ስሜነህ ገመቹ | ለዘ-ሐበሻ ስፖርት
በዩሮ 2016 ውድድር ውጤታማ እግርኳስን በማበርከት ልዩ ትኩረትን ከሳቡት ተጨዋቾች ውስጥ ቤልጅየማዊው ኢንተርናሽናል ሚኪ ባትሹአይ አንዱ ነው፡፡ ይህንን የ22 ዓመቱ የአጥቂ መስመር ተጨዋች ኦሎምፒክ ማርሴይ በጁላይ 2014 ከስታንዳርድ ሊዬዥ በ4.5 ሚልየን ፓውንድ ከገዛው ወዲህ ለክለቡ በ78 ግጥሚያዎች ላይ ተሰልፎ 33 ጎሎችን ለማስቆጠር መቻሉም በርካታ ክለቦች ፊርማውን ለማግኘት ከፍተኛ ጉጉትን እንዳያሳድሩበት ምክንያት ሆኖታል፡፡
በመጨረሻም ግን ባትሹአይ በውጤታማው ጣሊያናዊ አሰልጣኝ አንቶኒዮ ኮንቴ ስር ለቼልሲ መሰለፍን በመምረጥ በ33 ሚልየን ፓውንድ ስታምፎርድ ብሪጅ ደርሷል፡፡ ለቼልሲ የመፈረም ውሳኔ ላይ እንዲደርስ አንዱ ምክንያት የሆነውም የቤልየም ብሔራዊ ቡድን ጓደኞቼ የሆኑት ኤደን ሃዛርድ እና ቲቧ ኩርቷ ጋር አብሮ የክለቡ ፉትቦሉን ለማድረግ በመመኘት መሆኑን ተናግሯል፡፡
ቼልሲ ባትሹአይን ከኦሎምፒክ ማርሴይ በውድ ዋጋ ለመግዛት ምንም አይነት የማመንታት መንፈስ ያልታየበት አዲሱ አሰልጣኙ አንቶኒዮ ኮንቴ ለሚከተሉት 3-5-2 የጨዋታ ሲስተም ከዲያጎ ኮስታ ጎን ከቡድናቸው ሁለት የፊት አጥቂዎች አንዱ በመሆን ያማረ የማጥቃት እንቅስቃሴን ለመፍጠር የሚችልበት የጨዋታ ስታይልና ተደናቂ ብቃቶችን አሟልቶ መያዙን ስላመኑበት ነው፡፡
የግል አድናቂዎቹ በስሙ ላይ ባት የሚል ቃል በመኖሩ ከክሪኬት ስፖርት ተጨዋቾች ጋር በማዛመድ ባትስ ማን የሚል ተቀፅላን ያወጡለት የ22 ዓመቱ ቤልጅየማዊ ከቼልሲ ቲቪ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስም ለምዕራብ ለንደኑ ክለብ ገና ለመጀመሪያ ጊዜ ከምሰለፍበት ግጥሚያ አንስቶ የወጣበት ዋጋን የሚመጥን ውጤታማ እግርኳስን ለማበርከት እንደሚችል እርግጠኝነቱን አንፀባርቋል፡፡
በተለይም ቼልሲ ባለፈው የውድድር አመት የነበረውን ደካማ ውጤትን ለመቀየር እንዲችል የበኩሉን ቁልፍ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው በማመን ባትሹአይ መግለጫውን የሰጠው ‹‹ወደዚህ ትልቅ ክለብ የመጣሁበት ዋነኛ አላማዬ ቼልሲ በአዲሱ የውድድር አመት ምንም አይነት የማመንታት መንፈስ ያልታየበት አዲሱ ወደወርቃማ ዘመኖች እንዲመለስ እንደምረዳው እርግጠኛ በመሆኔ ነው፡፡ በውጤታማ ባለሙያነቱ በማደንቀው አዲሱ አሰልጣኝ አንቶኒዮ ኮንቴ ስር ለዚህ ክለብ መጠናከር የተነደፈው እቅድንም ተደናቂ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡
ኮንቴ የስራ ተግባሩን በጠንካራ ሁኔታ የመስራት ባህል ያለው አሰልጣኝ በመሆኑ ከዚህ በፊት ጁቬንቱስ ለድፍን ሶስት ዓመታት ከአውሮፓ ጠንካራ ቡድኖች አንዱ ያደረገበት ተደናቂ ተግባሩን በቼልሲም ገና በመጀመሪያው ሲዝኑ እንደሚደግሙለት አምንበታለሁ፡፡ እኔ በግሌም የቤልጅየም ብሔራዊ ቡድን ጓደኞቼ ኤደን ሃዛርድና ቲቧ ኩርቷን ጨምሮ በቼልሲ የምሰለፍበት በርካታ ምርጥ ብቃት ያላቸው ተጨዋቾች በዙሪያዬ ባሉበት ሁኔታ በመሆኑ ከእስካሁኑም በብዙ የተሻለ ስኬታማ ሲዝንን ለማሳለፍ እንደምችል እርግጠኛ ነኝ፡፡ ከወዲሁም በ2016-17 ሲዝን ያለኝ ዋነኛ አላማ ቼልሲን ደግሞ ለእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮንነት ክብር በማብቃት በአንድ ዓመት ጊዜ ወደ ቻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ተሳትፎ ለመመለስ እንዲችል መርዳት ነው›› በማለት ነው፡፡
ባትሹአይ በሌሎች ጉዳዮች ለቀረቡለት ጥያቄዎች ከሰጠው ምላሽ ከዚህ በታች ያለው ይገኝበታል፡፡
ጥያቄ፡- ትልቁ ጠንካራ ጎኔ ነው የምትለው የትኛውን ብቃትህን ነው?
መልስ፡- ገና የ22 ዓመት ወጣት በመሆኔ ሁሉንም አይነት ብቃቶች ይዣለሁ በሚል ራሴን ላኩራራው አልሻም፡፡ ምክንያቱም እስካሁንም ድረስ የምማራቸውና የማሻሽላቸው ተጨማሪ ኳሊቲዎች እንዳሉኝ አምናለሁ፡፡ በእርግጥ ከእኔ ጠንካራ ጎኖች ውስጥ የቴክኒክ ብቃቴ ከፍተኛነትና በሁለቱም አገሮቼ ተመጣጣኝነት ባለው መልኩ የምጫወትበት አስተማማኝ ተሰጥኦን መላበስ መቻሌ መሆኑን አምናለሁ፡፡
ጥያቄ፡- በቼልሲው አዲስ አሰልጣኝ አንቶኒዮ ኮንቴ ስር ለመጫወት ያለህ ጉጉት ምን ይመስላል?
መልስ፡- በቅርቡ በአንቶኒዮ ኮንቴ ከተመራው የጣሊያን ብሔራዊ ቡድን ጋር በተደረገ የወዳጅነት ግጥሚያ ላይ ለቤልጅየም ብሔራዊ ቡድን ጎል ማስቆጠሬን አስታውሳለሁ፡፡ ያንን ግጥሚያ በተቃራኒ ቡድን ሆኜ ባደርግም አንቶኒዮ ኮንቴ እጅግ ተደናቂ ታክቲካል ብቃቶች ያሉት ውጤታማ ባለሙያ መሆኑን ለመረዳት አስቸጋሪ አልሆነብኝም ነበር፡፡ ከዚህ አንፃር ኮንቴን ለመሰለ ምርጥ ብቃትን በተላበሰ ባለሙያ ስር ለቼልሲ ለመጫወት ዕድል የተፈጠረልኝ መሆኑን ለእኔ ትልቅ አጋጣሚ እንዲመጣልኝ የምቆጥረው ይሆናል፡፡ ከወዲሁም ከአንቶኒዮ ኮንቴ ጋር ለቼልሲ ስለምፈርምበት ጉዳይ ዙሪያ ተገናኝቼ ለአጭር ጊዜ የማውራት ዕድልን አግኝቻለሁ፡፡ በውይይታችን ወቅት ኮንቴ በጥሩ ሁኔታ እንግሊዝኛ ቋንቋን ለመናገር እንደሚችል ለመረዳት ችያለሁ፡፡ የእኔ እንግሊዝኛ ቋንቋ ግን ጥሩ የሚባል እንዳልሆነ አልደብቅም፡፡
ጥያቄ፡- በቅርብ ዓመታት ውስጥ የቼልሲ ግጥሚያዎችን ተመልክተሃል?
መልስ፡- በዚህ አገር ያለው ሊግ ውድድር በመላው ዓለም ሰፊ ተወዳጅነት ያለው በመሆኑ እኔም በየሳምንቱ የዚህ የሊግ ውድድር ግጥሚያዎች በመደበኛነት በቲቪ በመከታተል ዘልቄያለሁ፡፡ የቼልሲ ግጥሚያዎችንም በበቂ ሁኔታ መመልከቴን አምናለሁ፡፡
ጥያቄ፡- ይበልጥ የምትወደውና የምታደንቀው የዓለማችን ዝነኛ እግርኳስ ተጫዋች ማን ነበር?
መልስ፡- በማደግ ላይ እያለሁ የብራዚላዊው ዝነኛ ሮናልዶ አድናቂ ሆኜ ዘልቄያለሁ፡፡ ስለ እውነቱም ለመናገር ሮናልዶ አስገራሚ ክስተት የሆነ የተለየ አይነት ዝነኛ የአጥቂ መስመር ተጨዋች መሆኑን አስመስክሮ የፉትቦል ህይወቱን ለማሳለፍ ችሏል፡፡
ጥያቄ፡- በፈረንሳይ በተደረገው የዩሮ 2016 ውድድር ተሳትፎህን በምን መልኩ ትገልፀዋለህ?
መልስ፡- በትልቅ ኢንተርናሽናል ውድድር ተሳትፎዬ ከመሆኑ አንፃር ለቤልጅየም ብሔራዊ ቡድን የመሰለፍ ዕድልን ባገኘሁባቸው ግጥሚያዎች ያሳየሁት የጨዋታ እንቅስቃሴን ወድጄዋለሁ፡፡ በተለይም ከሀንጋሪ ጋር ባደረግነው ግጥሚያ ተቀይሬ እንደገባሁ ገና ከመጀመሪያ ጊዜ ባገኘኋት ኳስ ጎልን ማስጠሬ ትልቅ ደስታን የፈጠረልኝ ሆኗል፡፡ ሆኖም ግን ቡድናችን በውድድሩ ሩብ ፍፃሜ በዌልስ ብሔራዊ ቡድን መሸነፉ በጭራሽ የማይታመን ሆኖብኛል፡፡ ምክንያቱም የሁላችን እምነት ቢያንስ በውድድሩ ግማሽ ፍፃሜ ደረጃ ድረስ ለመዝለቅ እንችላለን የሚል ነበር፡፡ በዚህም በዌልስ ተሸንፈን ከውድድሩ ውጪ መሆናችን ከፍተኛ የሆነ ሃዘንን የፈጠረብን መሆኑን አልደብቅም፡፡
ጥያቄ፡- በአዲስ ክለብህ በግልህ ልትፈፅመው የምትመኘው አላማህ ምንድነው?
መልስ፡- ቼልሲ እያንዳንዱ ግጥሚያዎች በድል ለማጠናቀቅ እንዲችል የተቻለኝን ሁሉ ጥረትን የማድረግ አላማ አለኝ፡፡ ተስፋ የማደርገውም ዲዲዬ ድሮግባን የመሳሰሉት የዚህ ክለብ ዝነኞች ስኬታማ ተግባር በቼልሲ ቆይታዬ ለመድገም እችላለሁ ብዬ ነው፡፡ ከወዲሁም በዚህ ክለብ ደጋፊዎች ቃል የምገባው በአዲሱ ሲዝን የደስታ መንፈስ በገፅታቸው ላይ እንዲመለስ የበኩሌን ትልቅ እርዳታን አበረክትላቸዋለሁ በሚል ነው፡፡