ሊሊ ሞገስ | ለዘ-ሐበሻ ስፖርት
ማንችስተር ዩናይትድ በቅርቡ ያስፈረመው ሄንሪክ ምክሂታርያን በእግርኳስ ተጨዋችነት ዘመኑ የተለያዩ ቦታዎች ላይ ተጫውቶ አሳልፏል፡፡ አሰልጣኝ ጆዜ ሞውሪንሆ ለሚከተሉት ታክቲክ አርሜንያዊውን የአማካይ አጥቂ በፈለጉበት ቦታ ለመጫወት የሚያስችል ዕድል አግኝተዋል፡፡
የማንችስተር ዩናይትድ ደጋፊዎችም ባለፉት ሶስት ዓመታት ከቦሩሲያ ዶርትሙንድ ጋር ስኬታማ ጊዜያትን ያሳለፈውን ተጨዋች ለመመልከት ጓጉተዋል፡፡ ጆዜ በአመዛኙ በ4-2-3-1 ፎርሜሽን የሚጫወቱ በመሆናቸው ሄንሪክ በየትኛውም ቦታ ላይ መጫወት የሚያስችል ዕድል ይፈጠርለታል፡፡ በሲግናል ኤዱና ፓርክ ከመስመር እየተነሳ ነፃ በሆነ ሚና የሚያጠቃው አማካይ ለከርሞ በቀዩ ማልያ ደምቆ ይታያል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ከቀኝ መስመር ተነስቶ ወደ ግራ እየተዘዋወረ ሲጫወት ቆይቷል፡፡ ተጨዋቹ በሁለቱም ቦታዎች በብቃት መጫወት ይችላል፡፡
ባለፈው ዓመት ከቀኝ መስመር እየተነሳ በ24 ጨዋታዎች 10 ጎሎችን አስቆጥሮ 17 ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን ማቀበል ችሏል፡፡ በ21 ጨዋታዎች ከግራ መስመር ተነስቶ 12 ጎሎችን አስቆጥሯል፡፡ 12 ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን አቀብሏል፡፡
በስድስት ጨዋታዎች ተደራቢ አጥቂ ሆኖ የተጫወተው ምክሂታርያን ባለፈው ኦክቶበር በባየርን ሙኒክ 5-1 ሲሸነፉ አንድ ጎል አስቆጥሮ ቦታው እንዳልተስማማው አረጋግጧል፡፡ (በዚያ ጨዋታ ላይ በውሰት) ለቦሩሲያ ዶርትሙንድ ተሰጥቶ ግማሽ ዓመት የቆየው አድናን ያኑዛይ ተቀይሮ ገብቶ ተጫውቷል፡፡
በ2014/15 የውድድር ዘመን ምክሂታርያን በቀኝ መስመር በኩል (22) ጨዋታዎችን አከናውኗል፤ (16) በሚደርሱ ጨዋታዎች ደግሞ በግራ መስመር በኩል ተሰልፏል፤ ነገር ግን በመጀመሪያው የቡንደስሊጋ ዘመኑ በአመዛኙ ሲጫወት የነበረው በተደራቢ አጥቂነት (በአማካይ አጥቂነት)ሚና ነበር፡፡ በዚህ ወቅት ከጥልቅ አማካይ ሚና በመነሳት የተጫወተው በአንድ አጋጣሚ ቢሆንም ቦታው የሚጠይቀው ሚና ከፍ ያለ የፈጠራ አቅም፣ ታታሪነት እና ወደፊት ሄዶ የመጫወት አስተሳሰቡን ይገድብበታል፡፡
ምክሂታርያን እንደ ማንኛውም ተጨዋች በመጀመሪያ ዓመት ተቸግሮ ነበር፤ ሆኖም ባለፉት ሁለት ዓመታት ደረጃውን ወደላቀ ምዕራፍ አሸጋግሯል፡፡ እግርኳስን በከፍተኛ ደረጃ ለመጫወት የሚያስችል አቅም እንደያዘ የሚያጠራጥር ባይሆንም የአሰልጣኝ የጨዋታ ፍልስፍና እንዲሁም ቡድኑ የሚከተለው አጨዋወት እና የሚሰጠው ሚና በእግርኳስ ህይወቱን መሻሻል ላይ ከፍ ያለ ሚና ነበረው፡፡
ያም ቢሆን ግን ምርጥ ቦታው ከመስመር እየነሳ ወደ ውስጥ በመግባት የሚፈጥረው አደጋ እንደሆነ ቁጥሮች ያሳያሉ፤ ሁለገቡ ኮከብ በዩክሬይን ሻክታር ዶኔስክ ሳለ ከአማካይ አጥቂ እየተነሳ ምርጥ ብቃቱን አሳይቷል፡፡ ቦሩሲያ ዶርትሙንድ በመጀመሪው ዓመት ደጋግሞ እዚህ ቦታ ላይ ያሰለፈበት ምስጢርም ይኸው ነው፡፡
የአማካይ አጥቂውን እንደ ራያን ጊግስ አልያም አንድሪያ ኮንቼሊስክስ ማሰብ አይቻልም፡፡ ያም ቢሆን ጆዜ እንደሚከተሉት ታክቲክ፤ እንደ ተጋጣሚ የአጨዋወት ዘይቤ እና እንደ ውድድሩ አይነት ይሄንን አዲስ ፈራሚ በሚፈልጉት መልኩ ይጠቀሙበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በኢንተርናሽናል ጨዋታዎች ደግሞ ይሄ ሁለገብነቱ ይበልጥ አገሩን እንደጠቀመ በሚገባ ታይቷል፤ የአርሜንያ ብሔራዊ ቡድን አምበል እና ወሳኝ ተጨዋች ከመሆኑም ባሻገር ሚናው የተገደበ አይደለም፡፡ ሜዳውን ሙሉ ሸፍኖ በመጫወት በነፃነት ይንቀሳቀሳል፡፡
አንድ ነገር እርግጥ ነው- ጆዜ ይሄንን ተጨዋች ይበልጥ በቼልሲ ኤዲን ሃዛርድ በሚጫወትበት ሚና ያሰልፉታል፤ ነገር ግን ሁለገብነቱ በአንድ ቦታ ላይ ብቻ እንዳይገደብ ያደርገዋል፡፡ ፖርቹጋላዊው የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴን ተግባራዊ ለማድረግ እቅዱ ካላቸው ይሄ ተጨዋች የፈለጉትን ሊሰጣቸው ይችላል፡፡
ከ2006 ጀምሮ በከፍተኛ ደረጃ ሲጫወት የቆየው ምክሂታርያን ከአገሩ ክለብ ጋር አራት ዓት ቆይቶ አራት የሊግ ዋንጫ ማንሳት ችሏል፤ ወደ ሻክታር ዶኔስክ ካመራ በኋላ በ2012/13 የውድድር ዘመን በ29 የሊግ ጨዋታዎች 25 ጎሎችን አስቆጥሯል፡፡
ለአርሜንያ ብሔራዊ ቡድን ባለፉት አራት ጨዋታዎች በአማካይ አጥቂነት፣ በመሀል አማካይነት፣ የቀኝ እና ግራ መስመር አማካይነት ሲጫወት የቆየው ምክሂታርያ አገሩ በ2013 እና 2014 ከዴንማርክ ጋር ስትጫወት የመሀል አማካይ ሆኖ ተሰልፏል፡፡
ያለፈው ዓመት የቡንደስ ሊጋው የዓመቱ ኮከብ ተጨዋች ተብሎ የተመረጠው ምክሂታርያን ለአገሩ የመጀመሪያ ጨዋታውን በጃንዋሪ 2007 ላይ ማከናወን ከጀመረ በኋላ እስካሁን 20 ጎሎችን ማስቆጠር ችሏል፤ ባለፈው ግንቦት ወር- ሶስት ጎሎችን በማስቆጠር ሃት-ትሪክ የሰራው ኮከብ የአገሩ የምንጊዜውም ከፍተኛ ጎል አግቢ ነው፡፡
ሞውሪንሆ ማንቸስተር ዩናይትድን በይፋ ከተረከቡ በኋላ ፈጥነው ሶስት ተጨዋቾችን አስፈርመዋል፡፡ የመጨረሻው ፈራሚ የሆነው ምክሂታርያን ነው፤ አሰልጣኙ ይሄንን ተጨዋች ለምን መረጡ? የሚለው ጥያቄ ጥልቅ የሆነ ምላሽ ይፈልጋል፡፡ እርግጥ ነው የ27 ዓመቱ አማካይ በቡንደስሊጋው ስኬታማ ጊዜያትን ማሳለፉ አንዱ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡
‹‹ካስፈረምናቸው ተጨዋቾች መሀከል ሁለቱ የዓመቱ ኮከብ ተብለው የተመረጡ እንደሆኑ መረሳት የለበትም›› የሚል መረጃን የሚሰጡት ጆዜ፣ ‹‹(ዝላታን) እና ሚኪ (ምክሂታሪያን) ምርጥ ፈራሚዎች ናቸው፡፡ ይሄ ምርጫ በተጨዋቾች የተከናወነ መሆኑ ዋጋውን ከፍ ያደርገዋል፡፡ ሂንሪክ ምርጥ ተጨዋች ነው፡፡ ከምንም በላይ እውነተኛ አጥቂ ሳይሆን ያስቆጠራቸው ጎሎች መጠን በጣም ደንቆኛል፤ ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን በማቀበል ረገድ ያለው ሪከርድ በጣም ይገርማል፡፡ይሄ ደግሞ የፈጠራ አቅሙ፣ እይታው እና የቡድን ስራ ግንዛቤው ምን ያህል የላቀ እንደሆነ ማሳያ ነው፡፡ በእኛ ክለብ ደረጃ እነኚህ ነገሮች ፍፁም አስደሳች ናቸው በማለት ተጨዋቹን ያስፈረሙበት ምክንያት ይፋ አድርገዋል፡፡ 30 ሚሊዮን ፓውንድ የወጣበት ምክሂታርያን ለከርሞ በጉጉት ከሚጠበቁ ተጨዋቾች መሀከል አንዱ ነው፤ ‹‹በአዲሱ ዓመት በተጋጣሚዎቻችን ላይ የበላይነቱን እንምንወስድ እርግጠኛ ነኝ- ተጋጣሚዎቻችን መከላከል ላይ ትኩረት የሚያደርጉ ከሆነ በፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ መጫወት ግድ ይለናል፡፡ ሄንሪክ ደግሞ ከኳስም ሆነ ያለ ኳስ ከፍተኛ ፍጥነት እንደሚጠቀም አልጠራጠርም፤ ይሄ ደግሞ እንደ እኛ ላለ ክለብ በእጅጉ አስፈላጊ ነው›› ይላሉ- የ53 ዓመቱ አሰልጣኝ፡፡