Quantcast
Channel: ስፖርት | ዘ-ሐበሻ (ZeHabesha) - Latest Ethiopian News Provider
Viewing all articles
Browse latest Browse all 419

Sport: በቼልሲ ዙሪያ የተዘጋጀ ልዩ ዘገባ |ጉስ ሂድኒክ የቼልሲ ስራን ለመያዝ ተዘጋጅተዋል

$
0
0

ቼልሲ ያለፈውን የውድድር አመት ያጠናቀቀው ሁለት የዋንጫ ሽልማቶችን በማግኘት ማለትም ለፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮንነት ክብር በመብቃትና የካፒታል ዋን ውድድር ድልን በመቀዳጀት ነበር፡፡ ዘንድሮ ግን በእነዚህ ሁለት ውድድሮች የዋንጫ ሽልማቶችን የማግኘት ተስፋው ዝቅተኛ ሆኗል፡፡ ምክንያቱም ከስቶክ ሲቲ በመለያ ምት ተሸንፎ የካፒታል ዋን ውድድር ዘመቻውን ወደ ሩብ ፍፃሜው ደረጃ ለማሸጋገር ሳይችል ቀርቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከሊጉ መሪዎች ማንችስተር ሲቲና አርሰናል ጋር ያለው የነጥብ ልዩነት 11 በመሆኑም የፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮን ክብሩን የማስከበሩ ተስፋ ዝቅተኛ ሆኗል፡፡
chealsea

ይህንን እውነታን ከግንዛቤ በማስገባትም በፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ ምትክ የቼልሲ ስራን ለመረከብ በግንባር ቀደምትነት ሆላንዳዊው ጉስ ሂድንኪና ጣሊያናዊው ካርሎ አንቾሎቲ ታጭተዋል፡፡ የእነዚህ ሁለት ባለሙያዎች ስም ከቼልሲ ስራ ላይ እንዲያያዝ በዋነኝነት የሚጠቀሰው ምክንያት ሁለቱም በአሁኑ ወቅት ካለስራ መቀመጣቸው ነው፡፡ በተለይም ከዚህ በፊት ቼልሲን ለአጭር ጊዜ በተጠባባቂ ዋና አሰልጣኝነት የመሩት ጉስ ሂድኒክ ከሰሞኑ በሰጡት አንድ መግለጫቸው በሞውሪንሆ ምትክ የቼልሲ አዲሱ ዋና አሰልጣኝ ሆነው ለመሾም ዝግጁ መሆናቸውን የሚጠቁም ሆኗል፡፡

ሂድንኪ የፊታችን ሰኔ ወር በፈረንሳይ አዘጋጅነት ለሚካሄደው ዩሮ 2016 ውድድር የሆላንድ ብሔራዊ ቡድንን ተሳታፊ የማድረግ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ለመፈፀም ስለተሳናቸው ከአሰልጣኝነት ራሳቸውን ማግለላቸው ይታወቃል፡፡ በሰሞኑ መግለጫቸው ለ2ኛ ጊዜ ሊመሩት መመኘታቸውን የጠቆሙት ቼልሲን በ2009 ለስድስት ወራት ያህል በተጠባባቂ ዋና አሰልጣኝነት በመምራት ለኤፍ.ኤ.ካፕ ድል ያበቁት ከመሆኑም ባሻገር በፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮንነት ፉክክሩ እስከመጨረሻዎቹ ጥቂት ሳምንታት ድረስ በጠንካራ አቋም ሆኖ ለመዝለቅ እንዲችል ረድተውት ነበር፡፡

ያንን መልካም ጊዜቸውን መለስ ብለው በማስታወስ ሂድኒክ ደግሞ የቼልሲ ስራን ለመያዝ መመኘታቸውን የጠቆሙበት መግለጫን ሲሰጡ ተደምጠዋል፡፡ ‹‹ፉትቦል ኢንተርናሽናል›› የተባለው የሆላንድ ጋዜጣ ከሰሞኑ ‹‹ከስድስት ዓመታት በኋላ ወደ ቼልሲ በመመለስ በዋና አሰልጣኝነት የመስራት ፍላጎቱን አሳድረዋል በሚል ላቀረበላቸው ጥያቄ ሂድኒክ ምላሻቸውን ሲሰጡ የተደመጡት ‹‹በትልቅ ደረጃ በሚደረግ ውድድር የሚሳተፍ ትልቅ ክለብን በዋና አሰልጣኝት የመምራት ፍላጎትን የማሳደር ባህል አለኝ፡፡ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በርካታ ጥሪዎችንም ቀርበውልኛል፡፡ የቀረበልኝ ጥሪዎችን ሳልቀበላቸው የቀረሁት የትልቅ ክለብ ሥራን ለመያዝ በመመኘት ነው፡፡ ለምሳሌ እንደ ቼልሲ አይነቱ ትልቅ ክለብ ጥያቄ የሚያቀርብልኝ ከሆነ ካለምንም ማመንታት መልሴን የምሰጠው እንደሚሆን አልደብቅም፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ቀጣዩ ሥራዬ ምን እንደሚሆን እርግጠኛ ሆኜ የምናገረው ጉዳይ የለኝም›› በማለት ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት ዕድሜያቸው 68 የደረሰው ሂድኒክ ከዚህ በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ የቼልሲ ስራን በፌብርዋሪ 2009 የተረከቡት የብራዚሉ አሰልጣኝ ሉዊስ ፍሊፕ ስኮላሪ ለሰባት ወራት ከዘለቁበት የስታምፎርድብሪጅ ስራ መነሳትን ተከትሎ ነበር፡፡ ሃዲንኪ ስታምፎርድ ብሪጅ እንደደረሱም ቼልሲ እስከሲዝኑ መጋመስ ድረስ የነበረው የአቋም አለመረጋጋት የ2008-09 ሲዝን ዘመቻውን በፕሪሚየር ሊግ የደረጃ ሰንጠረዥ በ3ኛ ስፍራ ላይ ተቀምጦ እንዲጨርስ አስችለውታል፡፡

የቻምፒዮንስ ሊግ ዘመቻውን እስከ ግማሽ ፍፃሜው ደረጃ ድረስ ለመዝለቅ እንዲችልም አድርገውታል፡፡ በወቅቱ በቻምፒዮንስ ሊግ ግማሽ ፍፃሜ የደርሶ መልስ ግጥሚያ ቡድናቸው በባርሴሎና በአጠቃላይ ውጤት ተሸንፎ በሮም ከተማ ከተደረገው የውድድሩ ፋይናል የቀረውን ግልፅ የሆኑ የዳኝነት በደሎች ተፈጽሞበት እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ ሂድኒክ ያንን ፀፀታቸውን ግን በሜይ 2009 በዌምብሊ ስቴዲየም ከኤቨርተን ጋር የተደረገው የኤፍ.ኤ.ካፕ ፋይናልን 2ለ1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የዋንጫውን ሽልማትን በማግኘት በመጠኑም ቢሆን ሊረሱት ችለዋል፡፡ ይህ የሚያሳየው ሂድኒክ ቼልሲን ለአጭር ጊዜ በተጠባባቂ አሰልጣኝነት በመሩበት ግማሽ ሲዝን ለቡድኑ ጠንካራ አቋምን አስገኝተውለት እንደነበር ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የቼልሲው ባለቤት ሮማን ኢብራሞቪች በሚጠበቀው መልኩ ጆሴ ሞውሪኖን ከስራቸው ካነሷቸው ጉስ ሂድኒክን አዲሱ የክለባቸው ዋና አሰልጣኝ አድርገው መቅጠርን በቅድሚያ ምርጫቸው ቢያደርጉት አስገራሚ ሊሆን አይችልም፡፡
mourinho

ሂድኒክ የ2008-09 ሲዝን ከተጋመሰ ወዲህ የቼልሲን ስራ ተረክበው የቡድኑ ያልተረጋጋ አቋምን በፍጥነት ለማረም የቻሉበትን ያንን ተደናቂ ተግባራቸውን በማስታወስ በርካታ የፉትቦል ተንታኞች በዘንድሮ ሲዝን የቼልሲ የእስካሁን ችግሮች ትክክለኛው የመፍትሄ እርምጃን ሊያበጁለት የሚችሉበት ተደናቂ ተሰጥኦን ተላብሰዋል የሚል እምነት አሳድረውባቸዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር ለበርካታ ዓመታት በዘለቀው የአሰልጣኝነት ሙያቸው በርካታ ክለቦችና የተለያዩ አገሮችን ብሔራዊ ቡድኖችን በዋና አሰልጣኝነት የመሩት ሂድኒክ በቼልሲ ደጋፊዎችና በክለቡ አባላት በጠቅላላ እስካሁንም ድረስ ከፍተኛ የሆነ ከበሬታን አሳድረው ዘልቀዋል፡፡

‹‹እንደ ቼልሲ ያለው ትልቅ ውድቀትን በሌላ ክለብ አላስታውስም››
አለን ሽረር
ፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ ጆሴ ሞውሪኖ ባለፈው ሲዝን ቼልሲ ከፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮንነት ክብር ጋር ያገናኙት ሙሉው ሲዝንን በደረጃው ሰንጠረዥ አናት ላይ በማስቀመጥና የቅርብ ተቀናቃኙ ማንችስተር ሲቲን በስምንት ነጥቦች በልጦት እንዲጨርስ በማስቻል ነው፡፡ በዘንድሮው ሲዝን ግን ገና የመጀመሪያዎቹ 10 የፕሪሚየር ሊግ ግጥሚያዎች ከመደረጋቸው ከሊጉ መሪ ማንችስተር ሲቲ በ11 ነጥቦችና በአስር ደረጃዎች ላይ ተቀምጦ ይገኛል፡፡
ከእስካሁኑ 10 የሊጉ ግጥሚያዎች 15 ጎሎችን አስቆጥሮ መረቡን በ19 ጎሎች ማስደፈሩም ሌላው የቼልሲ አስደንጋጭ የአቋም መውረድ ችግር እንዲከሰትበት የሚያሳይ ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ አንዱ ምክንያት አብዛኛዎቹ የቡድኑ ተሰላፊዎች አቋም ወርዶ መገኘት ነው፡፡ ባለፈው ሲዝን የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ድሪም ቲም ምርጫ ከተካተቱት 11 ተጨዋቾች ውስጥ ስድስቱ የቼልሲ ተጨዋቾች ነበሩ፡፡ በዘንድሮ ሲዝን ግን አንድም በጥሩ አቋም ሊጠቀስ የሚችል ተጨዋች እስከመጥፋት ደረጃ ደርሷል፡፡

እነዚህ እውነታዎችን በመተንራስ የቀድሞው የኒውካስል ዩናይትዱ ስታር አለን ሽረር ሰሞኑን በሰነዘረው አስተያየቱ የቼልሲ በፍጥነት የአቋም መውረድን ‹‹ከዚህ በፊት በሌላ ክለብ ያልታየ አስደንጋጭ አጋጣሚ›› በማለት ገልፆታል፡፡ የቀድሞው የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ዝነኛ የአጥቂ መስመር ተጨዋች በመቀጠልም ‹‹እኔ እስከማስታውሰው ድረስ እንደ ቼልሲ ሁሉ በጥቂት ወራት ውስጥ ከነበረበት ትልቅ አቋም በፍጥነት ሙሉ ለሙሉ ወደ ታች የወረደ ክለብ በእንግሊዝ ክለብ አልታየም፡፡ የቼልሲ በአስደንጋጭ ሁኔታ ወርዶ መገኘት በክለቡ ውስጥ አንድ ግልፅ ያልታየ ከፍተኛ ችግር ተፈጥሯል የሚል ጥርጣሬን እንዳሳድር አስገድዶኛል፡፡ ከእነዚህ ችግሮች ውስጥ ምናልባትም አንዱ ሞውሪንሆ በስኳዳቸው የሚመኙት ትክክለኛዎቹ ተጨዋቾች አለማግኘታቸው ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም ግን ማንኛውም የፉትቦል አፍቃሪና አስተያየት ሰጪ ቢሆን በዘንድሮው ሲዝን በቼልሲ ላይ የተፈጠረውን መሰረታዊ ችግሮች ምንነትን በትክክል ይረዳዋል የሚል እምነት በጭራሽ የለኝም›› የሚል አስተያየት ሰጥቷል፡፡

የስፖርትስ ሜይል የፉትቦል ተንታኞች በበኩላቸው ጆሴ ሞውሪኖ በኦገስት ወር በቼልሲ የዘንድሮ ሲዝን የመጀመሪያው ከስዋንሲ ሲቲ ጋር 2ለ2 ሲለያይ ለክለባቸው ዶክተር ኢቫ ካርኔሮ ጋር ግጭትን ከፈጠሩ ወዲህ ቡድናቸው ካደረጋቸው ግጥሚያዎች ግማሽ ያህሉን መሸነፉን ከግንዛቤ በማስገባት ከዛ ወዲህ በምዕራብ ለንደኑ ክለብ ላይ የተፈጠሩትን ችግሮችን ከዚህ በታች ባለው መልኩ ዘርዝረዋቸዋል፡፡

ኦገስት 8፡-
ጆሴ ሞውሪኖ የክለባቸው ዶክተር ኢቫ ካርኔሮና ረዳቷን ጆን ፍርንን የሚተች መግለጫን በመስጠት በክለባቸው ችግር እንዲቀሰቀስ በር ከፋች ሆነዋል፡፡ በሞውሪኖና በህክምና ባለሙያዎቹ መካከል ተፈጠረው ግጭት ተካርሮ በመዝለቁ ፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ በእንግሊዝ ፉትቦል ማህበር እስከመከሰስ ደረጃ ደርሰዋል፡፡ ሆኖም ግን ካርኔሮን በብልግና ቃላት ሰድበዋል በሚል ከቀረበባቸው ክስ ካለምንም ቅጣት አምልጠዋል፡፡ በዚህ በመበሳጨት የህክምና ዶክተሯ በቼልሲ የነበራትን ስራ በራሷ ፈቃድ ለመልቀቅ ወስናለች፡፡

ኦገስት 16
ቼልሲ በኢትሃድ ስቴዲየም በማንችስተር ሲቲ 3ለ0 በተረታበት የፕሪሚየር ሊግ ግጥሚያው ወቅት ጆሴ ሞውሪኖ ባልተለመደ መልኩ የቡድናቸው አምበል ጆን ቴሪን ቀይረው አስወጥተውታል፡፡ ከዛ በኋላ ባሉት ጥቂት ግጥሚያዎች ላይም ቴሪን በመደበኛ ቋሚ አሰላለፋቸው ውጪ በማድረግ የክለባቸው ደጋፊዎችን ቅር አሰኝተዋቸዋል፡፡ ቼልሲ የፕሪሚየር ሊግ ውድድር የመጀመሪያዎቹ ሁለት ግጥሚያዎችን ለማሸነፍ ሲሳነው ዘንድሮ ከድፍን 17 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡

ኦገስት 29
ሞውሪኖ ቼልሲን በስታምፎርድ ብሪጅ የመሩበት 100ኛው የፕሪሚየር ሊግ ግጥሚያው በሽንፈት ተደምድሟል፡፡ በክሪስታል ፓላስ 2ለ1 የተሸነፈበትን ጨምሮ ሞውሪኖ በራሳቸው ሜዳ ባደረጓቸው 100 የፕሪምየር ሊግ ግጥሚያዎች ሽንፈት ሲደርስባቸው ያ ለሁለተኛ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ በዛ ግጥሚያ ኮሎምቢያዊው ኢንተርናሽናል ራዳሜል ፉልካኦ ለቼልሲ በውሰት ውል ከፈረመ ወዲህ የመጀመሪያውን ጎሉን ለማስቆጠር ቢችልም በስሙ ያስመዘገባት ጎል ግን ቼልሲን ከሽንፈት ሳታድነው ቀርታለች፡፡

ሴፕቴምበር 13
የሞውሪኖ ቡድን የጉድሰን ፓርክ ስቴዲየም ከኤቨርተን ጋር ያደረገው የፕሪሚየር ሊግ ግጥሚያውን 3ለ1 በሆነ ውጤት በሽንፈት ለማጠናቀቅ ተገድዷል፡፡ በዛ ግጥሚያ የኤቨርተን አጥቂ ስቴቨን ሃይስሚዝ ሶስት ጎሎችን በማስቆጠር ሃትሪክ የሰራው የቼልሲው የተከላካይ መስመር ከተሰለፉት ጆን ቴሪና ለፈረንሳዊው ወጣት ተከላካይ ኩርትዙማ ከአቅማቸው በላይ የሆነ እጅግ ውጤታማ የማጥቃት እንቅሰቃሴን በማድረግ ነው፡፡ እስከዛ ደረጃ ድረስም ቼልሲ በመጀመሪያዎቹ 5 የሊጉ ግጥሚያዎቹ በእያንዳንዱ ላይ ቢያንስ ሁለት ጎሎች ተቆጥረውበታል፡፡ ከአምስቱ ግጥሚያዎች በአጠቃላይ ያገኘው ነጥብ አራት ብቻ ነበር፡፡

ሴፕቴምበር 19
ቼልሲ አርሰናልን 2ለ0 በረታበት የፕሪሚየር ሊግ ግጥሚያ ወቅት የቡድኑ የፊት አጥቂ ዲያጎ ኮስታ ከሎረን ኮስኒሌይ ጋር በፈጠረው ግጭት ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ በእንግሊዝ ፉትቦል ማህበር የሶስት ተከታታይ ግጥሚያዎች የእገዳ ውሳኔ ተላልፎበታል፡፡ እስከዚህ ጨዋታ ድረስ ኮስታ ከአንድ የፕሪሚየር ሊግ ጎል በስተቀር ለማስቆጠር አልቻለም፡፡ ሆኖም ግን ሞውሪኖ ኮስታ ለሶስት ግጥሚያዎች የታገደበት ውሳኔን በመተቸት በእንግሊዝ ፉትቦል ማህበር ላይ የሰላ ትችትን ሲሰነዝሩ ተደምጠዋል፡፡

ሴፕቴምበር 29
ጆሴ ሞውሪኖ በ2004 ለአውሮፓ ሻምፒዮንነት ክብር ወደመሩት ፖርቶ ሜዳ ተመልሰው ባደረጉት የቻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያ ቡድናቸው 2ለ1 በሆነ ውጤት ተሸንፏል፡፡ በዛ ግጥሚያ ሞውሪኖ ኤደን ሃዛርድና ኔማኒያ ማቲችን ለቡድናቸው መደበኛ ቋሚ አሰላለፍ ውጪ ያደረጉበት ተግባር ስህተት የፈፀሙበት ተደርጎ ተቆጥሯል፡፡ ከፖርቶ ጎሎች ለአንዷ መገኘት ጥፋትን የፈፀመው ኩርት ዙማን በመደበኛ ቋሚ ተሰላፊነት በማስጀመር ጆን ቴሪን በተጠባባቂ ወንበር ላይ ያስቀመጡበት ተግባራቸውን ለቡድናቸው ሽንፈት ተወቃሽ የሆኑበት ሌላው ጉዳይ ሆኗል፡፡

ኦክቶበር 3
ቼልሲ በሳውዝአምፕተን 3ለ1 በተረታበት የዘንድሮ ሲዝን የፕሪሚየር ሊግ ውድድር 4ኛው ሽንፈቱ በኋላ ለሞውሪኖ ኃላፊነት ለትልቅ አደጋ ተጋልጧል፡፡ ከግጥሚያው ሶስት ቀናት በኋላ የቼልሲ ቦርድ ባወጣው ይፋዊ መግለጫው ግን ለሞውሪኖ ሙሉ ድጋፍን መስጠትን ምርጫው አድርጎታል፡፡ ሞውሪኖ በሳውዝአምፕተን የተረቱበት ግጥሚያ የመሩት አርቢትር ሮቤርቶ ማድሌይን በይፋ በመተቸታቸው በእንግሊዝ ፉትቦል ማህበር 50 ሺ ፓውንድ የገንዘብ ቅጣት ተላልፎባቸዋል፡፡

ኦክቶበር 17
ያለፈው ሲዝን የፕሪሚየር ሊግ ኮከብ ተጨዋች የሆነው ኤደን ሃዛርድ ቡድናቸው አስቶንቪላን 2ለ0 በረታበት የፕሪሚየር ሊግ ግጥሚያ ከመደበኛ ቋሚ አሰላለፋቸው ውጪ አድርገውታል፡፡ በኋላ ላይ በሰጡት መግለጫም የቤልጂየሙ ኢንተርናሽናል የዘንድሮው ሲዝን አቋሙን ከወትሮ በብዙ መልኩ የወረደ በማለት ተችተውታል፡፡

The post Sport: በቼልሲ ዙሪያ የተዘጋጀ ልዩ ዘገባ | ጉስ ሂድኒክ የቼልሲ ስራን ለመያዝ ተዘጋጅተዋል appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 419

Trending Articles