ስሜነህ ታደሰ | ለዘ-ሐበሻ ስፖርት
(ዘ-ሐበሻ) ሊጀመር 77 ቀናት የቀሩት አጓጊው የብራዚሉ ኦሎምፒክ ሃገራት የሚወክሏቸውን አትሌቶች በማሳወቅ ላይ ይገኛሉ:: ኢትዮያም ባለፈው ሳምንት በአጭር ርቀት ሩጫዎች የሚወክሏትን አትሌቶች አሳውቃ የነበረ ሲሆን የማራቶን ወኪሎቿን እስካሁን ስታሳውቅ ቀርታ ነበር::
ዘ-ሐበሻ ከዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ድረገጽ እንዳገኘችው መረጃ ከሆነ በሪዮ ኦሎምፒክ በማራቶን ኢትዮጵያን ከሚወክሉት ታላላቅ አትሌቶች መካከል የዓለም ሻምፒዮኗ ማሬ ዲባባ እንደምትገኝበት ታውቋል::
ማሬ ዲባባ ኦገስት 30, 2015 በቤጂንግ ቻይና በተደረገው 15ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ2:27:35 በመግባት አሸናፊ መሆኗ ይታወሳል::
ኦክቶበር 20, 1989 የተወለደችው ማሬ የማራቶን ቡድናችን መሪ ትሆናለች::
በወንዶች ተስፋዬ አበራ; ለሚ ብርሃኑ እና ፈይሳ ላሊሳ ሲመረጡ በተጠባባቂነት ቀነኒሳ በቀለ; አድሃነ የማነና ለሊሳ ዲሳሳ በማራቶን እንዲወክሉ ተመርጠዋል::
በሴቶች ማራቶን ማሬ ዲባባ; አበሩ ከበደና አሰለፈች መርጊያ ሲመረጡ በተጠባባቂነት ት ዕግስት ቱፋ እና ትርፌ ጸጋዬ ተመርጠዋል::
በሬዮው ኦሎምፒክ 206 ሃገራት ሲሳተፉ 42 ዓይነት ስፖርቶች ይካሄዳሉ::
ብራዚል ይህንታላቁን ኦሎምፒክ ለማዘጋጀት 37 የስፖርት ማከናወኛዎችን ገምብታለች::
መልካም ዕድል ለአትሌቶቻችን::