አሰልጣኝ ካርሎ አንቼሎቲ እጅግ በጣም የተከበሩ ባለሙያ ናቸው፡፡ ፍፁም የተረጋጋ ባህሪይ ያላቸው ካርሎ በጣልያን፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ እና ስፔን ቆይታቸው ስኬታማ ከመሆናቸውም ባሻገር ብዙዎች ፍፁም ያከብሯቸዋል፡፡
ያም ቢሆን ከጣልያን እና ፈረንሳይ ውጭ የሚገባቸውን ክብር አላገኙም፤ ስኬታማ ቢሆኑም ለስንብት ይዳርጋሉ፡፡ በቼልሲ ሳሉ የገጠማቸውን ስንብት ማን ይረሳል?
አሰልጣኙ በቅርቡ ለንባብ ባበቁት መጽሐፋቸው ላይ ይፋ ያደረጉት መረጃ አስገራሚ ነበር፡፡ በ2011 በቻምፒዮንስ ሊጉ ሩብ ፍፃሜ ቼልሲ ከማንችስተር ዩናይትድ ጋር ከመጫወቱ በፊት ጣልያናዊው አሰልጣኝ በሮማን አብራሞቪች አንድ ትዕዛዝ ተሰጣቸው፡፡ ‹‹ሽንፈት የምታስተናግድ ከሆነ በድጋሚ ቼልሲን ስለማሰልጠን እንዳታስብ›› የሚል፡፡
‹‹በደርሶ መልስ ተሸንፈን ወጣን፣ በድጋሚ ወደ ሥራ ስሄድ በድን የመሆን ስኬት ተሰምቶኝ ነበር›› የሚል መረጃን የሚሰጡት ካርሎ፣ ‹‹በግሌ ከሮማን ጋር እጋጫለሁኝ የሚል ስሜት ነበረኝ፤ ሆኖም የተፈጠረው አጋጣሚ ትርጉም የሚሰጥ አልነበረም›› ይላሉ፡፡
በተጨዋችነት ሁለት ጊዜ እንዲሁም በአሰልጣኝነት ሶስት ጊዜ የቻምፒዮንስ ሊጉን ዋንጫ ያነሱት አንቾሎቲ፣ ባለፉት 12 ወራት እረፍት ማድረጋቸው እንደጠቀማቸው ያስረዳሉ፡፡ ግለሰቡ ከቼልሲ ጋር ከተለያዩም በኋላ በስኬት ቀጥለዋል፤ ከፓሪስን ዠርሚ ጋር የፈረንሳይ ሊግ 1 ዋንጫ ያነሱት አሰልጣኝ ሪያል ማድሪድን ከ10ኛ የቻምፒዮንስ ሊግ ህልሙ ጋር አገናኝተውታል፤ አሁን ደግሞ ባየር ሙኒክን ሲረከቡ የጀርመኑ ክለብ ስምንተኛ ክለባቸው ይሆናል፡፡
አንቼሎቲ ስኬት የሚያስመዘግቡት መንገድ በተረጋጋ መንፈስ የተሞላ ነው፡፡ ሌሎችን አክብረው ራሳቸውንም አስከብረው ስኬትን ያስመዘግባሉ፤ ከአይብ አምራች ገበሬ ቤተሰብ የተገኙት ጣለያናዊው በዝምታ ውስጥ ሆነው መጓዝ ያስደስታቸዋል፡፡ ለተጨዋቾቻቸው የተመቹ ናቸው፣ ሪያል ማድሪድን ሲለቅቁ እንኳን ተጨዋቾቻቸው ደስተኛ አልነበሩም፤ ኧረ እንዲያውም ‹‹ለምን ይለቅቃሉ?›› ብለው ተቃውሞ አስነስተዋል፡፡
የውድድር ዓመቱን እረፍት ላይ የነበሩትን አንቼሎቲ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት አልተቸገሩም፡፡ ስለ ፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊው ክለብ ሌይስተር ሲቲ ስትጠይቋቸው ‹‹አሰልጣኝ (ክላውዲዮ) ሪኒዬሪ የማይታመን ስራ ሰርቷል›› የሚል መልስ ይሰጣሉ፡፡
የሊጉን ዋንጫ ማንሳት የሚፈጥረውን አስደሳች ስሜት ጠንቅቀው የሚያውቁት ጣልያናዊው አሰልጣኝ ይሄንን ክብር በማሳካት ሶስተኛው ጣልያናዊው ሆነዋል፤ እርሳቸው ግን በአንድ ዓመት የጥምረት ድል ባለቤት በመሆን ሌላ ታሪክ አስመዝግበዋል፡፡
የቀጣዩ ዓመት ፕሪሚየር ሊግ ከወዲሁ አጓጊ ሆኗል፡፡ በርካታ ታላላቅ አሰልጣኞች ወደ ሊጉ ማምራታቸው ይበልጥ አለማቀፋዊ ትኩረት ስቧል፡፡ በባርሴሎና እና ባየርን ሙኒክ ስድስት የሊግ ዋንጫ እንዲሁም ሁለት የቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎን ያነሳው ፔፕ ጋርዲዮላ ማንችስተር ሲቲን ተረክቧል፡፡ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ውበት የሆኑት ጆዜ ሞውሪንሆም ወደ ማንቸስተር ዩናይትድ አምርተዋል፡፡ የሁለቱ የማንችስተር ከተማ ክለቦች የእርስ በርስ ግንኙነት ከወዲሁ ተጠባቂ ሆኗል፡፡
ብዙዎች ከአሰልጣኝ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ስንብት በኋላ ትክክለኛ ተተኪው አንቾሎቲ እንደሆነ ይናገራሉ፤ እርሳቸው ይሄንን በተመለከተ ምን አይነት አስተያየት ይኖራቸው ይሆን?
‹‹(በ2013) ሪያል ማድሪድን ከመረከቤ በፊት ከፈርጉሰን ጋር ተነጋግረን የነበረ ቢሆንም ቅድሚያ ቃል በመግባቴ ወደ ስፔን መሄድ ነበረብኝ ሪያል ማድሪድን ከለቀቅኩኝ በኋላ ከማንም ጋር አልተወያየሁም፣ ስፔን ካገኘሁት ተሞክሮ በመነሳት ወደ እንግሊዝ ብመለስ ደስተኛ እሆን ነበር፡፡ ነገር ግን ባየርን ሙኒክን ለማሰልጠን ዕድል ማግኘቴ አስደስቶኛል፡፡›› ይላሉ ጣልያናዊው አሰልጣኝ፡፡
በዚህ ወቅት የእንግሊዝን እግርኳስ አስመልክቶ የውይይት ርዕስ የሆነው የአሰልጣኝ ጆዜ ሞውሪንሆ ማንችቸስተር ዩናይትድን መረከብ ነው፡፡ ጆዜ እና ካርሎ ቼልሲ እና ሪያል ማድሪድን በማሰልጠን አሳልፈዋል፤ በ2008/09 የውድድር ዘመን ሁለቱን የሚላን ክለቦች በማሰልጠን ተፎካካሪ መሆን ችለዋል፡፡
ካርሎ በ2009/10 የውድድር ዘመን የፕሪሚየር ሊግ እና ኤፍኤ ካፕ ዋንጫዎችን በማንሳት የጥምር ድል ባለቤት መሆን ቢችሉም ቼልሲ በቻምፒዮንስ ሊግ በኢንተር ሚላን ያስተናገደው ሽንፈት የአሰልጣኙ መጨረሻ መጀመሪያ ነበር፡፡
‹‹ሞውሪንሆ ፕሪሚየር ሊጉን ጠንቅቆ የሚያውቅ በመሆኑ (ከዩናይትድ ጋር) ሁለቱ የፈጠሩት ጥምረት ጥሩ ጋብቻ የመፈፀም ያህል ነው›› የሚል አስተያየትን የሚሰጡት የቀድሞው የሪያል ማድሪድ አሰልጣኝ፣ ‹‹ከዓለማችን ምርጥ አሰልጣኞች መሀከል አንዱ እንደሆነ ሁሉም ይስማማል፣ ክለቡ በአሁኑ ሰዓት የሚያስፈልገው ባለፉት ሁለት ዓመታት በአሰልጣኝ ሉዊስ ቫን ሃል የነበረውን ነገር ይበልጥ ማሻሻል የሚችል ነው›› ሲሊ ተናግረዋል፡፡
‹‹በቫን ሃል ያለፉት ሁለት ዓመታት ቆይታ ጥያቄዎች ይነሳሉ?››
‹‹በጭራሽ፣ በግሌ አሰልጣኙ ስኬታማ አልሆነም በሚለው ሃሳብ አልስማማም፣ ክለቡ ሪዮ ፈርንዲናንድ፣ (ፖል) ስኮልስ፣ (ራያን) ጊግስን ካጣ በኋላ አዲስ ቡድን በድጋሚ መገንባት ነበረበት፡፡ በኤሲ ሚላን የሆነውም ነገር ተመሳሳይነት አለው፡፡ ሚላን (ፓውሎ) ማልዲኒ፣ (ጄናሮ) ታቱሶ እና (ፊሊፕ) ኢንዛጊን ካጣ በኋላ በድጋሚ ለማገገም ተቸግሯል፤ የቡድን ግንባታ ቀላል አይደለም፡፡ ጊዜ ያስፈልጋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ዩናይትድ ጥሩ አቅም ያላቸውን ተጨዋቾች ይዟል፤ ምናልባት ባለፉት ሁለት ዓመታት ከዚህ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ነበረበት›› በማለት ዩናይትድ ከፈርጉሰን ስንብት በኋላ የሚገባውን ክብር እንዳላገኘ ገልፀዋል፡፡
‹‹ምናልባት በማንችስተር ዩናይትድ ያለው ጫና ከፍተኛ መሆን ከስኮትላንዳዊው አሰልጣኝ ስንብት በኋላ ይበልጥ ከፍ ብሎ ይሆን?›› ጥያቄው ሲነሳባቸው የሳቁት ካርሎ ‹‹እንዴ! ምን እያላችሁ ነው?! በማንችስተር ሲቲ ጫና የለም እንዴ? የትም ብትሄዱ ጫናው ከፍተኛ ነው፤ ስራው በራሱ ከባድ ቢሆንም ጥልቅ የሆነ ውስጣዊ ፍቅር ይኖራል፤ ከሞውሪንሆ ጋር ጥሩ ግንኙነት አለኝ፤ (ከዚህ ቀደም) በጋዜጦች ጉዳይ በጥልቀት ተወያይተናል፤ ሆኖም አሁንም ያለን ግንኙነት ጥሩ ነው፤ በየዕለቱ ባንወያይም የፅፍ መልዕክት እንለዋወጣለን›› የሚል አስተያየትን ሰጥተዋል፡፡
አንቼሎቲ ባሰለጠኗቸው ክለቦች ውስጥ ከአለቆቻቸው ሲልቪዮ ቤርሎስኪኒ፣ ቫያኒ አኜሌ፣ አብራሞቪች፣ በናስር ኤል ክህላፊ እና ፊዮሬንቲኖ ፔሬዝ ጋር አልፎ አልፎ የሚፈጠሩ ችግሮች ነበሩ፡፡
በ2012 የምድብ ማጣሪያ ፓራሰን ዠርመ ከፓርቶ ጋር ከመጫወቱ በፊት ጨዋታውን በድል የማይወጣ ከሆነ አሰልጣኙ ለስንብት ሊዳረጉ እንደሚችሉ ተነግሯቸው ነበር፤ አስገራሚ ነገር ካርሎ ይሄ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ክለቡ ከምድብ ማጣሪያው ማለፉን ካረጋገጠ በኋላ ነው፡፡
የአሰልጣኙ ብቃት ተጨዋቾችን ለስኬት ከማብቃት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ተጨዋቻቸውን የሚያስተባብሩበት መንገድ በጣም ይገርማል- ከትልልቅ ተጨዋቾች ጋር ተግባብቶ የመስራት ችግር የለባቸውም፤ በአሰልጣኝነት ዘመናቸው ‹‹ዘላታን ኢብቭራሂሞቪች፤ ክርስቲያኖ ሮናልዶ፣ ዴቪድ ቤካም፣ ቴሪ እና ማልዲኒን አሰልጥነው ታሪክ ሊዘነጋው የማይችል ስኬት መዝግበዋል፡፡
‹‹አውቃለሁኝ ጥሩ ውጤት ካስመዘገብኩኝ (ከአለቆቼ ጋር) ያለኝ ግንኙነት ጥሩ ይሆናል›› የሚል አስተያየትን ሰጥተው፣ ‹‹በአንፃሩ ውጤት ከጠፋ በክለቡ ባለቤቶች እና እኔ መሀከል አለመግባባት ይፈጠራል፣ በግሌ ከባለቤቶቹ ጋር ያለኝ ግንኙነት ያን ያህል ወሳኝ አይደለም፤ ለሁሉም አክብሮት ቢኖረኝም ትኩረቴ በቡድኔ ላይ ያርፋል›› ይላሉ፡፡
አንቾሎቲ በመጽፋቸው ላይ ኢብራሂሞቪች ብዙ ከታች የሚያድጉ ተጨዋቾች ላይ ይፈጥር የነበረው ተፅዕኖ አብራርተዋል፤ አንዳንድ ወጣት ተጨዋቾች ብቃታቸው ጥሩ ካልሆነ ስዊድናዊው ቁጣን ቀላቅሎ ‹‹አሁኑኑ ወደ ቤት ሄደህ ከዝላታን ጋር ልምምድ ሰርቻለሁኝ የሚል ማስታወሻ ያዝ፣ ምክንያቱም ይሄ እዚህ የምትሆንበት የመጨረሻህ ነው›› ይላቸው ነበር፡፡
ይሄንን ከግምት አስገብታችሁ የኢብራሂሞቪች ዝውውር በማንችስተር ዩናይትድ ‹‹ወጣት ተጨዋቾች ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ የለም?›› የሚል ጥያቄን ስታነሱ ‹‹… (ኢብራሂሞቪች) ወጣት ባይሆንም ብቁ ሆኖ እየተጫወተ ይገኛል፤ እውነተኛ የአሸናፊነት አዕምሮ (ስነ ልቦና) ይዟል፤ ምናልባት ማንቸስተር ዩናይትድ ጥሩ ልምድ ያለው ተጨዋች እንዳገኝ ይሰማኛል፤ በፓራሰን ዠርመ ብዙ ከታች ያደጉ ተጨዋቾች ነበሩ፡፡ በወቅቱ (አንድ ከታች ያደገ ወጣት ተጨዋች) እንዲህ አይባልም፡፡ ለሌሎች አርአያ መሆን አለብህ፤ ለወጣት ተጨዋቾች በራስ የመተማመን ስሜት እንዲያጎለብቱ ማድረግ አለብህ፡፡ ከታች የሚመጡ ተጨዋቾች ከዋናው ቡድን ሲጫወቱ በራስ የመተማመን ስሜታቸው አነስተኛ እንደሆነ መታወቅ አለበት፤ ለኢብራሂሞቪች እና ቲያጎ ሲልቫ ያላቸው አክብሮታዊ ፍርሃት መጠኑን ያለፈ ነበር፤ ይሄ ደግሞ ምቾት አይሰጣቸውም፤ ዝላታን ራስ ወዳድ አይደለም፤ ወደ ክለቡ ከመጣ በኋላ የማሸነፍ ስነ ልቦና አስረዋል፤ ጎል እንደሚያስቆጥር እርግጠኛ ሆኖ ይናገራል፤ በዚህ ባህሪዪው አርአያ በመሆን በክለቡ ውስጥ የራስ የመተማመን ስሜት እንዲኖር አስችሏል፡፡ ፓራስን ዠርመ ለስኬቱ ክብር መስጠት ካለበት ዝላታን ቀዳሚው ነው›› የሚል ምላሽ ይሰጣሉ፡፡
በባርየን ሙኒክ አንቾሎቲ የሚጠብቃቸው ፈተና ቀላል አይደለም፡፡ ከዩፕ ሄይንከስ ስንብት በኋላ ፔል ጋርዲዮላን ክለቡን ለሶስት ተከታታይ ዓመታት ለቡንደስሊጋ ድል ቢያበቃም የቻምፒዮንስ ሊግ ጉዞ ከግማሽ ፍፃሜ ባለማለፉ ፈተናው ቀላል አይሆንም፡፡ በፓራሰን ዠርመ እና ቼልሲ መጠነኛ ለውጥ ያደረጉት አሰልጣኝ አንፃራዊ ስኬት ያስመዘገበብትን አካሄድ ይከተላሉ ብሎ መጠበቅ ተገቢ ነው፡፡
‹‹ሁሉም አሰልጣኝ የራሱ የሆነ የስልጠና መንገድ አለው፤ ጋርዲዮላ (በሲቲ) የሚከተለው የራሱን መንገድ ነው›› የሚል አስተያየትን የሚሰጡት አንቾሎቲ ናቸው፤ ‹‹ባርሴሎናን ለቅቆ ወደ ባየርን ሙኒክ ሲያመራ ሰዎች ሊዮኔል ሜሲን ባለመያዙ በአዲሱ ክለቡ ተመሳሳይ ስኬት ማስመዝገብ አይችልም ብለው ነበር፤ ነገር ግን በባየርን ሙኒክ የፈጠረው የአጨዋወት ዘይቤ ከባርሴሎና ጋር ተመሳሳይነት ነበረው፤ ተጨዋቾቹ የተለያዩ ቢሆኑም የአጨዋወት ዘይቤው ግን ተመሳሳይነት አለው፤ በቀጣይ በማንቸስተር ሲቲ ተመሳሳይ ነገሮችን መመልከታችን አይቀርም፡፡
‹‹ጋርዲዮላ የራሱን አሻራ እና ማንነት የሚያሳርፍ ቡድን መገንባት በመቻሉ ልናወድሰው ይገባል፤ ወደ ቼልሲ ሳመራ በማንቸስተር ዩናይትድ ወይም ሪያል ማድሪድ ደረጃ የራሳቸው የሆነ ነገር ነበራቸው፡፡ የእነኚህን ክለቦች ባህል እና ልማድ መቀየር አይቻልም፤ የራስህን አስተሳሰብ እና የአጨዋወት ዘይቤ ማምጣት ይጠብቅሃል፡፡
‹‹ማንቸስተር ሲቲ ጋርዲዮላን ሲያስፈርሙ የራሱ የሆነ ማንነት፣ አዲስ ዘይቤ እና አዲስ ባህል ይዞ እንደሚመጣ ተገንዝቧል ሲቲ አንድ ዩናይትድ እና አርሰናል አይደለም፤ ገና ወደ ስኬት ማማ እየወጣ ያለ ክለብ ነው፡፡
ሌላው የአንቼሎቲ መለያ ስኬታማ መሆን የተሳናቸውን አሰልጣኞች በመተካት የሚያስመዘግቡት ስኬት ነው፤ በቼልሲ ስኬታማ ጊዜ ሲያሳልፉ የተኩት ጉስ ሃዲንክን ነበር፤ በሪያል ማድሪድ የቻምፒዮንስ ሊጉን ዋንጫ ሲያነሱ ሞውሪንሆ ያሳለፉት ጊዜ ይታወቃል፡፡
‹‹ወደ ባየርን ሙኒክ የመራሁት ጋርዲዮላ ስኬታማ መሆን ስላልቻለ አይደለም፤ እርሱ በባየርን ሙኒክ ስኬታማ ጊዜያትን አሳልፏል፤ ክለቡ አሰልጣኝ መለወጥ ያስፈልገው ፔፕ የክለብ ለውጥ ማድረግ ስለፈለገ ነው፤ የእኔም ነገር የተለወጠ አይደለም፤ እዚያ የምሄደው ስኬት ለማምጣት እንደሆነ መታወቅ አለበት›› ይላሉ ትሁቱ አሰልጣኝ፡፡
ከኤሲ ሚላን ጋር በተጫዋችነት ዘመናቸው በ1980 እና 1990 የቻምፒዮንስ ሊጉን ዋንጫ ካነሱ በኋላ ያልተደፈረ ሪከርድ የያዙት ካርሎ በአሰልጣኝነት አራተኛውን የቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ለማንሳት መፋለማቸው ጥርጥር የለውም፡፡
በተጫዋችነት ዘመናቸው በ1982 ከጣልያን ብሔራዊ ቡድን ጋር የዓለም ዋንጫ የማንሳት ዕድል ነበራቸው፤ የጉልበት ጉዳት ከፊታቸው ተጋርጦ ህልማቸውን እውን እንዳያደርጉ አገዳቸው እንጂ፡፡ በ1984 ሮማ ክሊቨርፑል ጋር ባደረገው የቻምፒዮንስ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ ተሰልፈውም ነበር፡፡ የዓለም ዋንጫ አለማንሳታቸው ይረብሻቸው ይሆን? ‹‹በጭራሽ፣ ዕድለኛ አልነበርኩም ብዬ አላስብም፤ ያገኘሁት ይበቃኛል›› ይላሉ፡፡