የዛሬ ሃያ ዓመት ነበር ኢትዮጵያ በሴቶች ማራቶን የመጀመሪያውን ወርቅ በአትሌት ፋጡማ ሮባ አማካኝነት አትላንታ ላይ ያገኘችው:: የዛሬ 4 ዓመት በለንደን ቲኪ ገላና ይህን ወርቅ ደግማው ነበር:: ዛሬ ደግሞ አትሌት ማሬ ዲባባ 3ኛ በመውጣት ይህን የኦሎምፒክ የማራቶን ድል ወደ ኢትዮጵያ አምጥታዋለች::
እርሷን ተከትላ አትሌት ትርፌ ፀጋዬ አራተኛ ደረጃን የያዘች ሲሆን አትሌት ትዕግስት ቱፋ 18ኛ ኪሎ ሜትር ላይ በጉዳት ከውድድሩ ልትወጣ ተገዳለች::
የሪዮውን ኦሎምፒክ በአንደኝነት ያጠናቀቀችው ኬንያዊቷ ሱኦንግ ጃሌት ስትሆን የገባችበት ሰዓትም 2:24:04 ነው:: እንዲሁም ለባህሬን ዜግነቷን ቀይራ የምትሮጠው ኪርዋ ጄፕኪሩይ በ9 ሰከንድ ተቀድማ ሁለተኛ ሆናለች::
ማሬ እ.ኤ.አ. በ2015 በቻይናዋ ቤጂንግ በተካሄደው የዓለም ሻምፒዮና በማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘችው ርቀቱን 2 ሰዓት 27 ደቂቃ ከ39 በመግባት ነበር፡፡ አትሌት ትርፌ ፀጋዬ 2 ሰዓት ከ20 ደቂቃ ከ18 ሰከንድ በ2014 የበርሊን ማራቶን ላይ ያጠናቀቀችበት ሰዓት ነው። የፓሪስና የቶኪዮ የማራቶን አሸናፊ ነበረች፡፡
ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ ተሳትፎዋ እ.ኤ.አ. በ1996 በአትላንታ ሴቶች ማራቶን ፋጡማ ሮባ 2 ሰዓት ከ26 ደቂቃ ከ05 በመግባት የመጀመርያውን ወርቅ አምጥታለች፡፡ ከዚያ በኋላ በሴቶች ማራቶን በኦሊምፒክ ወርቅ ለማምጣት አራት ኦሊምፒያድ ወስዷል፡፡ በቲኪ ገላና አማካይነት በ2012ቱ የለንደን ኦሊምፒክ ወርቅ ተመዝግቧል፡፡ ከአራት ዓመት በፊት በለንደን ጎዳና ላይ በተደረገው ውድድር ቲኪ ርቀቱን 2 ሰዓት ከ23 ደቂቃ ከ07 በመፈጸም የኦሊምፒክ ሪከርድ መስበሯ ይታወሳል፡፡