Quantcast
Channel: ስፖርት | ዘ-ሐበሻ (ZeHabesha) - Latest Ethiopian News Provider
Viewing all articles
Browse latest Browse all 419

Sport: የእንግሊዝ ፕ/ር ሊግን ሊያደምቁት የተዘጋጁት የዓለማችን ምርጥ አሰልጣኞች

$
0
0

የ2016/17 የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ውድድርን በከፍተኛ ጉጉት እንዲጠበቅ ካደረጉት ጉዳዮች ውስጥ ግንባር ቀደሙ በዓለም ታላላቅ የሚባሉት ባለሙያዎች የሊጉ ውድድር ተሳታፊ መሆናቸው ነው፡፡ በዩሮ 2016 ውድድር ለጣሊያን ብሔራዊ ቡድን ውጤታማ ተግባርን ለመፈፀም የቻለበት አንቶኒዮ ኮንቴ የቼልሲ ስራን መያዙ፤ እንዲሁም ጆዜ ሞውሪንሆ እና ፔፕ ጋርዲዮላ በማንችስተር ዩናይትድ እና የማንቸስተር ሲቲ አሰልጣኞች በመሆን ከዚህ በፊት ስፔን ውስጥ ጀምረውት የነበረው ከፍተኛ የሆነ የተቀናቃኝነት መንፈስን በማንችስተር ከተማ ሊደግሙት መዘጋጀታቸውንና ከወዲሁም በሊጉ ውድድር የርገን ክሎፕ፣ አርሴን ቬንገር፣ ማውሪሲዮ ፓቼቲኖ እና ክላውዲዮ ራኒዬሪን የመሳሰሉት ውጤታማ ባለሙያዎች መኖራቸው የ2016/17 የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር የአሰልጣኞች የውጊያ መድረክ በሚል ከወዲሁ እንዲገለፅ ምክንያት ሆኖታል፡፡

managers

አርሴን ቬንገር አርሰናልን ከድፍን 13 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮንነት ክብር ለማብቃት የሚጓጉበት የውድድር አመት ይሆናል፡፡ ሌይስተር ሲቲን ባለፈው የውድድር ዘመን በአስገራሚ ሁኔታ ለፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮንነት ክብር ያበቁት ጣልያናዊው አሰልጣኝ ክላውዲዮ ራኒየሪ የሻምፒዮንነት ክብራቸውን ለማስከበር ከፍተኛ የሆነ ጥረትን የሚያደርጉበት የውድድር ዘመን እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ እነዚህን ሁኔታዎች በመንተራስም የስፖርትስ ሜይል የእግር ኳስ ተንታኞች የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ውድድርን የሚያደምቁት ታላላቅ አሰልጣኞች በተለያዩ ዘርፎች በመከፋፈል ከዚህ በታች ባለው መልኩ የሙያው ብቃታቸውን አመዛዝነውታል፡፡

ጆዜ ሞውሪንሆ (ማን.ዩናይትድ)

ታክቲክስ 9/10

የፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ ከሁሉም በላይ ትልቁ ጠንካራ ጎን የታክቲካል ብቃታቸው ውጤታማነት ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ታክቲካቸውን ከቡድናቸው ተሰላፊዎች የጨዋታ ስታይል ጋር የማዋሃድ ተሰጥዋቸው ከፍተኛ ነው፡፡ ለዚህ ኢንተር ሚላንን በ2009/10 ሲዝን ለቻምፒዮንስ ሊግ ለዋንጫ ድል ለማብቃት የተጠቀሙበት ያማረ ታክቲካል ስትራቴጂያቸው በቂ ማስረጃ ነው፡፡

ፐርሰናሊቲ 6/10

የጆዜ ሞውሪንሆ ፐርሰናሊቲ ተደናቂ የሙያው ብቃታቸው በትክክል የማይመትነው ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፤ በተለይም ባለፈው ሲዝን የቼልሲ ስራን እንዲያጡ በዋነኝነት የሚጠቀስ ምክንያት ሆኗቸዋል ቢባልም ማጋነን አይሆንም፡፡ በተለይም የቼልሲ የቀድሟ ዶክተር ከነበረችው ኢቫ ካርኒዮሮ ጋር የፈጠሩት ግጭት ያለፈው ሲዝንን በውዝግብ ታጅበው ለመጀመር ያስገደዳቸው ሆኗል፡፡ በሪያል ማድሪድ አሰልጣኝነት ዘመናቸው ከስፔናዊው ግብ ጠባቂ አይከር ካስያስ ጋር የፈጠሩት አለመግባባት ኃላፊነታቸው በትልቅ ውዝግብ እንዲታጀብ ያስገደዳቸው ሆኗል፡፡ ሆኖም ግን ቢያንስ የማንቸስተር ዩናይትድ ደጋፊዎች የሞውሪንሆ የኦልድ ትራፎርድ ስራን መያዝ በመደሰት እጃቸውን ዘርግተው ተቀብለዋቸዋል ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡

የዝውውር እንቅስቃሴ -5/10

ሞውሪንሆ በ2004 የቼልሲ ስራን ለመጀመሪያ ጊዜ በያዙበት ወቅት ዲዲዬ ድሮግባ፣ ሪካርዶ ካርቫልሆ እና ማይክል ኤሲዮንን የመሳሳሉት ተጨዋቾችን በማስፈረም ለምዕራብ ለንደኑ ክለብ ጠንካራ አቋም ያለው ቡድንን ፈጥረውታል፡፡ ሆኖም ግን በቼልሲ ስራ የመጨረሻው ሲዝናቸው ከኃላፊነት እንዲነሱ ያስገደዳቸው የዛሬ ዓመት በፕሪ ሲዝን ዝውውር መስኮት የነበራቸው ተጨዋቾችን የማስፈረም እንቅስቃሴያቸው የተበላሸ መሆን ነው፤ ምክንያቱም በዝውውር መስኮቱ ያስፈረሟቸው አራት ተጨዋቾች ማለትም ባባ ራህማን፣ ፔድሮ ፓፒይ፣ ጅሎ ቦዲ እና ራዳሜል ፉልካኦ ስኬታማ ሊሆኑላቸው አልቻሉም፡፡ ሆኖም ግን ሞውሪንሆ በኦልድ ትራፎርድ ስራ ኤሪክ ባሌይ፣ ዝላታን ኢብራሂሞቪች እና ሄንሪክ ሚኪታሪያንን በመግዛት ያማረ የዝውውር እንቅስቃሴን አጀማመር አድርገዋል፡፡

ፔፕ ጋርዲዮላ /የማን.ሲቲ/

ታክቲክስ-9/10

ስፔናዊው አሰልጣኝ ከዚህ በፊት በባርሴሎናና ባየር ሙኒክ በርካታ ዋንጫዎች የተቀዳጀበት ውጤታማ ተግባርን ለመፈፀም የቻለው የተነደፈው ታክቲካል ስትራቴጂ ስኬታማ ሆኖለት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከዚህ አንፃር የጋርዲዮላ የታክቲክሱ የፉትቦል ስትራቴጂ በአዲሱ ሲዝን ኢትሃድን ቢያበራው አስገራሚ አይሆንም፡፡ የማንቸስተር ሲቲ ባለቤቶች ክለባቸው ለአውሮፓ ሻምፒዮንነት ክብር እንዲበቁ ያላቸውን ከፍተኛ ጉጉት በአግባቡ ለማሳካት የሚችልላቸው ትክክለኛው ባለሙያ ጋርዲዮላ እንደሚሆንም ይታመናል፡፡

ፐርሰናሊቲ 7/10

በባየር ሙኒክና ለሪያል ማድሪድ ጋርዲዮላ ሞውሪንሆ ስር የመጫወት እድልን ያገኘው ዣቪ አሎንሶ በቅርቡ በሰጠው መግለጫው ‹‹ጋርዲዮላና ሞውሪንሆ የሚለያዩት በሚከተሉት የፉትቦል ፊሉዞፊያቸው ነው፡፡ ከዚህ በተረፈ ን በሁለቱ ባህሪና አጠቃላዩ ፐርሰናሊቲ በአብዛኛው ተመሳሳይነት ያለው ሆኖ አግኝቼዋለሁ›› ብሎ ነበር፡፡ በእርግጥ ጋርዲዮላ ለቡድኑ ተጨዋቾች ደካማ ጎናቸውን ከመንገር የማይቆጠብበት ግልፅ የሆነ ባህሪው ከሞውሪንሆ ጋር ያመሳስለዋል፡፡ በሁለቱ መካከል የፐርሰናሊቲ ልዩነት ቢኖር ጋርዲዮላ እንደ ሞውሪንሆ ሁሉ አወዛጋቢ መግለጫዎች የመስጠት ባህል የሌለው መሆኑ ነው፡፡

የዝውውር እንቅስቃሴ 7/10

እንደ ሞውሪንሆ ሁሉ ጋርዲዮላም አንዳንድ ተጨዋቾችን ባስፈረመበት ውሳኔው አልፎ አልፎ ስህተትን ሲሰራ ታይቷል፡፡ ለምሳሌ ዤራርድ ፒኬን ከማንቸስተር ዩናይትድ ወደ ባርሴሎና የመለሰበት ተግባሩ ስኬታማ ሆኖለታል፡፡ በአንፃሩ ግን ሴስክ ፋብሪጋስና ዝላታን ኢብራሂሞቪችን በውድ ዋጋ የገዛበት ውሳኔው በስህተት የተሞላ ሲሆን ታይቷል፡፡

የማንቸስተር ሲቲ ስራን የጀመረው ግን ከወዲሁ የጀርመኑ ኢንተርናሽናል ኤልካይ ጉንዶጋንና ስፔናዊው አጥቂ ሚሊቶን በመግዛት በመሆኑ በአሁኑ የዝውውር መስኮት ስኬታማ ጊዜን ለማሳለፍ እንደሚችል ለመገመት አስቸጋሪ አልሆኑም፡፡ በቀጣዮቹ ጥቂት ቀናት ውስጥም ማንቸስተር ሲቲ ሌሎች ሁለት ተጨማሪ ምርጥ ብቃት ያላቸው ተጨዋቾችን ለማስፈረም ዝግጁ መሆኑን አሳውቋል፡፡ ይህ የሚያሳየው ጋርዲዮላ የፕሪ ሲዝን ዝግጅት የሚጀምረው በስኳዱ እንዲኖሩት የሚመኛቸው ተጨዋቾችን በተሟላ ሁኔታ ለመያዝ ችሎ እንደሚሆን ነው፡፡

ከደጋፊዎች ጋር ያለው ግንኙነት 7/10

በ2012 ዓመት ጋርዲዮላ ለድፍን አራት ዓመታት የዓለማችን እጅግ ውጤታማ ክለብ ያደረገውን የባርሴሎና ስራን በመልቀቅ የክለቡ ደጋፊዎች በከፍተኛ ደረጃ አዝነዋል፡፡ ባርሴሎናን በመልቀቅ የባየር ሙኒክ ስራን ከያዘ ወዲህ ግን ከባቫሪያኑ ክለብ ደጋፊዎች ር ያንን ያህል በመልካም ጎኑ ሊጠቀስ የሚችል ግንኙነት ፈጥሮ ነበር ሊባል አይችልም፡፡ የጀርመን ሚዲያዎችም እንደ ባርሴሎና ሁሉ ለባየር ሙኒክ ውጤታማነት ከፍተኛ የሆነ የተቆርቋሪነት መንፈስን መያዙን በመጠራጠር በተደጋጋሚ ትችቶችን ሲያቀርቡበት መታየታቸው የተለመደ ባህላቸው ሆኖ ዘልቋል፡፡

ከዚህ በተረፈ ግን ጋርዲዮላ የሚከተለውን የጨዋታ ስታይል የየትኛውም ክለብ ደጋፊዎች ቢሆኑ ሊጠሉት የሚችሉት አይነት አይደለም፡፡ ከዚህ አንፃር በአሁኑ ስራው ከማንቸስተር ሲቲ ደጋፊዎች ጋር መልካም ግንኙነትን የመፍጠሩ ተስፋ የሰፋ እንደሚሆን ይታመናል፡፡

አንቶኒዮ ኮንቴ /ቼልሲ/

ታክቲክስ 8/10

ኮንቴ ከዚህ በፊት በጁቬንቱስና በጣሊያን ብሔራዊ ቡድን የተከተለውን 3-5-2 የጨዋታ ሲስተምን በቼልሲ ዋና አሰልጣኝነት ዘመኑ ተግባራዊ እንደሚያደርገው ለመገመት አስቸጋሪ አልሆነም፡፡ በዚህ ፎርሜሽን የጣሊያን ብሔራዊ ቡድን በዩሮ 2016 ውድድር ያልተጠበቀ ጥንካሬን እንዲይዝ የረዳው ሆኗል፡፡

ሆነም ግን ከጀርመን ጋር በተደረገው የውድድሩ ሩብ ፍፃሜ በዚህ ሲስተም የማጥቃት ታክቲክስን ተግባራዊ ማድረጉ ፍሬያማ ሳይሆንለት ቀርቷል፡፡ ከዚህ አንፃር የቼልሲ ደጋፊዎች በኮንቴ ስር ቡድናቸው በመከላከል ላይ ያተኮረ ታክቲክስን መሰረት በማድረግ ጎሎችን በፈጣን የካውንተር አታክ ሲስተም የማስቆጠር ስትራቴጂን እንደሚይዝ ቢጠብቁ አስገራሚ አይሆንም፡፡

ፐርሰናሊቲ 9/10

በዩሮ 2016 ውድድር ተሳትፎው ኮንቴ በጣሊያን ብሔራዊ ቡድን ታክቲካል ኤሪያ በእያንዳንዱ ግጥሚያዎች ላይ በከፍተኛ ስሜት ተውጦ ሲወራጭ የታየበት ተግባሩ በውስጡ ያለው ባህሪ ምን እንደሚመስል የማንፀባረቅ ኃይል ያለው ከፍተኛ የሆነ የማሸነፍ ወኔና ለሚመራው ቡድን ስኬታማነት ከፍተኛ የሆነ ተቆርቋሪነት መንፈስን መላበሱን በጭራሽ መጠራጠር አያሻም፡፡

ከዚህ አንፃር ጆዜ ሞውሪንሆ የቼልሲ ስራን ሲለቁ በክለቡ ደጋፊዎች በከፍተኛ ደረጃ የሚወደድ ሌላ አሰልጣንን ማግኘታቸው አጠራጣሪ የሆነበት እውነታን የኮንቴ የስታምፎርድ ብሪጅ ስራን መያዝ እንደሚለውጠው ይጠበቃል፡፡ ውጤታማ ዘመን ደግሞ ወደ ምዕራብ ለንደኑ ክለብ እንዲመለስ የሚያስችል ትክክለኛው ባለሙያም ጭምር ነው፡፡

የዝውውር እንቅስቃሴ 8/10

ኮንቴ በጁቬንቱስ አሰልጣኝነት ዘመኑ ፖል ፓግባን ከማንቸስተር ዩናይትድ በነፃ ዝውውር ከማስፈረምም አልፎ አርቱሮ ቪዳልን ማግኘቱ ስልጠናው የዝውውር እንቅስቃሴ ስትራቴጂ እንዳለው በቂ ማስረጃ ነው፡፡ ያለፉትን ሁለት ዓመታት ያሳለፈው የጣሊያን ብሔራዊ ቡድንን በአሰልጣንነት በመምራት መሆኑ ምንም ተፅዕኖን ሳይፈጥርበት በቼልሲ ስራው ከወዲሁ ቤልጅየማዊው ኢንተርናሽናል ሚኪይ ባትሹላይን በ33 ሚልየን ፓውንድ ሂሳብ ከኦሎምፒክ ማርሴይ የገዛበት ውልን ተፈፃሚ አድርጎታል፡፡የኮንቴ ቀጣዩ ተግባር የሚመስለውም የቼልሲ የተከላካይ መስመርን የአማካይ ክፍልን የሚያጠናክርበት አዲስ ተጨዋቾችን ማስፈረም መቻል ነው፡፡ ከወዲሁ ስማቸው ከቼልሲ ዝውውር ጋር በመያያዝ ላይ ያሉት ንጎሎ ካንቴና ራድ ያንጎላን በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት ውስጥ ስታምፎርድ ብሪጅ የመድረሳቸው ተስፋ ሰፊ ሆኖ በመታየት ላይ ነው፡፡ በተለይም ያንጎላን ለቼልሲ እንዲፈርም የቤልጅየም ብሔራዊ ቡድን ጓደኛው ኤደን ሃዛርድ በዩሮ 2016 ውድድር ተሳትፏቸው ወቅት ይፋ ያደረገበት መግለጫን መስጠቱ ይታወሳል፡፡

የደጋፊዎች ግንኙነት 9/10

የማንኛውም ክለብ ደጋፊዎች ቢሆኑ ለቡድናቸው ውጤታማነት ከፍተኛ የሆነ የተቆርቋሪነት መንፈስ ያለው ዋና አሰልጣኝ እንዲኖቸው መመኘታቸው የተለመደ ነው፡፡ በዩሮ 2016 ውድድር ተሳትፎው በእያንዳንዱ ግጥሚያዎች ላይ በከፍተኛ ስሜት ተውጦ የቡድኑን ተጨዋቾች በመምራት ባሀሪው ላይም ከሚታወቀው ኮንቴ የተሻለ ይህንን ክራይቴሪያን በተገቢው ሁኔታ የሚያሟላ ባለሙያን ማግኘት ይከብዳል፡፡ ከዚህ አንፃር ኮንቴ የቼልሲ የስራ ዘመኑ ከክለቡ ደጋፊዎች መልካም ግንኙነትን ፈጥሮ እንደሚዘልቅ ለመገመት አስቸጋሪ አይሆንም፡፡

አርሴን ቬንገር /አርሰናል/

ታክቲክስ 7/10

ፈረንሳዊው አሰልጣኝ አርሰናልን ከመሩበት 20 ዓመታት ውስጥ የመጀመሪያዎቹ ስምንት ዓመታት ያሳለፉት ለቡድናቸው በርካታ ጎሎችን በማስቆጠር በማጥቃት ላይ ያተኮረ ስትራቴጂን በማስገኘት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ውድድርን ውበት በተላበሰ ፉትቦል አድምቀውት ነበር፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህም የቬንገር በማጥቃት ላይ ያተኮረ የፉትቦል ፊሎዞፊ ብዙም አልተቀየረም፡፡ ሆኖም ግን ይህ ፊሎዞፊያቸው በተጋጣሚ ቡድኖች ከበቂም በላይ የታወቀበት እውነታን ለመቀየር የሚችሉበት አማራጭ ታክቲክስ ሲቀይሩ አለመታየታቸው አርሰናልን ከ2003/04 ሲዝን ወዲህ አንድ እንኳን የፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮንነት ክብርን ያሳጣው ሆኗል፡፡

ፐርሰናሊቲ 6/10

የፈረንሳዊው አሰልጣኝ ባህሪን አጥብቀው የሚጠሉት ወገኖች አሉ፡፡ በተለይም የተጋጣሚ ቡድን አሰልጣኞች ‹‹ሽንፈትን በፀጋ በመቀበል ችግር አለባቸው›› በሚል ይወቅሷቸዋል፡፡ በዛኑ መጠን ግን የቬንገርን ባህሪና ስብዕና የሚወዱት ወገኖችም አሉ፡፡ ከሚወደድላቸው ባህሪዎቻቸው ውስጥ ለሽንፈታቸው የራሳቸው ቡድን ተጨዋቾችን በይፋ ከመውቀስ መቆጠባቸውና ቡድናቸውን ከአስቸጋሪ ሁኔታ በፍጥነት እንዲላቀቅ ለማስቻል የሚያደርጉት ሙሉ ትኩረት ነው፡፡

የዝውውር እንቅስቃሴ 8/10

ቬንገር በአብዛኛው አዳዲስ ተጨዋቾችን በማስፈረም ተግባራቸው ስኬታማ ሲሆኑ ታይተዋል፡፡ በተለይም ቲዬሪ ሆንሪን ከጁቬንቱስ በማስፈረም በአርሰናል ታሪክ የክለቡ የምንጊዜውም ከፍተኛው ጎል አግቢ እንዲሆን አስችሎታል፡፡

በ2015 ፕሪ ሲዝን ግን ፒተር ቼክን በማስፈረም የተገደበ የዝውውር እንቅስቃሴን በማድረግ ልላ የሜዳ ላይ ምርጥ ብቃት ያለው ተጨዋችን ለማስፈረም ተስኗቸዋል፡፡ ያንን ስህተታቸው በአሁኑ የዝውውር መስኮት ስዊዘርላንዳዊው አማካይ ግራንት ዣካን ከወዲሁ በማስፈረም እርማትን ማስገኘት ጀምረዋል፡፡ ቀጣዩ የቬንገር አላማ ትክክለናው ጎል አዳኝን ለቡድናቸው የፊት አጥቂ መስመር ለማስገኘት መቻል ነው፡፡

የደጋፊዎች ግንኙነት 5-10

ቬንገር በየዓቱ የአርሰናል የቻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ተሳትፎን ማግኘት ትልቅ ኩራትን ሲፈጥርባቸው የሚታዩበት ባህሪያቸው ከክለባቸው ደጋፊዎች ውስጥ በግማሽ ያህሉ እንዲጠሉ በሞኝነት የሚጠቀስ ምክንያት ሆኗቸዋል፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የአርሰናል ደጋፊዎች የቡድናቸው በወሳኝ ወቅት ከፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮንነት ፉክክር የመሸሽ ባህሉን በመጥላት በቬንገር ላይ ከፍተኛ ተቃውሞን ማሰማታቸው የተለመደ ሆኗል፡፡

የርገን ክሎፕ /ሊቨርፑል/ 

ታክቲክስ 6/10

ጀርመናዊው አሰልጣኝ በቦሪሺያ ዶርትሙንድ ቆይታቸው ይበልጥ ስኬታማ ያደረጋቸው ታክቲክሳቸው ካውንተር ፕሬሲንግ የሚለው መመሪያቸው ነው፡፡ ይህንን የቡድናቸው ተሰላፊዎች በከፍተኛ ፍጥነት በታጀበ የማጥቃት እንቅስቃሴ በተጋጣሚ ቡድን ላይ ከፍተኛ ጫናን እንዲፈጥሩ የሚያደርጉበት ስትራቴጂን ወደ ሊቨርፑል ዘልቆ እንዲገባ አስችለውታል፡፡ ይህ ታክቲክስ በሊቨርፑል ፍሬያማ መሆን ለመጀመሩ ቡድኑ የ2015/16 ሲዝን የዩሮ 2015/16 ሲዝንን ለዩሮፓ ሊግ የፍፃሜ ግጥሚያ በመድረስ ማጠናቀቁ በቂ ማስረጃ በመሆኑም የክሎፕ ካውንተር ፕሬሲንግ ሲስተም በአዲሱ ሲዝንም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ይጠበቃል፡፡

ፐርሰናሊቲ 10/10

የየርጊን ክሎፕ የግል ባህሪና አጠቃላዩ ሰብዕና በራሳቸው ቡድን ተጨዋቾች ብቻ ሳይሆን በተቃራኒ ቡድኖች አባላትና በገለልተኛ የፉትቦል አፍቃሪዎች ጭምር የሚደድ ነው፡፡ በተለይም የቡድናቸው ድልን በከፍተኛ የፈንጠዝያ ስሜት ሆነው ደስታቸውን የሚገልፁበት ባህሪያቸው ሁሉንም ክለቦችን ደጋፊዎችን የማዝናናት ደረጃው ከፍተኛ ነው፡፡

የዝውውር እንቅስቃሴ 7/10

ባሪሽያ ዶርትሙንድ ሁለት ጊዜ የጀርመን ቡንደስሊጋ ሻምፒዮንነት ክብር የተቀዳጀውና በ2013 የቻምፒዮንስ ሊግ ፋይናል በዌምብሊ ለማድረግ የቻለው በክሉፕ ብልህ የዝውውር እንቅስቃሴን መሰረቱ በማድረግ ነው፡፡

በተለይም ማትስ ሃሜልሰና ሮቤርቶ ሌዎንዶውስኪን በማስፈረም የዶርትሙንድ እጅግ ምርጡ ተጨዋቾች አድርገዋቸው ነበር፡፡ በአሁኑ የዝውውር መስኮት ከወዲሁ ለሊቨርፑል ያስፈረሟቸው ሶስት ተጨዋቾች ማለትም ሳይዶ ማኔ፣ ሊሪስ ካሪዩስና ጀይል ማቲፕ ግን የክለቡን ትልቅ ስታንዳርድን የሚመጥን ውጤታማ ብቃትን መያዛቸውን የሚጠራጠሩ አስተያየት ሰጪዎች አሉ፡፡

የደጋፊዎች ግንኙነት 9/10

ክሎፕ በዶርትሙንድ የስራ ዘመናቸው በክለቡ ደጋፊዎች በከፍተኛ ደረጃ ይፈቀሩ ነበሩ፡፡ ይህ ሁኔታ የአንፊልድ ስራ ሲይዙ በሊቨርፑል ደጋፊዎች በተደረገላቸው ያማረ አቀባበል ተደግሞላቸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ጀርመናዊው አሰልጣኝን የሚጠላ አንድም የሊቨርፑል ደጋፊ መኖሩ አጠራጣሪ ነው፡፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 419

Trending Articles