(ዘ-ሐበሻ) ከቸልሲ ጋር 703 ጨዋታዎችን ያደረገው አንጋፋው ተከላካይ ጆን ቴሪ በስታንፎርድ ብሪጅ የሚያቆየው ኮንትራት የሚጠናቀቀው በዚህ ሲዝን መጨረሻ ላይ ሲሆን ክለቡ ተጫዋቹ ለአንድ ዓመት ያህል እንዲቆይለት ጥሪ ማቅረቡን የ እንግሊዝ ጋዜጦች ዛሬ ዘግበዋል::
እንደዘገባዎች ከሆነ የ35 ዓመቱ ጎልማሳ ጆን ቴሪ በክፍተኛ ገንዘብ ክፍያ ለቻይና ክለብ ሄዶ በሚቀጥለው ሲዝን ይጫወታል ተብሎ እየተጠበቀ ሲሆን በቸልሲ ለቀረበለት የ አንድ አመት ኮንትራት ማራዘሚያ ለ እርሱና ለቤተሰቡ ትልቅ ውሳኔ ይሆናል ተብሏል::
ቸልሲን ከጆሴ ሞሪንሆ ተረክበው በጊዜያዊነት ያሰለጠኑት ጉስ ሂዲኒክ በሚቀጥለው ዓመት ክለቡን ከሚይዙት ጣሊያናዊው አንቶኒዮ ኮንቴ ጋር ከተወያዩ በኋላ በክለቡ ውስጥ ትላልቅ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች እንዲኖሯቸው ይፈልጋሉ:: በዚህም የተነሳ ጣሊያናዊው ኮንቴ ጆን ቴሪን በቀጣዩ ሲዝን ከክለባቸው ማጣት እንደማይፈጉ ጋዜጦቹ ዘግበዋል::
ጆን ቴሪ ቸልሲ በፕሪምየር ሊጉ በስታንፎርድ ብሪጅ ከሌስተር ሲቲ ጋር በሚያደርገው ጨዋታ በቅጣት ምክንያት አይሰለፍም:: ቸልሲን ለመልቀቅ ከወሰነም ከደጋፊው ጋር ዳግም ላይገናኝ ይችላል::