Quantcast
Channel: ስፖርት | ዘ-ሐበሻ (ZeHabesha) - Latest Ethiopian News Provider
Viewing all articles
Browse latest Browse all 419

የአሰልጣኝ ክላውዲዮ ራኒዮሪ አስደናቂ የስኬት መንገድ

$
0
0

 ስሜነህ ታደሰ | ለዘ-ሐበሻ ስፖርት

ጣልያናዊው አሰልጣኝ ክላውዲዮ ራኒዮሪ በአሰልጣኝነት ህይወታቸው እጅግ የተገፉ ነበሩ፡፡  አሰልጣኙ በሌይስተር ሲቲ ስኬታማ ጊዜያትን ከማሳለፋቸው በፊት በርካታ ክለቦችን አሰልጥነዋል፡፡ የመጀመሪያ ክለባቸው ካግሊያሪ ነበር፤ አሰልጣኙ የጣልያኑን ክለብ በ1988 ተረክበው ከሴሪ ቸ ወደ ሴሪ አው እንዲያድግ አስችለዋል፡፡

claudio Ranieri

ቀጥሎ የተረከቡት ናፖሊን በ1991 ነበር፡፡ ያም ቢሆን በወቅቱ ዲያጎ ማራዶና ከአበረታች ዕፅ ጋር በተያያዘ ለ15 ወራት በመታገዱ ራኒዮሪ ከአርጀንቲናዊው ጋር አብረው ለመስራት አልታደሉም፡፡ በሳን ፓውሎ ሁለት ዓመት ቢቆዩም ምንም አይነት ስኬት አላስመዘገቡም፡፡ እዚያ በነበራቸው ቆይታ በበጎ ጎኑ ሊነገርላቸው የሚችለው ነጥብ ጂያንፍራንኮ ዛላን ወደ ዋናው ቡድን ማምጣታቸው ነው፡፡

ናፖሊን ከለቀቁ በኋላ ቀጣይ ማረፊያቸው ፊዮረንቲና ነበር፡፡ የፍሎረንሱን ክለብ ከሴሪ ቢ ወደ ሴሪ አው በማምጣት ከጋብሪዬል ባቲስቱታ ጋር አስደሳች ጊዜያትን አሳልፈዋል፡፡ ከፊዮረንቲና ጋር የ1996 የኮፓ ኤታሊያ እና ሱፐር ካፕ ዋንጫዎችን አንስተዋል፡፡

ከፊዮረንቲና ጋር ስኬታማ ዓመት ካሳለፉ በኋላ ቀጣይ ማረፊያቸው ቫሌንሲያ ነበር፡፡ ከሜዲትራኒያኑ ክለብ ጋር የኮፓ ዴልሬይ ዋንጫ በ1999 ካነሱ በኋላ በዚያኑ ክረምት አትሌቲኮ ማድሪድን ተረክበዋል፡፡ አሁን በሚገኝበት ደረጃ ላይ ያልነበረው አትሌቲኮ ማድሪድ ከሶስት ዓመት ቀደም ብሎ የላ ሊጋ እና ኮፓ ዴል ሬይ ዋንጫ አንስቶ የጥምር ድል ባለቤት ቢሆንም ራኒዮሪ ወደ ቪቼንቴ ካልዴሮን ባመሩበት ወቅት በአስተዳደራዊ ጉዳዮች ችግር ውስጥ ወድቆ ነበር፡ በሊጉ መጠናቀቂያ አካባቢ ከወራጅ ቀጣና አንድ ደረጃ ብቻ ከፍ ብሎ ሲቀመጥ ራኒዮሪ በገባ ፈቃዳቸው ከኃላፊነታቸው ተነሱ፡፡

ያም ቢሆን ራኒዮሪ ከቀዩ እና ነጩ ቤት ከተሰናበቱ በኋላ ሴፕቴምበር 18/2000 ወደ እንግሊዝ በማምራት የቼልሲ ሁለተኛው ጣልያናዊው አሰልጣኝ ሆኑ፡፡ በስታምፎርድ ብሪጅ በነበራቸው የአራት ዓመት ቆይታ ግን ስኬታማ መሆን አልቻሉም፡፡ ከእርሳቸው በፊት ቼልሲ ሁለት የኤፍኤ ካፕ እና ሊግ ካፕ ዋንጫዎችን ማንሳት ቢችልም እርሳቸው ይሄንን ማሳካት አልቻሉም፡፡

በቼልሲ ሳሉ እንግሊዘኛ ለመናገር ተቸግረው የነበሩት ራኒዮሪ አስተርጓሚ አለመፈለጋቸው አስገራሚ አጋጣሚ ነበር፡፡ በንፅፅር ጥቂት ስኬት ያስመዘገቡት ክላውዲዮ በየጨዋታው ቋሚ 11 መለዋወጣቸው ‹‹ፈላስፋው አሰልጣኝ›› አስብሏቸዋል፡፡

በመጀመሪያ ዓመታቸው ዊሊያም ጋላስ እና ፍራንክ ላምፓርድን አስፈርመው ለቡድኑ መሰረት የጣሉት ራኒዮሪ ከቼልሲ በተሰናበቱበት የመጨረሻው ዓመት ክለቡን በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በቻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ እንዲሆን አስችለው ሩብ ፍፃሜ እንዲደርስ አድርገዋል፡፡

በወቅቱ እንግሊዝን በመወከል በቻምፒዮንስ ሊጉ የሚሳተፉ ክለቦች ቁጥር ሶስት ነበር፡፡ ማንችስተር ዩናይትድ እና አርሰናል የመጀመሪያዎቹ ሁለት ደረጃዎች ያለማቋረጥ መቆናጠጣቸው እንዲሁም ሊቨርፑል እና ሌድስ ዩናይትድ እየተፈራረቁ ሶስት ደረጃ መያዛቸው ለራኒዮሪ ፈታኝ ሆኖ ቆይቷል፡፡

ሆኖም ራኒዮሪ በቼልሲ ሁለተኛ ዓመታቸውን ከያዙ በኋላ እንግሊዝን በመወከል በአውሮፓ የሚሳተፉ ክለቦች ቁጥር ወደ አራት ከፍ አለ፡፡ ሆኖም ሊድስ ዩናይትድ በገንዘብ ችግር ምክንያት እየወረደ ሲመጣ ኒውካስል ዩናይትድ በቼልሲ ላይ የበላይነቱን ወሰደ፡፡

ቼልሲ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በቻምፒዮንስ ሊጉ መሳተፍ የቻለው በራኒዮሪ ሶስተኛ ዓመት የመጨረሻ ጨዋታ ሊቨርፑል በማሸነፍ ነበር፡፡ የምዕራብ ለንደኑ ክለብ በታላቁ የአውሮፓ መድረክ በተሳተፈበት ዓመት የራሺያው ከበርቴ ሮማን አብራሞቪች ክለቡን ተረከቡ፡፡ ከፍተኛ ክፍያ ፈፅመውም ዳሚዬን ዳፍ፣ ሄርናን ክሬስፓ እና በሪያል ማድሪድ የተገፋውን ክሎድ ማኬሌሌን አስፈረሙ፡፡

Claudio+Ranieri+

ሆኖም አርሰናል ያለሽንፈት የሊጉን ዋንጫ ሲያነሳ ቼልሲ የሊጉ ሻምፒዮን ማንቸስተር ዩናይትድ በልጦ ሁለተኛ ደረጃ ይዞ መፈፀሙ የመሻሻሉ በጎ ምልክት ነበር፡፡ በ1965 የሊጉን ዋንጫ ካነሳ በኋላ ትልቁ ውጤት መሆኑ በበጎ ጎኑ ታይቷል፡፡

ራኒዬሪ በቼልሲ አራት ዓመት ከቆዩ በኋላ በአሰልጣኝ ጆዜ ሞውሪንሆ ተተክተው ከስታምፎርድ ብሪጅ ጋር ተለያዩ፡፡ ሆኖም በዚያ የውድድር ዘመን ሩብ ፍፃሜ ላይ አርሰናልን አሸንፈው ግማሽ ፍፃሜ መድረሳቸው አስደሳች ነበር፡፡ ጋላስ እና ላምፓርድን ማምጣታቸው በቀጣይ ለተመዘገበው ስኬት እጃቸው ነበረበት አስብሏል፡፡

ጣልያናዊው የእንግሊዝ ቆይታቸው አስደሳች ሊባል ይችላል፤ ጥሩ ሰብዕና አላቸው፡፡ ከሚዲያው ጋር ያላቸው ግንኙነት በወዳጅነት ስሜት የተሞላ ነው፡፡ የሞውሪንሆን ያህል የስኬት ታሪክ ባይኖራቸውም ቼልሲን ከተሰናበቱ በኋላ የላ ሊጋ እና ዩሮፓ ሊግ ዋንጫዎችን ባነሱት ራፋ ቤኒቴዝን ተክተው ቫሌንሲያን በድጋሚ ተረከቡ፡፡

በአዲሱ ክለባቸው የአውሮፓ ሱፐር ካፕ ዋንጫን ማንሳት ቢችሉም አራት ጣልያናውያን ተጨዋቾችን ማስፈረማቸው በደጋፊዎቹ ዘንድ አልተወደደላቸውም ነበር፡፡ ቫሌንሲያ ከምድቡ ማለፍ ተስኖት በቻምፒዮንስ ሊጉ በጊዜ ሲሰናበት፤ በዩሮፓ ሊግ በስቱዋ ቡካሪስት ሽንፈትን አስተናግዶ ከውድድሩ ውጭ ሆነ፣ ራኒዮሪም ለስንበት ተዳረጉ፡፡

ከሁለት ዓመት በኋላ አሰልጣኙ ፓርማን ተረከቡ፣ ታሪካውያን ክለብ በሴሪአው እንዲቆይ ማድረጋቸው በበጎ ጎን ሊታይ ቢችልም እዚያ ብዙም ሳይቆዩ ዲዲዬ ዴቮ ከሴሪ ቢ ወደ ሴሪ አው ያሳደገውን ጁቬንቱስ ተረከቡ፡፡

ከአንፃሩ በጁቬንቱስ የጨዋታ ማጭበርበር ቅሌት ምክንያት ሴሪ አውን በበላይነት የተቆጣጠረው ኢንተር ሚላን የራኒዮሪን ተቀናቃኝ ጆዜ ሞውሪንሆን ሾመ፡፡ በጁቬንቱስ ሁለት ዓመት ቆይተው ስኬት ማምጣት ያልቻሉት ክላውዲዮም ከኃላፊነታቸው ተነሱ፡፡

የራኒዮሪ ጉዞ አሁንም ቀጥሏል፡፡

በቀጣይ ሮማ አና ኢንተር ሚላንን ቢረከቡም የተለየ ውጤት ማምጣት ተሳናቸው፡፡ በ2012 ሞናኮን ተረከቡ፤ የፈረንሳዩን ክለብ ከፈረንሳይ ሊግ ደ ወደ ፈረንሳይ ሊግ ኧ ማሳደግ ቻሉ፡፡ በ2014 በሊጉ ሁለተኛ ደረጃ ይዞ እንዲፈፅም ማድረግ ቢችሉም ክለቡ የውድድር ዓመቱ ሲጠናቀቅ ኮንትራታቸውን ሊያራዝም ፍላጎት አልነበረውም፡፡

ከፈረንሳይ መለስ ቀጣይ ጉዞዋቸው ወደ ግሪክ ሆነ፡፡ እዚያ ሁለት ዓመት ቆይተው የነበረ ቢሆንም ስንብታቸው አስደሳች አልነበረም፡፡ ከምንም በላይ በሜዳቸው በፋሮ ደሴቶች የደረሰባቸው ሽንፈት የስንብታቸው ዋነኛ ምክንያት ነበር፡፡

ከዘመናት ትዕግስት በኋላ ግን በሌይስተር ሲቲ ህልማቸውን ማሳካት ችለዋል፡፡ ሌይስተር ሲቲ ከሌሎች እርሳቸው ካሰለጠኗቸው ክለቦች በሙሉ ያነሰ ቢሆንም ከስኬት ጎዳና ተጉዘዋል፡፡ የ64 ዓመቱ አሰልጣኝ በ16 አጋጣሚዎች በአሰልጣኝንነት ካመሩ በኋላ በአውሮፓ እግርኳስ ታሪክ ምርጡን ውጤት ለማስመዝገብ ከመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሰዋል፡፡

ለራሳቸው ‹‹ክርስቶፎር ኮሎምበስ›› የሚል ስም የሰጡት አሰልጣኝ ማንም ግምት ያልሰጣቸውን ጂሚ ቫርዲ፣ ንጎሎ ካንቴ እና ሪያድ ማህሬዝን ለታላቅ ስኬት አብቅተዋል፡፡ የውድድር ዓመቱ ሲጀመር የ40 ነጥብ ግብ አስቀምጠው ዓላማቸው በሊጉ መቆየት እንደሆነ ያረጋገጡት ራኒዬሪ በመጨረሻም የሊጉ ሻምፒዮን በመሆን ክብር መቀዳጀታቸው በጣም ይገርማል፡፡

ሌይስተር ሲቲ ባለፈው ዓመት ከሊጉ ላለመውረድ በጣም ብዙ ታግሏል፡፡ አሰልጣኝ ናይጅል ፒርሰን እና ተጨዋቾቻቸው እጅግ በጣም ለፍተዋል፡፡ ያም ቢሆን ፒርሰን ከኃላፊነታቸው መነሳታቸውን ተከትሎ ኃላፊነቱን ራኒዬሪ ተረክበዋል፡፡

‹‹በኦስትርያ የቅድመ ውድድር ዝግጅታችንን እየሰራን ይበልጥ ትኩረት አድርጎ ሲነግረን የነበረው ባለፈው ዓመት የተቸገርንበትን ምስጢር ማወቅ ነበር›› ይላል- ተከላካይ ክሪስቲያን ፋችስ፡፡ ‹‹በዚህ አካሄድ ሁሉም የቡድናችን ተጨዋቾች ፍፁም ደስተኛ ነበሩ፤ ይሄንን ቡድን በምን አይነት መልኩ መሻሻል እንደሚችል ነግሮን የራሱን የጨዋታ ፍልስፍና አስረዳን፤ የነገረን ነገር ቡድናችንን አሻሽለው፤ ይበልጥ እንዲረጋጋ አደረገው፤ ጣልያናዊ በመሆኑ መከላከል ይወድዳል››

ሌይስተር ሲቲ በሊጉ የመክፈቻ ጨዋታ ሰንደርላንድን 4-5 ካሸነፈ በኋላ ወደ ኋላ አልተመለሰም፡፡ በስምንተኛው ጨዋታ ቡድኑ 5-2 እስኪሸነፍ ድረስ ያለሽንፈት የተጓዘው የራኒዬሪ ቡድን ቀጥሎ በነበሩት 10 ጨዋታዎች ላይ በድጋሚ ሽንፈት ሳያስተናግድ ጉዞውን ቀጠለ፤ ይሄ ደግሞ የአሸናፊ ቡድኖች ምልክት ነው፡፡

ራኒዬሪ የተጨዋቾቻቸውን ኳሊቲ ከግምት ውስጥ አስገብተው የነደፉት ታክቲክ የስኬታቸው አንዱ ምክንያት ነው፡፡ በታክቲኩ ረገድ ከጣልያናዊውያን አሰልጣኞች ጋር ሲነፃፀሩ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚቀመጡ ተደርገው ይታያሉ፡፡ ከጂዮቫኒ ትራፓቶኒ፣ አሪጎ ሳኪ እና ፋዚዮ ካፔሎ ጋር በጭራሽ አይነፃፀሩም፡፡ ከፊዮረንቲና የኮፓ ኢታልያ እንዲሁም በቫሌንሲያ የኮፓ ዴል ሬይ አንስተው ጥቂት መደነቅን ከመፍጠር ውጭ የስኬት ታሪክ አልነበራቸውም፡፡

በቼልሲ የመጨረሻ ዓመት ቆይታቸው ያስፈረሙት ክሎድ ማኬሌሌ የሰጣቸውን ግልጋሎት በሚገባ የተረዱት አሰልጣኝ ዘንድሮ ይሄንን ግልጋሎት በንጎሎ ካንቴ አግኝተዋል፡፡ ፈረንሳዊውን ‹‹አዲሱ ባትሪዬ›› ብለው ገልፀውታል፡፡ በአማካይ ተከላካይ ቦታ ለዚህ ተጨዋች ትልቁን ኃላፊነት የሰጡት ስዊዘርላንዳዊውን ጎክሃን ኢንለርን ችላ ብለው መሆኑ ደግሞ በጣም ይገርማል፡፡

በአጥቂ ቦታ ላይ ለቫርዲ የሰጡት ኃላፊነት በመጨረሻም ተጠቃሚ አድርጓቸዋል፡፡ እንግሊዛዊው ሳይጠበቅ ያለማቋረጥ በ11 ተከታታይ የሊጉ ጨዋታዎች ላይ ጎል በማስቆጠር በሩድ ቫን ኒስቴልሮይ ተይዞ የነበረውን ሪከርድ አሻሽሏል፡፡

የተከላካይ መስመሩ ደግሞ በጣም ይገርማል፡፡ ቬዝ ሞርጋን፣ ሮበርት፣ ሁዝ፣ ካስፐር ሺማይክል እና ፋችስን የያዘ ነው፡፡ እነኚህ ተከላካዮች እጅግ ታታሪክ ናቸው፡፡ ቀድ የሚመጣውን አደጋ ማሽተት ይችላሉ፡፡

ሌይስተር ሲቲ ስዋንሲ ሲቲን 4-0 ካሸነፈ በኋላ የሰጡት አስተያየት ቡድናቸው ስኬታማ የውድድር ዓመት እያሳለፈ የሚገኝበትን ምስጢር ማወቅ ይችላል፤ ‹‹ተጨዋቾቹን ሁልጊዜ ቢሆን የዚህ አይነት ብቃት እንዲያሳዩ እጠይቃቸዋለሁኝ፤ ዕድል ያላቸው የረሃብ ስሜት እንዲጨምር፣ ጠንካራ እና በከፍተኛ ደረጃ ተጭነው እንዲጫወቱ ነግሬያቸው ነበር፤ ይኼንንም በሚገባ አሳክተዋል›› ብለው ተጨዋቾቻቸውን አወድሰዋል፡፡

የራኒዬሪ እቅድ እና ፍላጎት ግልፅ ነው፡፡ ተጨዋቾቹም የአሰልጣኙን ምክር ይሰማሉ፤ ይሄ ከሆነ ደግሞ የፈተናው 50 በመቶ ተቀርፏል ወደሚል ድምዳሜ ያደርሰናል፡፡

በ2004 ቼልሲ በቻምፒዮንስ ሊግ ግማሽ ፍፃሜ በሞናኮ ደርሶ መልስ ውጤት ተሸንፎ ፍፃሜ ለመግባት የነበረው ህልም ባልተሳካበት አጋጣሚ ትልቅ ትምህርት የቀሰሙት ራኒዬሪ አሁን ከስህተታቸው በጣም ብዙ ነገሮችን ተምረዋል፡፡ በቋሚ አሰላለፍ 27 ጊዜ ለውጥ ያደረጉት አሰልጣኝ አሁን ከተጨዋቾቻቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት በጣም ያስቀናል፡፡

በፒርሰን ዘመን የነበረውን በሶስት ተከላካዮች የመከላከል ታክቲክ በአራት ተከላካዮች ተክተዋል፡፡ ይሄ ውሳኔ የተከላካይ መስመሩን አሻሽሎታል፡፡ በመጀመሪያዎቹ ዘጠኝ የሊግ ጨዋታዎች ጎሉን አለማስደፈር ያልቻለው የተከላካይ መስመሩ ካለፉት 17 ጨዋታዎች በ12 ያህሉ ጎል ተቆጥሮበታል፡፡

‹‹በምን አይነት መልኩ በሊጉ መቆየት እንዳለብን ነግሮናል፡፡ በታክቲክ ጉዳዮች ላይ የነበረው ብቃት በጣም ይገርማል›› ይላል ሞርጋን፡፡

ጎሎችን ከተለያየ አቅጣጫ የሚያስቆጥረው የራኒዬሪ ቡድን የቫርዲ ጥገኛ ነው ቢባልም እንግሊዛዊው ባልተሰለፈባቸው ስድስት ጨዋታዎች በአምስቱ አሸንፏል፡፡ በአንዱ አቻ ተለያይቷል፤ ከቫርዲ ውጭ ማህራዝን አለማንሳት በጣም ከባድ ነው፡፡ 17 ጎሎችን አስቆጥሮ 11 ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ ያቀበለው አልጀርያዊው ኮከብ የፒኤፍኤ አሸናፊ ሆኗል፡፡ በአጠቃላይ በሌይስተር ሲቲ የዘንድሮ የስኬት ጉዞ የራኒዬሪ የጨዋታ እቅድ ተጨዋቾችን የመቆጣጠር ብቃት እና የቡድን ህብረት የፈጠሩበት መንገድ ትኩረትን እንዲስብ አድርጓል፡፡ አሁን ትኩረቱ በሙሉ ሌይስተር ሲቲ እና ራኒዬሪ ላይ አርፏል፡፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 419

Trending Articles