Quantcast
Channel: ስፖርት | ዘ-ሐበሻ (ZeHabesha) - Latest Ethiopian News Provider
Viewing all articles
Browse latest Browse all 419

ጆዜ ሞውሪንሆ ተናገሩ –‹‹ማንችስተር ዩናይትድን ወደ ስኬታማነት ባህሉ እመልሰዋለሁ››

$
0
0

የዛሬ ሶስት ዓመት ገደማ በብሪትሽ ፉትቦል ታሪክ እጅግ ዝነኛው አሰልጣኝ የሆኑት ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ከሙያቸው ሲገለሉ ማንችስተር ዩናይትድ በምትካቸው ጆዜ ሞውሪንሆን የመቅጠር መልካም አጋጣሚ ተፈጥሮለት ነበር፡፡ ምክንያቱም በዛን ወቅት ፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ ለሶስት ዓመታት ከዘለቁበት የሪያል ማድሪድ ዋና አሰልጣኝነታቸው በመልቀቅ ካለ ስራ ተቀምጠው ነበር፡፡ ያኔ የማንችስተር ዩናይትድ ኃላፊዎች ሞውሪንሆን ለመቅጠር ያልቻሉበት ትክክለኛው ምክንያት ግን ሰሞኑን የ53 ዓመት ፖርቹጋላዊ አሰልጣኝ የኦልድ ትራፎርድ ስራን ከተረከቡ በኋላ በይፋ ተረጋግጧል፡፡
Jose Manchester united
እንደ ማንችስተር ዩናይትድ ከፍተኛ ባለስልጣን ኤድዋርድ ውድዋርድ መግለጫ በሜይ 2013 ክለባቸው ከሞውሪንሆ ይልቅ ዴቪድ ሞዬስን በዋና አሰልጣኝነት ከመቅጠሩ በፊት በቅድሚያ ያነጋገረው ፖርቹጋላዊውን አሰልጣኝ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ከሞውሪንሆ የተሰጣቸው ምላሽ ‹‹በቼልሲ ገና ያልጨረስኩት የቤት ሥራ አለኝ›› የሚል ሆኗል፡፡ ‹‹ሞውሪንሆ ለ2ኛ ጊዜ የቼልሲ ስራን መያዝን ምርጫቸው ካደረጉበት ከዛ ጊዜ በፊት ሶስት ዓመታት ማንችስተር ዩናይትድ ካለዋንጫ ሽልማት የዘለቀበት ሁኔታን ለመቀየር የቻለው የዘንድሮው የኤፍ.ኤ.ካፕ ድልን በመቀዳጀት ነው፡፡

ይህ ግን ለሆላንዳዊው አሰልጣኝ ሉዊ ቫንሃል በስራው ለመዝለቅ በቂ ውጤት ሳይሆንላቸው በመቅረቱ ሲፈላለጉ የዘለቁት ጆሴ ሞውሪኖና የኦልድትራፎርድ ስራ አመራሮች በመጨረሻም ተገናኝተዋል፡፡ ከዚህ በፊት ቼልሲን በሶስት የፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮንነት ክብሮች የመሩት ሞውሪንሆ ለአራት ዓመታት በሚዘልቅ የኮንትራት ውል የኦልድትራፎርድ ስራን ከተረከቡ በኋላ በሰጡት ይፋዊ መግለጫም ‹‹ የማንችስተር ዩናይትድ ስራን በእስካሁኑ የሙያ ዘመኔ በትልቅነቱ አቻ የማላገኝለት የኃላፊነት ቦታ ነው› በማለት ከመግለፅም አልፈው የክለቡ ደጋፊዎች ባለፉት ሶስት ዓመታት በቡድናቸው ላይ የተፈጠረው በርካታ ውጣ ውረዶችን ከአዕምሯቸው እንዲያስወጡት እንደሚረዳቸውና ከቀጣዩ የውድድር ወቅት አንስቶ የዋንጫ ሽልማቶችንና የሻምፒዮንነት ክብሮች ዳግም ወደለመዱበት ቦታ ኦልድ ትራፎርድ እንዲመለስ የሚያስችሉበት ስኬታማ ተግባርን እንደሚፅሙላቸው ቃል ገብተውላቸዋል፡፡ ሞውሪንሆ የማንችስተር ዩናይትድ ስራን የያዙት በአንድ ዓመት ከክለቡ 15 ሚሊዮን ፓውንድ ደመወዝ እንዲሰጣቸው በመስማማት በመሆኑም በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ከፍተኛው ተከፋይ መሆናቸው ከወዲሁ በይፋ የተረጋገጠ ሆኗል፡፡

የማንችስተር ዩናይትድ የተጨዋቾች ዝውውር ውሎችን በበላይነት የሚመሩት ውድዋርድ ‹‹በአሁኑ ወቅት በዓለም ፉትቦል እጅግ ምርጡ ባለሙያ›› በማለት ለገለጿቸው ሞውሪኖ በአሁኑ የዝውውር መስኮት ለአዳዲስ ተጨዋቾች ግዥ 200 ሚሊዮን ፓውንድ በጀትን ክለባቸው እንደፈቀደላቸውም ማረጋገጫቸውን ሰጥተዋል፡፡ ፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ በባህላቸው ለአዳዲስ ተጨዋቾች ግዥ ሰፊ በጀት የሚፈቅዱላቸው ክለቡን ምርጫቸው የሚያደርጉ መሆናቸው ከግንዛቤ ሲገባም ለአራት ዓመታት በሚዘልቀው የኦልድትራፎርድ የስራ ዘመናቸው ስኬታማ ተግባሮችን ለመፈፀም የሚችሉበት የተመቻቸ ሁኔታ እንደሚፈጠርላቸው እርግጠኛ ሆኖ ለመናገር ይቻላል፡፡

ይህንን በማመንም ሞውሪንሆ በዋና አሰልጣኝነት መሾማቸውን ተከትሎ ከማንችስተር ዩናይትድ ድረ-ገፅ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የኦልድትራፎርድ ስራን ከሚጀምሩበት ገና ከመጀመሪያው ዓመት አንስቶ ‹‹ማንችስተር ዩናይትድ በየዓመቱ የዋንጫ ሽልማትን ወደማግኘት ባህሉ እመልሰዋለሁ›› በማለት በውስጣቸው ያለውን ከፍተኛ የሆነ የራስ የመተማመን መንፈስን አንፀባርቀዋል፡፡

በመቀጠልም ‹‹የማንቸስተር ዩናይትድ ስራን መረከብ መቻል እኔ በግሌ አቻ የማላገኝለትን ትልቅ ክብር እንደተፈጠረልኝ የምቆጥረው ሆኖልኛል፡፡ ምክንያቱም የማንችስተር ዩናይትድ በመላው ዓለም ሰፊ ዝናና ከፍተኛ የሆነ ደጋፊዎችን በመያዝ ከማንኛውም ክለብ ጋር የሚነፃፀር አይደለም፡፡ በየትኛውም የዓለማችን ክፍል ማንቸስተር ዩናይትድ የሚለው ስም የሚነሳው ከመልካም ጎን ጋር በተያያዘ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር በስፖርት ዓለም ትልቁ ክለብ በሆነው በዚህ ስራ ምን አይነት ኃላፊነትን መፈፀም እንዳለብኝ ለማወቅ አስቸጋሪ አልሆነብኝም፡፡

ከወዲሁ ግን ለዚህ ክለብ ተወዳጅ ደጋፊዎች ቃል የምገባላቸው የማንችስተር ዩናይትድ የስኬታማነት ባህል በእኔ የሥራ ዘመን ሙሉ ለሙሉ ወደነበረበት ቦታ ለመመለስ ይችላል በሚል ነው፡፡ እኔ በግልም በኦልድትራፎርድ ስቴዲየም መጫወት አቻ የማላገኝለት ትልቅ የምስራች ሲፈጠርልኝ የዘለቀ ጉዳይ ነው፡፡ በኦልድ ትራፎርድ የተደረጉት ግጥሚያዎች በርካታ አስደሳች ውጤቶችን አስመዘግቤያለሁ፡፡ አሁን ደግሞ ማንቸስተር ዩናይትድን በዋና አሰልጣኝነት በመምራት በዚህ ተወዳጅ ሜዳ በየሳምንቱ ግጥሚያዎችን ለማድረግ የምችልበት አስደሳች አጋጣሚ ተፈጥሮልኛል፡፡

ከዚህ አንፃር ማንችስተር ዩናይትድን በመምራት የመጀመሪያው ግጥሚያ በኦልድትራፎርድ ለማድረግ ከወዲሁ ከፍተኛ የሆነ ጉጉትን ማሳደር መቻሉን ለማረጋገጥ እወዳለሁ›› የሚል አስተያየታቸውን አክለዋል፡፡

አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ሞውሪንሆ ለማንችስተር ዩናይትድ በማጥቃት ላይ ያተኮረ የጨዋታ ሲስተም ባህልን የማይመጥን ባለሙያ ናቸው የሚል ስጋትን በማሳደር ለኦልድትራፎርድን ስራ ትክክለኛው ባለሙያ መሆናቸውን ቢጠራጠሩትም በተግባር የታየው ሁኔታ መረዳት የተቻለው ግን የማንችስተር ዩናይትድ ኃላፊዎች ሞውሪንሆን ለመቅጠር ለበርካታ ወራት ከፍተኛ ጉጉትን አሳድረው መዝለቃቸው ነው፡፡ በተለይም ዴይሊ ሜይል ጋዜጣ የክለቡ ውስጥ አዋቂዎችን በመጥቀስ ሰሞኑን ይፋ ባደረገው መረጃ ፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ ባለፈው ዲሴምበር ወር ከቼልሲ ስራ ከተነሱ ጊዜ አንስቶ ማንችስተር ዩናይትድ የሌላ ክለብ ስራን ለማግኘት መነጋገር እንዳይጀምሩ ከ4 ሚሊየን ፓውንድ ያላነሰ የቦነስ ክፍያን ለሞውሪንሆ ሰጥቷቸዋል፡፡ ይህ ምን ያል በጥብቅ ሲፈለጉ የዘለቁ ሁለቱ ወገኖች ያገናኘ የአሰልጣኝነት ቅጥር ውል በኦልድትራፎርድ ተፈፃሚ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 419

Trending Articles