ሊሊ ሞገስ | ለዘ-ሐበሻ ስፖርት
– ይህ ጽሁፍ ነገ በሚኒሶታና አካባቢው ታትሞ በሚሰራጨው ዘ-ሐበሻ ጋዜጣ ላይ የወጣ ነው::
አርሰናል በአሁኑ የዝውውር መስኮት እስካሁን ሁለት አዲስ ተጨዋቾችን መግዛቱ ይታወቃል፡፡ የመጀመሪያው ከቦሪሽያ ሞንቼግላድባህ በ33.2 ሚሊየን ፓውንድ የተገዛው ስዊዘርላንዳዊው አማካይ ግራንት ዣካ ነው፡፡ የ23 ዓመቱ ስዊዘርላንዳዊው በዩሮ 2016 ተሳትፎ ውጤታማ እግርኳስን ለማበርከት መቻሉ አርሴን ቬንገር በትክክል የሚጠቅማቸው ተጫዋችን ለማስፈረም መቻላቸውን ያስመሰክሩበት ሆኗል፡፡
ከዛ ወዲህ ቬንገር ጃፓናዊውን ኢንተርናሽናል አጥቂ ታኩማ ኢሳኖን ከሳንፍሬሴ ሄሩሽማ ክለብ ገዝተውታል፡፡ ከዚህ በፊት ቬንገር ከፀሐይ መውጫዋ አገር ጃፓን ያስፈረሟቸው ሁለት ተጨዋቾች ማለትም ሹኒጂ ኡናሞታና ራዬ ሚያቺ አርሰናልን ለመጥቀም ተስኗቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ የሰሜን ለንደኑ ክለብን ለመልቀቅ ተገድደዋል፡፡
ሆኖም ግን ኢሳኖ የአርሴን ቬንገር ቡድንን ለመጥቀም የሚችልበት የራሱ የሆኑ ተደናቂ ብቃቶን አሟልቶ መያዙን በቅርበት የሚያውቁት ባለሙያዎችን ይመሰክሩታል፡፡ የኢሳኖ ትልቁ ጠንካራ ጎኑ የማይታን አይነት ከፍተኛ ፍጥነትን በተፈጥሮው መላበሱ ነው ጎሎችን አስቆጥሮ ደስታውን የሚገልፅበት የራሱ የሆነ ባህል አለው፡፡
ምክንያቱም ሁለት እጆቹን ከጭንቅላቱ በላይ በማንሳት በጥፍሮቹ የመቧጨር ምልክትን በማሳየት ከእያንዳንዱ ጎሎቹ በኋላ ደስታውን የሚገልፅበት የራሱ የሆነ ስታይል አለው፡፡ ይህንን የድመት ዘሮች ደስታ አገላለፅ ከግንዛቤ በማስገባትም ጃፓናዊያን ፉትቦል አፍቃሪዎች ‹‹ጃጉዋር›› የሚል ተቀፅላን አውጥተውለታል፡፡
ጃጉዋር በሚለው ተቀፅላው እንዲፀኑ ሌላው አንድ ምክንያት የሆናቸው ለተጋጣሚ ቡድን የተከላካይ መስመር ተጨዋቾች አስቸጋሪ የሆነው ከፍተኛ ፍጥነቱ ነው፡፡ ከከፍተኛ ፍጥነቱ ባሻገር የኳስ ስኬሉን ቴክኒካል ብቃቱ አስተማማኝ መሆኑ አርሴን ቬንገር የቡድናቸው የጨዋታ ሲስተምን በትክክል ለመመጠን የሚችልበት ስታይልን መላበሱን እንዲያምኑበት ምክንያት ሆኗቸዋል፡፡
ሆኖም ግን ኢሳኖ ከአውሮፓ ታላላቅ ክለቦች አንዱ ለሆነው አርሰናል ለመፈረም የቻለው በእስካሁኑ የእግርኳስ ህይወቱ ብዛት ያላቸው ጎሎችን ለማስቆጠር ባልቻለበት ሁኔታ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት ግን ለሄሩሽማ ክለብ ዋናው ቡድን በ34 የጃፓን ጄ ሊግ ግጥሚያዎች ላይ ተሰልፎ ዘጠኝ ጎሎችን ለማስቆጠር የቻለበት ውጤታማ ፉትቦሉ የ2015 ውድድር ወጣት ኮከብ ተጨዋችነት ስያሜን ለማግኘት በቂው ሆኖለታል፡፡
በዘንድሮው ዓመት የክለቡ አሰልጣኝ ሰፊ ልምድን ያካበተው የ32 ዓመቱ ፒተር ኡታላን በቡድናቸው የፊት አጥቂ ሚና መጠቀምን ምርጫቸው በማድረጋቸው ኢሳኖ ከእስካሁኑ 11 የጄ ሊግ ግጥሚያዎች ውስጥ በመደበኛ ቋሚ ተሰላፊነት የመጀመር እድልን ያገኘው በአራት ጨዋታዎች ላይ ብቻ ነው፡፡
ሆኖም ግን ከፍተኛ ትኩረትን በሚስቡ ግጥሚያዎች ላይ ወሳኝነት ያላቸውን ጎሎችን ማስቆጠርን የተለመደ ባህሉ አድርጎት ለመዝለቅ ችሏል፡፡ በዲሴምበር 2015 በተከናወነው የክለቡ ወርልድ ካፕ ውድድር ተሳትፎውም የብዙዎችን ልዩ ትኩረትን የሳበለት ሆኗል፡፡ በተለይም በዛ ውድድር ሰንፍሬሴ ሄሩሽማ የዲ.ሪ ኮንጎውን ቲፒ ሚዜምቤን 3ለ0 በማሸነፍ ወደ ግማሽ ፍፃሜው ለመሸጋገር እንዲችል ምክንያት የሆነ ጎልን በማስቆጠር የታጀበ ታላቅ ፐርፎርማንስን ለማበርከት ችሏል፡፡
በግማሽ ፍፃሜው በአርጀንቲና ሪቨርፕሌት 1ለ0 በሆነ ጠባብ ውጤት ቢያሸንፍም አሳኖ በእግርኳስ ህይወቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳተፈበት ትልቅ ውድድር ያሳየው ውጤታማ ፉትቦሉና ከዛ ወዲህም በአራት የጁ ሊግ ግጥሚያዎች ብቻ በመደበኛ ቋሚ ተሰላፊነት የመጀመር ዕድልን አግኝቶ ሁለት ወሳኝ ጎሎችን ለማስቆጠር መቻሉ ለአርሰናል ለመፈረም የተመቻቸ ሁኔታን እንደፈጠረለት ይታመናል፡፡
አርሰን ቬንገር የአርሰናል ስራን ከመያዛቸው በፊት የጃፓኑ ግራሞፐስ ኤይትን በዋና አሰልጣኝነት ለሁለት ዓመታት መምራታቸውም በአገሪቱ በየጊዜው ብቅ የሚሉት ተደናቂ ብቃት ያላቸው ተጨዋቾች የሚጠቀሟቸው ወዳጆችን ጃፓን ውስጥ እንዲያፈሩ ምክንያት ሆኗቸዋል፡፡ ኢሳኖ በእስካሁኑ የፕሮፌሽል ፉትቦል ህይወቱ በ56 ግጥሚያዎች ተሰልፎ ያስቆጠራቸው ጎሎቹ 13 ብቻ ቢሆኑም ከፍተኛ ፍጥነቱና እጅግ የላቀ ቴክኒካል ብቃቱን መሰረት በማድረግ የተጋጣሚ ቡድን የተከለካይ መስመርን ለማስከፈት የሚችልበት የቲምዎርክ ደረጃው ግን ትልቅ ስታንዳርድን የነካ የሚባል ነው፡፡
ይህንን ከግንዛቤ በማስገባትም ቬንገር የ21 ዓመቱ ጃፓናዊው ባስፈረሙበት ማግስት በሰነዘሩት አስተያየት ኢሳኖን ‹‹በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ የአርሰናል እጅግ ምርጡ ተጨዋች ለመሆን እንደሚችል ምንም አይነት ጥርጣሬ የለኝም›› በማለት ገልፀውታል፡፡ ፈረንሳዊው አሰልጣኝ ኢሳኖ ለዋናው ቡድናቸው የሚጠበቅበት ትልቅ ጠቀሜታዎችን የሚሰጥበት ጊዜን የሁለት ዓመታት ቀጠሮን ያወጡለት እንግሊዝ ውስጥ የመጫወት ፈቃዱን ለማግኘት በቅድሚያ በሌላ አውሮፓ አገር ለሚገኝ ክለብ በውሰት ውል መጫወት እንደሚያስፈልገው ግንዛቤን በማሳደር ነው፡፡ ከዚህ በተረፈ ግን ቬንገር የኢሳኖ በሁሉም የአጥቂ መስመር ሚናዎች ላይ ለመጫወት የሚችልበት ሁለገብ ብቃትን የተላበሰ ለመሆኑና በበርካታ ፓሶች ላይ የተመረኮዘ የጨዋታ ስታይሉ ለአርሰናል የጨዋታ ሲስተምን በትክክል ተስማሚነት ያለው ለመሆኑ አንዳችም ጥርጣሬ የላቸውም፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የኢሳኖ ከፍተኛ ፍጥነት በአሁኑ ወቅት በአርሰናል ስኳድ ከሚያገኙት ፈጣን ተጨዋቾችን ማለትም ሄክተር ቤሌሪንና ቲኦ ዋልኮትን የሚያስንቅ ነው፡፡
ምክንያቱም ኢሳኖ በቅርቡ በልምምድ ፕሮግራም ወቅት 50 ሜትር ርቀትን በ5.96 ሴኮንድ ለመግባት ችሏል፡፡ ይህ ጀማይካዊው የዓለም ሻምፒዮን ዮሴን ቦልት ተመሳሳይ ርቀትን በ5.5 ሴኮንድ ከገባበት ጊዜ በ0.4 ማይክሮ ሰከንድ ብቻ የዘገየበት ነው፡፡ ቬንገር ሌላው ኢሳኖን የማስፈረም ውሳኔ ላይ የደረሱበት ዋነኛ ምክንያት ለአርሰናል በማልያ ሽያጭ ከፍተኛ ገቢን የሚፈጥርለት መሆኑን ከግንዛቤ ማስገባታቸው ነው፡፡
ከወዲሁም በቶኪዮና በሌሎቹ የጃፓን ከተሞች የኢሳኖ ለአርሰናል መፈረም ትልቅ የመወያያ ርዕስን የፈጠረ ከመሆኑም ባሻገር ገና ለአዲሱ ክለቡ በአንድ ግጥሚያ ላይ እንኳን ሳይሰለፍ የኢሳኖ ስምን የያዙ የአርሰናል ማሊያዎቹ ለሽያጭ መቅረብ ጀምረዋል፡፡ ከዚህ አንፃር ቬንገር ጃፓናዊው አጥቂን ያስፈረሙበት ውሳኔያቸው ያንን ያህል የአርሰናል ደጋፊዎችን የሚያስከፋቸው አይሆንም፡፡