(ኢ.ኤም.ኤፍ – የዳዊት ከበደ ወየሳ አጭር ዘገባ)
በሪዮ ኦሎምፒክ የማራቶን ውድድር 2ኛ የወጣው አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ፤ በአሜሪካ መንግስት ተቀባይነት በማግኘት ወደ አሜሪካ የሚገባበት ቪዛ ተሰጥቶታል። ምሽቱን ዘግይቶ የደረሰን ዜና እንዳመለከተው ደግሞ፤ አሁን አሜሪካ የሚገኝ መሆኑን ውስጥ አዋቂ ምንጮች በተለይ ለኢ.ኤም.ኤፍ ገልጸዋል።
አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ የሪዮ ኦሎምፒክን 2ኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ፤ ሁለት እጆቹን አቀናጅቶ፤ በኢትዮጵያ እየተደረገ ያለውን በመንግስት ድጋፍ የሚደረገውን ጥቁር ሽብር ማውገዙ ይታወሳል። አትሌቱ በዚህ የጀግና ስራው በኢትዮጵያውያን ዘንድ ታላቅ አክብሮትን ተቀዳጅቷል። ሌሎች አትሌቶች የሩጫ ውድድር ሲያሸንፉ በተመሳሳይ መልኩ እጃቸውን በማቀናጀት ተቃውሟቸውን ማሰማት ጀምረዋል።
ለአትሌት ፈይሳ… ግጥሞች ተጽፈውለታል። በቅኔ ተወድሷል፤ ዘፈን ተዘፍኖለታል። ሲ.ኤን.ኤን እና ቢቢሲን ጨምሮ የአለም ታላላቅ የዜና አውታሮች፤ እጁን ያቀናጀበትን ምክንያት በመዘርዘራቸው፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የሰብአዊ መብት ረገጣ ለማጋለጥ ልዩ ምክንያት ሆኗል።በአጭሩ… ኢትዮጵያውያን ለ25 አመታት የጮሁለትን እውነት፤ የ25 አመቱ ወጣት አትሌት… 25 ደቂቃ ባልሞላ ግዜ ውስጥ የ25ቱን ግፍ አለም እንዲያውቀው አድርጎታል።
አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ፤ ቤተሰቡን ኢትዮጵያ ትቶ ትልቅ መስዋዕትነት በመክፈል ለፈጸመው አኩሪ ተግባር እውነተኛ ኢትዮጵያውያን ደስታቸውን ሲገልጹ፤ የኢህአዴግ ደጋፊዎች በድርጊቱ ተቆጭተው፤ “ሜዳሊያውን መቀማት አለበት” እስከማለት ደርሰው ነበር። ያሰቡት ግን አልተሳካም። ይልቁንም የአትሌት ፈይሳ ሌሊሳ የብር ሜዳልያ ፤ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ለወደቁት እና ለሚሞቱት ዜጎች ዘላለማዊ መታሰቢያ ሆኗል። ሌላም ነገር እንጨምር። በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ፤ 2ሺህ 852 ሰዎች በ18 ቀናት ውስጥ ከ160 ሺህ ዶላር በላይ በኢንተርኔት መዋጮ አድርገውለታል።
በዚህ የኦሎምፒክ ማራቶን ውድድር የአሜሪካ አትሌት ጌለን ራፕ 3ኛ መውጣቱ ይታወቃል። ይህም በዚህ ክፍለ ዘመን 5ኛው የማራቶን ሜዳሊያ ነው – ለአሜሪካ። በቀጣይ አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ ለአሜሪካ ብሔራዊ አትሌቲክስ ቡድን እንደሚሮጥ ይጠበቃል። በሚቀጥለው የኦሎምፒክ ማራቶን ካሸነፈ ደግሞ ለአሜሪካ የክፍለዘመኑ 6ኛውን ሜዳሊያ ያስገኛል ማለት ነው።