የሪዮ ኦሎምፒክን ተከትሎ በዋና ስፖርት የተካፈለው ኢትዮጵያዊው ሮቤል ኪሮስ የዓለም መነጋገሪያ መሆኑ አይዘነጋም:: ከኢትዮኪክ አዘጋጅ ማርታ በላይ ጋር እየተወራበት ስላለው ነገር ሁሉ ተወያይቷል:: ያንብቡት::
ኢትዮ ኪክ:- አሁን በብራዚል ሰአት አቆጣጠር ከሌሊቱ 9 ሰአት ነው አንተ ግን አልተኛህም(ኢንተርቪው ባደረግነበት ሰአት በብራዚል ሌሊት ነበር) ?
ሮቤል:- አዎ አልተኛሁም፤ በማህበራዊ ድህረ ገፆች እና በሜዲያዎች እያየሁት ያለሁት ነገር እንቅልፍ የሚያስወስድ አይደለም።
ኢትዮኪክ:- በዚህ መልኩ መታወቅህ የፈጠረብህ ስሜት?
ሮቤል:- በጣም አዝኛለው። በእውነቱ ሰዎ ያልገባው ነገር አለ…..እኔ እዚህ ውድድር ላይ ለማሸነፍ አይደለም የመጣሁት፣ ከዚህ በፊትም በሬዲዮ ላይ ተናግሪያለው። ከዚህ በፊት ከነበረን ታሪክ በተወሰነ መልኩ ለማስተካከል እሞክራለው ብዬ ነው የመጣሁት ፤ ይህ ጥፋት ከሆነ ለሁሉም ይቅርታ!
ኢትዮ ኪክ :- ከዚህ በፊት የነበረው ውጤት ስትል?
ሮቤል:- ከዚህ በፊት ከነበረን የተሻለ ታሪክ ለመስራት፤ ወርልድ ሻምፒዮን ሰአቴ 1:03፤ ኦል አፍሪካ ጌም ላይም እንደዛው። ከአሁኑ በ02 ሰከንድ ነው የሚያንሰው። በዛ ላይ ኢትዮጵያ የተዘጋጀሁት 50ሜትር ነበር ኦሎምፒክ ሊደርስ ሲቃረብ 100ሜትር እንደምወዳደር የተነገረኝ። ብዙም ባልተዘጋጀሁበት ርቀት የተወዳደርኩት።
ኢትዮ ኪክ :- ኢትዮጵያን ወክሎ ኦሎምፒክ ላይ ሮቤል እንዴት ታሳተፈ?
ሮቤል:- ሩሲያ ላይ ውድድር ነበር ወርልድ ሻምፒዮን ውድድሩ 1ኛው አላማው ለኦሎምፒክ ሚኒማ ለሟሟላት ሲሆን 2ኛው በተሳትፎ ኦሎምፒክ ቀጥታ ለመሳተፍ በሚለው እኔም ቀጥታ ልወዳደር ችያለው።
ኢትዮ ኪክ:- ሩሲያ ላይ ብቻ መሳተፍ በቂ ነበር ኦሎምፒክ ላይ ኢትዮጵያን ለመወከል ?
ሮቤል:- በቂ ሳይሆን የአለም አቀፉ ዋና ፌዴሬሽን መስፈርቱ ነበር።
ኢትዮ ኪክ:- አንተ መስፈርቱን አሟልተክ ነው ማለት ነው?
ሮቤል:- ራሺያ ሶስት ዋናተኞች ሄድን፣ ከዛ በፊት ሚኒማ ለወርልድ ሻምፒዮን ለሟሟላት አገር ቤት ከ1 ዋናተኛ ጋር ተወዳድሬ እሱን በነጥብ ስላሸነፍኩ ራሺያ ወርልድ ሻምፒዮን ሄድኩኝ።
ኢትዮ ኪክ:- ሰውነትክ የዋናተኛ አይመስልም ?
ሮቤል :- አቃለው!
ኢትዮ ኪክ :- ክብደትህ ስንት ነው?
ሮቤል:- ከሁለት ወራት በፊት 120 ነበር ኪሎዪ ከዛ ቀንሼ ነው 80 ። ከዚህ በፊት ክብደቴ 74 ኪሎ ነበር ። ናዝሪት ከባጃጅ ላይ ወድቄ እጄ ተሰብሮ ከስፖርቱ ስርቅ ኪሎዪም ጨመረ።
ኢትዮ ኪክ:- አባትህ የዋና ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ናቸው?
ሮቤል:- አዎ ልክ ነው።
ኢትዮ ኪክ :- የአባትህ በፌዴሬሽን ውስጥ ፕሬዝዳንት መሆን እንጂ አንተ ለኦሎምፒክ አትመጥንም ለሚለው ምላሽህ ?
ሮቤል:- እኔ አባቴ ፕሬዝዳንት መሆኑ ከኔ ይልቅ ለፌዴሬሽኑ ጠቅሞታል። አባቴ የዋና ስፖርት ስለሚወድ ለፌዴሬሽኑ ከራሱ ገንዘብ እያወጣ ይከፍላል።ለስፖርተኞች ሲያሸንፉ 3ሺም 5ሺም የሚከፍለው አባቴ ከራሱ ኪስ ነው። እኛ ሩሲያ ለወርልድ ሻምፒዮን ስንሄድ ለሶስት ዋናተኞች ሁሉንም ወጪ የሸፈነው ፌዴሬሽኑ ሳይሆን አባቴ ነው። ፌዴሬሽኑ እኮ ቢዘጋ ይመረጣል ምክንያቱም ገንዘብ የሌለው ፤ የመዋኛ ገንዳ የሌለው ፌዴሬሽን ነው ያለን ስለዚህ የዋና ፌዴሬሽን ባይኖረን ይመረጣል።
ኢትዮ ኪክ :- ፌዴሬሽን የለንም እንበል፤ ኦሎምፒክ ላይ ዋናተኛ አለን ብለን አንተ መወክለህስ እንዴት ይታያል?
ሮቤል:- እኔ በራሴ ጥረት እዚህ የደረስኩት። የምሰራው ብቻዪን ነበር።
ኢትዮ ኪክ :- አሰልጣኝ የለክም ነበር ?
ሮቤል:- አሰልጣኝ አልነበረኝም። በፌዴሬሽኑ እና በአሰልጣኙ መሀከል ግጭት ስለነበር እኔ የምሰራው ሮኪ አዲስ አበባ ገንዳ ነበር፤ በርግጥ ፌዴሬሽኑ ጊዮን ተፈቅዶለትን ነበር። የጊዮን መዋኛ ቀዝቃዛ ነው፤ ሮኪ ሙቅ ውሀ ነው ፤በዛ ላይ የተሻለ ነበር።
ኢትዮ ኪክ:- የመክፈቻው እለት ባንዲራ ይዘህ ከፊት ነበርክ ፤ እንዴት ነው ያንን ክብር ያገኘኸው?
ሮቤል:- ከመክፈቻው ስነስርአት ከ30 ደቂቃ በፊት ነው የተነገረኝ። መክፈቻው ላይ ባንዲራ ይይዛል የተባለው ጥጋቡ( ብስክሌተኛው) በንጋታው ጠዋት ላይ ውድድር እንዳለው የታወቀው እዛው ከደረስን በኃላ ነበር ። የመክፈቻው ስነስርአት በአጠቃላይ 5 ሰአታት ይፈጃል፤ እሱ ደግሞ 5 ሰአት ሙሉ የሚቆም ከሆነ ሳይተኛ ውድድሩ ውስጥ ሊገባ ነው። በዛ ሰአት ወንድ ስፖርተኛ ሲፈለግ እኔ ብቻ ነበርኩ። ለእኔም እዛው ሳልዘጋጅ ተነገረኝ ። አትሌቶቹ ገና ዛሬ ነው የሚገቡት።በርግጥ እንደዚህ አይነት ክብር ለእነ ደራርቱ፣ ቀነኒሳ እና ታሪክ ለሰሩ ሰዎች ይገባ ነበር።
ኢትዮ ኪክ:- ከዚህ በኃላ ሮቤል ምን ያስባል?
ሮቢል:- ከዚህ በኃላ በዋና ስፖርት አልወዳደርም። ስለ ሁሉም ነገር እግዚሐብሔር ይመስገን። እኔ በእይወቴ ፖለቲካ አላውቅም። ስፖርትና ፖለቲካ አይገናኙም። ብዙ ሰዎች ባንዲራ ከያዝኩ ቀን ጀምሮ በፌስ ቡክ ይሰድቡኛል። እኔ ተወልጄ ያደኩት ናዝሪት ነው። በአባቴ የትግራይ ተወላጅ እናቴ አማራ ቢሆንም ስለ ፖለቲካ የማውቀው ነገር የለም። ግን በዛ መልኩ አያይዘው ብዙ ነገሮች እየተባለ ነው ምላሼ ዝምታ ነው።
ኢትዮ ኪክ:- ሮቤል እንቅልፉን ሰውቶ ፍቃደኛ በመሆኑ አመሰግናለው