለው ዕድል ዝቅተኛ እንደሆነ መግለፁ ኢዚልን አላስደሰተውም፡፡ቢሆንም ተጨዋቹ በጋዜጦች ላይ የተነገረውን መረጃ አስተባብሎ በክረምቱ አዳዲስ ተጨዋቾችን በማስፈረም የፕሪሚየር ሊግ እና ቻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ላይ አሸናፊ ሊሆኑ እንደሚገባ ተናግሯል፡፡
‹‹ብዙ ነገሮች በትክክለኛው መንገድ ሊተገበሩ እንደሚገባ የተናገርኩት ለዚህ ነው፤ ቡድኑን ማገዝ እሻለሁኝ፣ አላማችን አርሰናል የሊጉን ዋንጫ እንዲያነሳ ማስቻል ነው፣ በግሌ ቡድኑ ህልሙን እውን እንዲያደርግ የምችለውን አስተዋፅኦ ማበርከት እፈልጋለሁኝ፣ እዚህ ህልምህን እውን ማድረግ ትችላለህ፡፡ ተጨማሪ ጥቂት ጥሩ አቅም ያላቸውን ተጨዋቾች ማስፈረም ከቻልን ህልማችን እውን ይሆናል›› ብሏል ኦዚል፡፡
ኦዚል ግላዊ ብቃቱን የማሻሻል ፍላጎት እንዳለውም አረጋግጧል፡፡ ዘንድሮ ሰባት ጎሎችን አስቆጥሮ 18 ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን ሰጥቶ ዓለምን ያስገረመው የዓለም ዋንጫ አሸናፊው ኮከብ፣ ‹‹አውቃለሁኝ ባለፉት ዓመታት በተለያዩ ክለቦች ጥሩ የምሆንባቸው የውድድር ዓመታት ጥቂት የሚባሉ ናቸው፤ በአርሰናል ዘንድሮ ጥሩ ጊዜ እያሳለፍኩኝ እንደሆነ ይሰማኛል፣ ነገር ግን በግላዊ ስኬቴ የመኩራራት ስሜት አይሰማኝም›› የሚል አስተያየትን ሰጥቶ፣ ‹‹በየጊዜው ራሴን ማሻሻል እፈልጋለሁኝ፤ ከዚህ የተሻለ ነገር ማድረግ እና ቡድኑን መጥቀም እንዳለብኝ ይሰማኛል፤ በመጪዎቹ ዓመታት ይሄንን ህልሜን እውን ማድረግ እሻለሁኝ፣ ያም ቢሆን ጥሩ የውድድር ዘመን ማሳለፌ መረሳት የለበትም፡፡ ሁልጊዜም ቢሆን መጪውን ዘመን አሻግሬ መመልከትን እመርጣለሁኝ፣ ዘንድሮ ደግሞ ጥሩ አቋም ሳሳይ ቆይቻለሁኝ›› በማለት ብቃቱ ጥሩ ቢሆንም እንደማይኩራራ አረጋግጧል፡፡